August 24, 2022

በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነው ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክለት ጠየቀ። ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ በምክር ቤቱ የተላለፈው ውሳኔን በተመለከተ ደግሞ፤ የህዝበ ውሳኔ መርኃ ግብር የማዘጋጀት ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ በዚሁ አግባብ የጊዜ ሰሌዳውን ወደ ፊት እንደሚገልጽ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 17 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ቦርዱ በዚሁ ደብዳቤው፤ በደቡብ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የጋራ ክልል መመስረትን በተመለከተ በየምክር ቤቶቻቸው ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ህዝበ ውሳኔ ለማደራጀት ለቦርዱ በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሷል።
Thread

በደቡብ ክልል የሚገኙት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ የደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች
አዲስ በሚቋቋም ክልል በአንድ ላይ ለመደራጀት በምክር ቤቶቻቸው
ውሳኔዎችን አሳለፉ። የአማሮ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎችም በምክር ቤቶቻቸው
ተመሳሳይ ውሳኔ አጽድቀዋል።
Translate Tweet
In the southern region, the zones of Wolaita, Gedo,
Gamo, South Omo and Konso passed resolutions in
their councils to organize together in a newly
established region. The special districts of Amaro and
Basketo also approved the same decision in their
councils.
7:21 AM · Jul 30, 2022 ·Twitter Web App
13 Retweets 4 Quote Tweets 50 Likes
ዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎቹ ይህንኑ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር አያይዘው የሏኳቸው ሰነዶችም ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ለሚደረገው ዝግጅት የሚያስፈልጉ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አመልክቷል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡለትን ጥያቄዎች እና ተያያዥ ሰነዶች ለቦርዱ እንዲልክ በደብዳቤው ተጠይቋል።
በደቡብ ክልል የሚገኙት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን እንዲሁም የደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች፤ በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡት ከ20 ቀናት በፊት ሐምሌ 28፤ 2014 ነበር። ዞኖቹ እና ወረዳዎቹ የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን ይህን ውሳኔ በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት ሐምሌ 23 እና 24፤ 2014 ባካሄዷቸው ስብሰባዎች ናቸው።
ምርጫ ቦርድ በዚሁ ደብዳቤ ያነሳው ሌላው ጉዳይ ህዝበ ውሳኔው የሚደረግበትን የጊዜ ማዕቀፍ በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ያሳለፈው ውሳኔ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 12፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ መወሰኑ ይታወሳል።
Tweet

የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ክልል የሚመሰርት
ህዝብ ውሳኔ እንዲካሄድ ወሰነ። ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 12 ባካሄደው
አስቸኳይ ጉባኤ፤ ምርጫ ቦርድ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ህዝብ ውሳኔ
እንዲያደራጅም ውሳኔ አሳልፏል። #Ethiopia
Translate Tweet
5:01 AM · Aug 18, 2022·Twitter Web App
10 Retweets 3 Quote Tweets 29 Likes
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ “ቀን ቆጥሮ” የሰጠበትን አካሄድ፤ ቦርዱ “አግባብነት ካላቸው የህግ ማዕቀፎች አንጻር” በጥልቀት መመርመሩን በደብዳቤው አስታውቋል። በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ምርጫዎች እና ህዝበ ውሳኔዎች የሚካሄዱበትን የመርኃ ግብር ሰሌዳ የማውጣት ስልጣን “የተቋሙ ብቻ መሆኑን” ቦርዱ በአጽንኦት ገልጿል።
“ቦርዱ የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም ከተቋማዊ እና መዋቅራዊ ነጻነት በተጨማሪ በህግ ተለይተው የተሰጡትን ስልጣን እና ኃላፊነቶች በተመለከተ የሚኖረው የውሳኔ እና የስራ አፈጻጸም ነጻነት ሁሌም መከበር ይኖርበታል” ሲልም ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው አሳስቧል።
ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 የወጣው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የቦርዱን ስልጣን እና ተግባር በሚዘረዝረው ክፍል፤ “በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎች መርኃ ግብር ሰሌዳ እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ ማጽደቅ እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻልና መፈጸሙን መከታታል” የቦርዱ ስልጣን እና ተግባር መሆኑን ይደነግጋል። በዚሁ መሰረት ቦርዱ ለህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ሰሌዳ አውጥቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚገልጽ በደብዳቤው አስታውቋል።
“ቦርዱ የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም ከተቋማዊ እና መዋቅራዊ ነጻነት በተጨማሪ በህግ ተለይተው የተሰጡትን ስልጣን እና ኃላፊነቶች በተመለከተ የሚኖረው የውሳኔ እና የስራ አፈጻጸም ነጻነት ሁሌም መከበር ይኖርበታል”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከጻፈው ደብዳቤ የተወሰደ
የጊዜ ሰሌዳው የሎጂስቲክስ ዝግጅት ለማድረግ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመልመል እና ለመመደብ፣ ምርጫ ጣቢያዎች ለማደራጀት እና ለታዛቢዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ይሆናል ብሏል ቦርዱ። ምርጫ ቦርድ በዚሁ ደብዳቤው በህዝበ ውሳኔ ላይ የሚያገባቸውን ባለድርሻ አካላት የማወያየት እቅድ እንዳለው ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)