
23 ነሐሴ 2022, 08:25 EAT
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠበቆች የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ላይ ክስ መሠረቱ፡፡
ክሱን የመሠረቱት የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) አላግባብ በዶናልድ ትራምፕ ቤት ላይ ፍተሻ አድርጎ ሰነዶችን በጉልበት ወስዷል በሚል ነው፡፡
ፍሎሪዳ የሚገኘው የትራምፕ ቅንጡው ማራ ላ ጎ መኖርያ ቤት በፖሊስ ድንገተኛ ወረራ እና ብርበራ የተደረገበት በቅርቡ ነበር፡፡
ብርበራውን ተከትሎ በአሜሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ ክርክር ትኩሳት ተቀስቅሷል፡፡ በዲሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች መካከልም ለተጋጋለ ፖለቲካዊ ሙግት በር ከፍቷል፡፡
ይህን የፖሊስ ብርበራ ተከትሎ የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ የአገር ምሥጢር የነበሩና ትራምፕ መኖርያ ቤት መቀመጥ ያልነበረባቸው የተባሉ ጥብቅ ሰነዶችን ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ወትሮ በእንዲህ ያለ ጊዜ የምርመራ ቢሮ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ ካገኘ በኋላ በብርበራ ስለተገኙ ሰነዶች ምንነት ምርመራ ሳይጠናቀቅ ይፋ አያደርግም፡፡
ሆኖምበፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ላይ የደረሰውን ሕዝባዊ ትችት ለማርገብ የዚህ መሥሪያ ቤት አለቃ በብርበራው የተገኙ ሰነዶችን ይዘት በደምሳሳው ምን እንደሆኑ ፍንጭ ለመስጠት ተገደው ነበር፡፡
ብርበራው የተካሄደውም ሕጋዊ የፍርድ ቤት ማዘዣን በመያዝ እንደሆነም ለአሜሪካ ሕዝብ አስረድተዋል፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎች ግን ይህ ብርበራ የትራምፕን ፖለቲካዊ ቁመና ለመጉዳት የታለመ ነው ይሉታል፡፡ በዲሞክራቶች የተጎነጎነ ፖለቲካዊ ሴራ እንደሆነም ያምናሉ፡፡
የትራምፕ ጠበቆች አሁን ዳኞችን እየጠየቁ ያሉት ‘ያልተገባና ሕግን ያልተከተለ’ ያሉትን የፍትሕ ቢሮ ምርመራ እንዲያስቆሙላቸው ነው ፡፡
- ውጤቱ ቀስ በቀስ እየታየ ያለው የአጎዋ ተጽእኖ23 ነሐሴ 2022
- አዲሱ ‘የማኅበራዊ ልማት ግብር’ ኑሮን ሊያስወድድብን ይሆን?22 ነሐሴ 2022
- የፑቲን አጋር የሆኑት ግለሰብ ልጅ የተገደለችው በዩክሬን እንደሆነ ሩሲያ ከሰሰች22 ነሐሴ 2022
ትራምፕ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የአገር ምሥጢርን በእንዝህላልነት በግል በመያዝ ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል፡፡
አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ከለቀቀ በኋላ እንዲህ ያሉ ከፍ ያሉ የአገር ምሥጢር የያዙ ሰነዶችን ማስረከብ ያለበት ለብሔራዊ መዛግብት ቢሮ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ ትራምፕ እነዚህ ጥቂቶች ብቻ ማየት የሚፈቀድላቸውን ሰነዶች ከነጩ ቤተ መንግሥት ወደ ፍሎሪዳ መኖርያ ቤታቸው መውሰዳቸው ከተረጋገጠ እስር ሊጠብቃቸው ይችላል፡፡
ሆኖም ትራምፕ እነዚህ ሰነዶች ከጥብቅ ምሥጢራዊ ሰነድነት የወጡ ናቸው ብለው ይከራከራሉ፡፡
አሁን የትራምፕ ጠበቆች ለፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የ27 ገጽ ክስ፣ የአሜሪካ ምርመራ ቢሮ ትራምፕ ወደፊት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት በድጋሚ እንዳይወዳደሩ ለማድረግ የሸረበው ሴራ ስለሆነ ሰነዶቹን አሁኑኑ ይመልስ፣ ምርመራውን ዛሬ ነገ ሳይል ያቁምልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከትራምፕ ጠበቆች አንዱ ደግሞ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ሦስተኛ ገለልተኛ አካል ተመድቦ ነገሩን ያጣራ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የፍትሕ ቢሮ ለዚህ ክስ በሰጠው አጭር ምላሽ አቃቢ ሕግ በትራምፕ ላይ እየተደረገ ያለውን ምርመራ እንዲያውቅና በፍርድ ቤት ተገቢውን ምላሸ እንደሚሰጥ ተቁሟል፡፡
የፍትሕ ቢሮ ቃል አቀባይ አንተኒ ኮሊ እንዳሉት የማሮላጎ ብርበራን በተመለከተ ፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ ካተመ በኋላ የተደረገ ሕጋዊ መስመርን የተከተለ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የምርመራ ቢሮው ከትራምፕ የፍሎሪዳ ቤታቸው የወሰዳቸውን 300 ሰነዶች እየመረመረ እንደሆነ ዘግቦ ነበር፡፡
እነዚህ ሰነዶች ደግሞ ከብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ፣ ከሲአይኤ የስለላ ቢሮ እና ከብሔራዊ የምርመራ ቢሮ ጋር የተገናኙና ከፍ ያለ የአገር ምሥጢራትን የያዙ እንደሆኑ አመላክቷል፡፡
በትራምፕመኖርያ ቤት ብርበራው እንዲደረግ ለምርመራ ቢሮ ፈቃድ ያተሙት ዳኛ በምን አግባብ ይህን ሊፈቅዱ እንደቻሉ ይፋ የተደረገ ነገር የለም፡፡
አንድ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በእንዲህ ዓይነት መልኩ በመኖርያ ቤቱ በወንጀል ተጠርጥሮ ብርበራ ሲካሄድበት ዶናልድ ትራምፕ በታሪክ የመጀመርያው ናቸው፡፡
ትራምፕበፈረንጆቹ 2024 ዓ/ም ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን ይሻሉ፡፡
