ፖለቲካ ዜና

ሲሳይ ሳህሉ

August 24, 2022

ሕወሓት ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ የትግራይ ሕዝብ ግፊት ሊያደርግ እንደሚገባ፣ የብልፅግና ፓርቲ ማዕካላዊ ኮሚቴ አባልና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕካል አስተባባሪ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የተቋረጠውን ግንኙነት ለማስቀጠል፣ የፌደራል መንግሥቱን ከሕወሓት ጋር ለማደራደር እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ሁለቱ ተደራዳሪዎች በሚያደርጓቸው የቃላት ምልልሶች የታሰበው ፖለቲካዊ ድርድር ላይ ደመና አጥልቶበታል፡፡

ዓለሙ (ዶ/ር)  ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሕወሓት በኩል እየተሰማ ያለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማና ዝግጅት በመሆኑ ለድርድሩ ቁርጠኛ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በዚህም የተነሳ ሕወሓት በፌደራል መንግሥቱ ልክ ለድርድሩ እየተዘጋጀ ነው ለማለት ጥርጣሬ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሕወሓት በኩል ሁልጊዜ የሚሰማው ጉዳይ ተስፋ ያለው አይደለም፣ እኛ ግን ሰላምን ለማምጣት እንሠራለን፣ ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ ግፊት መጨመር አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ድርድሩን ለማስጀመር ከሕወሓት የሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎችን አስመልክተው፣ ‹‹ለሰላም ድርድር ምንም ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም፣ የምንደራደረውና ወደ ውይይት የምንገባው የትግራይ ሕዝብ እነዚህ የሚጠየቁ የመሠረተ ልማቶችን እንዲያገኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ ስልክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ባንክና ሌሎች የተቋረጡበትን አገልግሎቶች እንዴት ያገኛል የሚለውን ጉዳይ ነው እንነጋገር ያልነው፡፡ ነገር ግን ይህንን አልቀበልም ያለው ሕወሓት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የመንግሥት አገልግሎትን ስትሰጥ አገልግሎቱ ሕዝቡ ዘንድ በትክክል መድረሱን መንግሥት ማወቅ አለበት፣ ሳትነጋገር እንዴት ይህ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

 ‹‹በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የሉም፣ ባንክ ለመክፈት ደግሞ አለመዘረፉን ማረጋገጥና የራሱ የፀጥታ አካል መኖር አለበት፡፡ ስለዚህ ዝም ብለህ ብር አታመጣም፣ የባንክ ብር የሕዝብ ነው፣ መብራትና ቴሌኮም ሥራ ለማስጀመርም ቢል መሰብሰብ አለበት፤›› በማለት አክለዋል፡፡

 ይህ የሚጠየቀው አገልግሎት ወደ ሕዝቡ መድረሱንና እንዴት ብሎ መቅረብ አንዳለበት፣ የመብራትና የስልክ ሠራተኞች እንዴት ተንቀሳቅሰው መሥራት ይችላሉ የሚለውን መነጋገር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

 ይሁን እንጂ ንግግር ሳይኖር አቅርቡልኝ ማለት ‹‹ሳታመሀኝ ብላ›› ማለት እንደሆነ፣ ምክንያቱ ደግሞ ለሰላም ዝግጁ ስላልሆኑ እንደሆነና ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› ዓይነት ሰበብ መፈለግ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹እኛ ይህን ለማድረግ እንነጋገር እያልን ነው፣ የፌደራል መንግሥት ወደ ድርድር እንምጣ፣ ዘላቂ ሰላም እናምጣ ሲል፣ የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ምሽግነት ያጣውን ሰላም እንዲያገኝ እናድርግ እያለ ቢሆንም፣ ችግሩ እንዳይፈታ ያደረገው ሕወሓት ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የፌዴራል መንግሥቱ የጀመረው የሰላም ድርድር ለሁሉም ኃይሎች በሁሉም አካባቢ ላሉና አሻፈረኝ ላሉ አካላትም እንደሚሠራ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ የኦነግ ሸኔን ልዩ የሚያደርገው በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ የተማከለ መሪ ካላቸው የሰላማዊ ድርድር መርሁ ሰሜን ብቻ የሚሠራ እዚህ የማይሠራ ባለመሆኑ፣ ለጉሙዙ፣ ኦሮሞው፣ በየትኛውም አካባቢ ላለው ሰላም ፈላጊ ሁሉ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የቅድሚያ ጉዳይ እንጂ ማንም ስለሰላም ለመወያየት ከመጣ እኛ ዝግጁ ነን፡፡ ለመወያየት ከዚህ ከዚያ ብለን የምንመርጠው የለም፡፡ ነገር ግን ኦነግ ሸኔ ባለቤት አለው ወይም በአንድ ዕዝ የሚመራ ነው የሚለውን አናውቅም፣ ከዚያ በኩልም የቀረበ ጥያቄ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት አካታች ውይይት ስለሚፈልግና ዘላቂ መፍትሔ ስለሚሻ፣ ማንኛውም አካል ጠመንጃውን አስቀምጦ ከመጣ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ወደ ድርድር ሲመጣ የአሸባሪነት ስያሜው እንዴት ይነሳል በሚለው ላይ ውይይት እንደሚደረግበትም አስረድተዋል፡፡