
ከ 5 ሰአት በፊት
ሁለት ዓመት ሊደፍን ጥቂት ወራት የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ፊቱን ወደ ድርድር መልሷል።
የፌዴራሉ መንግሥትና የህወሓት ኃይሎች አፈሙዛቸውን ካዘቀዘቁ ስድስት ወራት ገደማ ተቆጥረዋል።
ሰኔ 07/2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሰላም ድርድር ዝግጁ መሆናቸው ሲገልጡ በተመሳሳይ ዕለት የትግራይ ኃይሎች ለድርድር ክፍት መሆናቸውን የሚጠቁም ግልፅ ደብዳቤ ይፋ አድርገዋል።
ማዕከላዊው መንግሥት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ባሳወቀ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይወክሉኛል ያላቸውን ሰባት ተደራዳሪዎችን ይፋ አድርጓል።
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የሞቱበት፣ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት፣ በርካቶች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጋለጡበት የሰሜኑ ጦርነት በማዕከላዊ መንግሥትና ትግራይ ውስጥ ቢሆንም የተቀሰቀሰው ግጭቱ ወደ አጎራባች የአማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል።
አልፎም የጎረቤት አገር ኤርትራ ሠራዊት በዚህ ጦርነቱ ተሳትፎ፣ ጥፋት ማድረሱን አስመልክተው በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወቀሳ ሲሰነዝሩ ነበር።
አሁን ህወሓት እና የፌዴራሉ መንግሥት ወደ ድርድር ሲመጡ በዚህ ጦርነት የተሳተፉ እንደ ኤርትራና የአማራ ልዩ ኃይል ሊወከሉ ይገባል የሚል ድምፅ መሰማት ጀምሯል።
ምንም እንኳ የአማራ ልዩ ኃይል በዚህ ድርድር ሊወከል ይገባል ቢባልም ከፌዴራል መንግሥት ተደራዳሪዎች መካከል ክልሉን የሚወክሉ አሉ የሚል ምላሽ ይሰማል።
የኤርትራ መንግሥት በዚህ የሰላም ድርድር ሊሳተፍ ይገባል ወይ የሚለው ግን አነጋጋሪ ሆኗል።
- መንግሥት እና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ላይ ለምን መስማማት አልቻሉም?13 ነሐሴ 2022
- የመንግሥትና የህወሓት ድርድር ከኬንያ ምርጫ በኋላ ሊጀመር ይችላል ተባለ29 ሀምሌ 2022
- መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ28 ሀምሌ 2022
የሰላም ድርድሩ መጓተት
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ኅብረትን ወክለው በህወሓትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት መካከል ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ሲጥሩ ቆይተዋል።
ነገር ግን ህወሓት የኦባሳንጆ አደራዳሪነት የተዋጠለት አይመስልም። በምትኩ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት የድርድሩ አሸማጋይ እንዲሆኑ ይሻል።
የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተመራማሪ ዊሊያም ዴቪሰን ድርደሩ ከታሰበው በላይ መጓተት እያሳየ ነው ይላሉ።
“የፌዴራል መንግሥትን ወክለው የሚደራደሩ ሰዎች ስም ይፋ ሆኗል። ህወሓትም አሳውቃለሁ ብሏል። ነገር ግን ሁለቱም ወደ ተግባር አልገቡም። የፌዴራሉ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ኦባሳንጆ አደራዳሪ እንዲሆኑ ይሻል። ህወሓት ደግሞ ድርድሩ በኬንያው ፕሬዝዳንት እንዲመራ ይፈልጋል።”
ዴቪሰን፤ መንግሥትና ህወሓት ከድርድሩ በፊት ሊስማሙባቸው የሚገቡ፣ ነገር ግን ይስማሙ አይስማሙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ ይላል።
“ለምሳሌ ህወሓት መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲከፈቱ ይፈልጋል። የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ድርድሩ ቀድሞ እንዲጀመር ይሻል። ሁለቱ አካላት ከበድ ያለ ጦርነት ካደረጉ ቆየት ብሏል። ነገር ግን ወደ ሰላም ድርድር ለመምጣትም ጊዜ እየወሰዱ ነው።”
ተመራማሪው የሰላም ድርድሩ በፍጥነት መጀመር እንዳለበትና ከታሰበው በላይ ጊዜ እየወሰደ እንደሆነ ያምናል። ድርድሩን እያጓተቱ ያሉ ጉዳዮች ባልተፈቱ ቁጥር ነገሮች እየተወሳሰቡ ይሄዳሉ በማለት ስጋቱን ያጋራል።
“ድርድሩ ሳይጀመር መቆየቱ ሊያሳስብ ይገባል። ይህ በትግራይ ኃይሎችና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለው ጦርነት መልሶ እንዲያገረሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በትግራይና በኤርትራ ኃይሎች አሊያም በትግራይና በአማራ ኃይሎች መካከል ግጭት ሊነሳ እንደሚችልም አንዘንጋ።”
ዴቪሰን፤ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ቁርጠኛ መሆናቸውን ቢገልፁም፤ ለራሳቸው የሚጠቅማቸው ቅደመ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ግራ ያጋባል ይላል።

የኤርትራ ጉዳይ
ህወሓት ድርድሩን በማስመልከት ባሰራጨው ደብዳቤ፣ ውይይቱን የኬንያ መንግሥት እንዲመራውና የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ተሳታፊ እንዲሆኑ መጠየቁ ይታወሳል።
ነገር ግን በዚህ ድርድር በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት የኤርትራ መንግሥት እና የአማራ ክልል ኃይሎች በዚህ ድርድር ተሳታፊ ስለመሆናቸው በውል የተገለጸ ነገር የለም።
ሆኖም የተለያዩ የአማራ ሕዝብ ጥቅምን እናስከብራለን የሚሉ ፖለቲካዊ ኃይሎች እና የኤርትራ ተቆርቋሪዎች ሁለቱም ወገኖች መሳተፍ አለባቸው የሚል ሐሳብ ያነሳሉ።
ለህወሓት የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት የሚታወቁት አምባሳደር ፍሰሃ አስገዶም፣ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ህወሓት አምስት ነጥቦች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመው ነበር።
የትግራይ ግዛት ከጦርነት በፊት ወደነበረት እንዲመለስ፣ በትግራይ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሄድ፣ በጦርነቱ ለተፈጸሙ ግፎች ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ፣ ለደረሰው ጉዳት ካሳ እና የትግራይ ሠራዊት ትጥቅ አለማስፈታት አንኳር ነጥቦች እንደሆኑ ዲፕሎማቱ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ከጦርነቱ በፊት በትግራይ መንግሥት አስተዳደር ሥር የነበረው እና የአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳበት ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች አሁንም በአማራ ኃይሎችና በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ውስጥ ይገኛሉ።
የትግራይ መንግሥት አሁንም ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ይጠይቃል።
የኤርትራ ኃይሎች በጦርነቱ መሣተፋቸውና አሁንም ድንበር አካባቢ መገኘታቸው በድርድሩ እንዲሳተፉ ምክንያት ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
ስዊዲናዊው የሕግ እና የፖለቲካ አማካሪ ሙሴ ኤፍሬም ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም ኃይሎች ከጅምሩ በድርድሩ መሳተፍ አለባቸው ይላሉ።
“በዚህ ጉዳይ [ጦርነቱ] ኤርትራ እጇ እንዳለበት ግልፅ ነው። በቀጠናው አብሮ ለመኖር የሚያስችል ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ተዋጊዎቹ ኃይሎች ከአገር ውስጥ ይሁኑ አይሁኑ ድርድሩ ላይ መሳተፍ አለባቸው። ካልሆነ የድርድሩን ሂደት የሚበላሹ ባህርያት ልናይ እንችላለን።”
ትውልደ ኤርትራዊው የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ኤልያስ ሃብተሥላሴ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።
ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ከጅምሩ ጦርነቱ በትግራይ ክልል እና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ የመጣ ስለሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የውስጥ ግጭት ተብሎ ነው የሚጠራው” ይላሉ።
ስለዚህ በአንድ አገር ውስጣዊ ግጭት ውስጥ፣ የውጭ ኃይል እጁን አስገብቶ ከሆነ ተጠያቂ ይሆናል እንጂ ለሰላም በሚደረገው ድርድር የሚገባበት ምክንያት የለም ሲሉ ይከራከራሉ።
“በሌላ አገር ጉዳይ መግባት በሕግ የተከለከለ ነው። ስለሆነም ኤርትራ በግጭቱ ውስጥ በምን መልኩ ነው የተሳተፈችው? ለምን ተሳተፈች? መሳተፏ ያስጠይቃታል ወይ? እጇን ያስገባችበት መንገድስ ትክክል ነው አይደለም? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ።
“እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ ራሱን የቻለ ዓለም አቀፍ ሕግ አለ። አሁን የሚካሄደው ድርድር ግን የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ኤርትራ በዚህ ለመሳተፍ ሕጋዊ መሰረት የላትም።”
ዊሊያም ዴቨሰን በበኩሉ የኤርትራ መንግሥት በድርድሩ መሳተፍ ካለበት ጊዜው አሁን አይደለም ይላል።
“አሁን ያለው አንድ መልካም ነገር የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ህወሓት ለድርድር ቁርጠኛ መሆናቸውና ውጊያ ማቆማቸው ነው። የኤርትራ መንግሥት ይሳተፍ የሚለው ሐሳብ ችግር አለበት። የኤርትራ መንግሥት በዚህ ድርድር ላይ መሳተፍ እንደሚፈልግ ምን ማረጋገጫ አለ? ከኤርትራ መንግሥት የሰማነው ነገር የለም።”
ዴቪሰን ከሕግ አማካሪው ሙሴ ጋር ቢስማሙም ከጅምሩ ሳይሆን በጊዜ ሂደት ነው ኤርትራ ልትሳተፍ የሚገባው ይላል።
“እርግጥ ነው ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። ነገር ግን የሌላ አገር መንግሥት ጦር በዚህ ውስጥ ተሳትፏል። ሁሉን ያሳተፈና የተረጋጋ ሰላም መፍጠር ካስፈለገ የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ መንግሥት ጋር አንድ ቀን ንግግር ማድረግ አለባቸው።”
ጦርነቱ ካስከለተለው ሰፊ ጥፋት አንጻር ቀስ በቀስ ሁሉንም የሚያካትት የሰላም ድርድር እንደሚያሳ የሚጠቅሰው ዴቪሰን፣ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የፌዴራልና የህወሓት መሪዎችን እንኳ ወደ ጠረጴዛው ማምጣት ከባድ በመሆኑ ጊዜው አይደለም ይላል።
ኤርትራ በዚህ ጦርነት ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ሠራዊቱ ወደ ትግራይ መግባቱን የተለያዩ ሪፖርቶች ሲቀርቡ መቆየቱ ይታወሳል።
ምንም እንኳ አሁን በህወሓትና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ያለው ጦርነት ቢቀዛቀዝም አልፎ አልፎ በትግራይ ኃይሎች እና በኤርትራ ሠራዊት መካከል የሚነሱ ግጭቶች እንዳሉ ይነገራል።
በመሆኑም ግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ አልፎም ኤርትራ የምታነሳቸው ጥያቄዎች ውይይት እንዲደርግባቸው ከተፈለገ ድርድሩ የኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት ያካተተ መሆን አለበት የሚሉ አሉ።
ነገር ግን ኤርትራ ያላት የድንበር ጥያቄ ትግራይ ክልል የሚመለከት ሳይሆን የኢትዮጵያን ፌደራላዊ መንግሥትን የሚመለከት ነው የሚሉት የሕግ ምሁሩ ኤልያስ ናቸው።
“ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ጉዳይ በውጭ ጉዳይና በዓለም አቀፍ ሕግ የሚፈታ ነው። ኤርትራ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የምትገባበት ምንም ምክንያት የላትም። እስከ አሁን ላደረገችው ጣልቃ ገብነት በሕግ ልትከሰስ የምትችል አገር ናት።”
ላለፉት አስር ዓመታት በሶማሊያ ግጭት አፈታት ዙሪያ ተሳትፎ የነበራቸው የሕግ ባለሙያው ሙሴ ኤፍሬም፣ ኤርትራን ወደ ጎን መተው የሚፈለገውን ሰላም ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት ነው ባይ ናቸው።
“ኤርትራን ያላካተተ ድርድር ቢጀመር ኤርትራ የሆነ ኃይል ተጠቅማ ሰላሙን ልትመርዘው ትችላለች። በሶማሊያ ያየነው ይህን ነው። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሁሉንም የሶማልያ ኃይሎች እንዲወያዩ ባለማድረጉ ምክንያት ችግሩን እስከ አሁን መፍታት አልተቻለም። ስለዚህ ወደ ኋላ የሚቀር ኃይል መኖር የለበትም፤ኋላ ላይ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ የሚመለከት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚሳተፉበት ንግግር መደረግ አለበት።”
አክለውም “ኤርትራ ደግሞ በጦር ወንጀል ከሚከሰሱ መካከል ስለሆነች፣ ድርድሩ ላይ አለማሳተፍ ሂደቱ ያዘገየዋል፤ስኬታማ አያደርገውም። ይህ በሶማልያ፣በሱዳን፣በደቡብ ሱዳን አይተነዋል” ይላሉ ሙሴ።

ሌሎች በድርድሩ መሳተፍ አለብን የሚሉ ኃይሎች
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ለዘለቀው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ይሆናል የሚል ተስፋ አለን ይላሉ።
ይሁን እንጂ የድርድሩ ሂደት የተያዘበት መንገድ ላይ ጥያቄ አላቸው።
እነዚህ ብሔራዊ ባይቶና ዓባይ ትግራይ፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትራይ ነጻነት ፓርቲ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድሩ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ብቻ መሆኑ ትክክል አይደለም ባይ ናቸው።
ፓርቲዎቹ ባለፈው ሰኔ ወር ባወጡት መግለጫ፤ “ህወሓት የትግራይ ሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት እና ጥቅም ስለማያስከብር በትግራይ ሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ዙሪያ የመደራደር ሕጋዊ ሥልጣን ስለሌለው፣ አልፎም የትግራይ ሕዝብ ለህልውናው እየታገለ ስለሆነ ድርድሩ ላይ በሰፊ የተወካዮቹ ቅንጅት መወከል አለበት” ብለዋል።
የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህወሓትን እንደ ብቸኛ ወኪል መውሰድ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ሲሉ ይሞግታሉ።
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ኃይሉ ከበደ፤ ፓርቲዎቹ ድርድሩ ላይ መካተት አለብን የሚሉበት ምክንያት በትግራይ እየተካሄደ ያለው ትግል “የሕዝብ ትግል ነው ብሎ ከማመን የሚመነጭ ነው” ይላሉ።
“በህወሓት ላይ እምነት የለንም፤ ምክንያቱም የህወሓት ኃይል ያለው የድርድር ታሪክ ደካማ እና ሁሌም ተሸንፎ የሚመጣ ኃይል ነው።”
ኃላፊው አክለውም “ድርድሩ ትግራይን ወደ ነበረችበት ሁኔታ የመመለስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የትግራይ ሕዝብ ዕጣ-ፈንታ የሚወስን ስለሆነ ይህ ጉዳይ ለአንድ ኃይል የሚተው አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ሆኖም በመጀመሪያው ዙር የሰላም ድርድር የሚጨበጥ ውጤት እንደማይጠበቅ ያነጋገርናቸው ሰዎች ያስረዳሉ።
በተደራዳሪዎቹ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑ፤ ፖለቲካውና ጦርነቱ ያስከተለው መቃቃር እንዲሁም በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች የፈፀሟቸው ወንጀሎችን የሚመለከቱ ክርክሮች ስለሚጠበቁ ድርድሩ ጊዜ የሚወስድ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ዴቪሰን፤ “አሁን አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ቁርጠኛ መሆናቸውን ቢገልፁም፤ ለራሳቸው የሚጠቅማቸው ቅደመ ሁኔታ ካልሆነ በቀር ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ነው” ይላል።