September 1, 2022 – Abebe Bersamo 

ነሐሴ 18 ቀን ሕወሃቶች ለሶስተኛ ጊዜ የከፈቱት ጦርነት አድማሱን አስፍቶ ፣ ከፍተኛ የዜጎች ሕይወት መቀጠፍንና ጥፋት እያስከተለ ነው፡፡ በራያ በኩል በስሜን ወሎ በሶስት አቅጣጫ የተጀመረው ውጊያ ቀጥሎ ውሏል፡፡ በአፋር ክልል ዞን 4፣ በሰሜን ሸዋ ቆቦና ጊዳን ወረዳዎች ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡

ላለፉት ሁለት ቀናት ደግሞ በወልቃይት መስመር፣ በሱዳን በኩል፣ በማይጠምሪ/አደርቃይ መስመር፣ በተንቤን/አበርገሌ/ሰቆጣ መስመር፣ ከኤርትራ ጋር በሽራሮና በራማ መስመር ውጊያዎች ተቀስቅሰዋል፡፡

ጀነራል ጻድቃን የቀድሞ የኢትዮጵያ የኤታ ማጆር ሹም የነበረ ሰው ነው፡፡ ሌተና ጀነራል መዓረግነት ያለው፡፡ በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሊተሪ ጠበብት ተብሎ በአማካሪነት ሲያገለግል የነበረ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደውም አንድ ዘገባ ሰርቶ። “The commander of Tigrayan rebel forces, Gen Tsadkan Gebretensae, is regarded by international security analysts as one of the finest military strategists of his generation in Africa.” ብሎ ነው ያወደሰው፡፡ የወጣነት ጊዜውን በጦርነት ያሳለፈ፣ የጦርነትን አስከፊነት የሚያውቅ ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ጀነራል ታደሰ ወረደም (ወዲ ወረደ) በኢትዮጵያ መከላከያ ውስጥ ላይ ከደረሱ የጦር አዛዦች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እርሱም ሌተና ጀነራል የነበረ ሲሆን፣ በደቡብ ሱዳን በአብዬ፣ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጦር ዋና አዛዥ ሆነ የሰራ ሰው ነው፡፡ በወቅቱ በሱዳን በሰራው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብላ እንድተጠራ ያደረገ፡፡

አንድ በሳል፣ አስተዋይ ጀነራል ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት መስራት ያለባቸው የቤት ስራዎች አሉ፡፡ ከሁለት ሺህ አመት በፊት የነበረው ታዋቂው የቻይና ሚሊተሪ ስትራቲጂስት ዙጌ ሊያን፡ “አዋቂ ከመዋጋቱ በፊት ያሸንፋል፣ አላዋቂው ደግሞ ለማሸነፍ ይዋጋል” ነበር ያለው፡፡ ዙጌ ሊያን ይሄን ሲል፣ ዉጊያ ከመረዱጉ በፊት የተሰራው ስራ ነው የጦርነትን ሁኔታ የሚወስነው ለማለት ፈልጎ ይመስለኛል፡፡

አንድ አስተዋይ ጀነራል ወደ ጦርነት ከመግባቱ በፊት ፡

  1. ለምን እንደሚዋጋ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ በዉጉያ ለማሳካት የፈለጋቸው ግቦች፣ አንድ ሁለት ተብለው በትክክል መቀመጥ መቻል አለባቸው፡፡
  2. ማንን እንደሚዋጋ ጠንቅቆ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሚዋጋዉን ኃይል አቅምና ጉልበት ማጥናት አለበት፡፡
  3. በውጊያው ወቅት ለተዋጊዎቹ የሚያስፈልገውን ስንቅና ትጥቅ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ስንቅና ትጥቅ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ስንቅና ትጥቅ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማመላለስ በቂ ኮሪዶሮች ሊኖሩት ይገባል፡፡
  4. የተዋጊዎቹ የመዋጋት ስሜት ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ አለበት፡፡ ተስፋ የቆረጠ፣ ተገዶ የመጣ፣ የመዋጋት ፍላጎት የሌለው ሰራዊትን ተማምኖ ወደ ዉጊያ አይገባም፡፡
  5. ኃይሉን በተለያየ ቦታ አይበታትንም፡፡ በተቻለ መጠን ጠላት አያበዛም፡፡ ከሁሉም ጋር ለመዋጋት አይንቀሳቀስም፡፡
  6. ከሁሉም በላይ ደግሞ ለማሳካት ያስቀመጣቸውን ግቦች ማሳካት እችላለሁ ወይ ብሎ በትክክል ገምግሞ፣ ማሳካት የማይችል ከሆነ ወደ ዉጊያ አይገባም፡፡
  7. አንዴ ስህተት ከተሰራ፣ ሽንፈት ካጋጠመ፣ የተለየ፣ ከሳጥን ውጭ( out of the box) የሆነ አዲስ ስትራቲጂ ይዞ ይመጣል እንጂ፣ ያንኑ ስህተት አይደግሞ፡፡ ሽንፈት ያከናነበውን ስትርቲጂ መልሶ አይጠቀምም፡፡

እነ እጀነራል ጻድቃን ከላይ በተቀመጡት ሰባት መስፈርቶች መሰረት ሲመዘኑ F ነው የሚሰጣቸው፡፡ መስፈርቶቹን በሙሉ ወድቀዋል፡፡

የሕወሃት የጦር አዛዦች ለሶስተኛ ዙር ጦርነት ሲከፍቱ ለምን እንደሚዋጉ እንኳን በትክክል አላስቀመጡም፡፡ ያኔ የጅቡቲን መስመር ለመዝጋት፣ አብይ አህመድን ለማስወገድ የሚል አላማ ነበራቸው፡፡ አሁን ኝ ለምን እንደሚዋጉ እንኳን ግልጽ አይደሉም፡፡  እነርሱ ለሰባት ወራት ሲሰለጥኑ በዚያኛውም ወገን ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ያለ ነው የመሰላቸው፡፡ ሊመክታቸው የተዘጋጀውን ኃይል ጥንካሬ በደንብ አልተገነዘቡም፡፡ የጦርነት አድማሳቸውን አስፍተዉት በብዙ ቦታ እየተወጠሩ ነው፡፡ ተዋጊዎቻቸው ከቤተሰብ አንድ በሚል ተገደው ስለመጡ የመዋጋት ሞራላቸው እንደበፊቱ አይደለም፡፡ በአየር ኃይል ምክንያት፣ ወረራ ለፈጸሙ ተዋጊዎቻቸው ስንቅና ትጥቅ ለማቀበል፣ ተጨማሪ ኃይል ለማሰመራት አስቸጋሪ ነው የሆነባቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ልክ ያለፈው አመት የተጠቀሙበት ታክቲክ ነው የተጠቀሙት፡፡ ብዙ ወታደር፣ ማእበል በመላክ ቦታዎችን መቆጣጠር፡፡ በፊት በሄዱበት መስመር ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ያለፈውን አመት ነው ለመድገም የሞከሩት፡፡ አዲስ ነገር፣ አዲስ ስትራቲጂ አላመጡም፡፡ በአጭሩ እንደሚሸነፉ እየወቁ  ነው ውጊያ የከፈቱት፡፡

የማናሸንፈው ውጊያ መክፈት ደግሞ እብደትና ድንቁርና ነው፡፡ ህዝብን ማስጨረስ ነው፡፡ እነ ጀነራል ጻድቃንና ጀነራል ታደሰ ወረደ እያደረጉት ያለው ይሄንኑ ነው፡፡

ሁልጊዜ እንደምለው አሁንም እላለሁ፡፡ ሕወሃቶች በጦርነት ማሸነፍ አይችሉም፡፡ እስከ አሁንም የቆዩት በአራት ኪሎ ባለው እጅግ በጣም ደካማና ወላዋያ፣ የማይታመን የፖለቲካ አመራር ምክንያት እንጂ ገና ድሮ ተሸንፈው ታሪክ ይሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህ እንደማይሸንፉ አውቀው በአስቸኳይ ወረው ከያዟቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ለቀው ይውጡ፡፡

ወልቃይትን በኃይል እንይዛለን የሚለው ቅዠታቸውን ያቁሙ፡፡ ተሳክቶላቸው ወልቃይትን ቢይዙም እንኳን በዚያ በሰላም መኖር አይችሉም፡፡ ችግር ውስጥ እየከተታቸው ያለውን ፣ “እኛ ተዋጊ ነን፣ እኛን የሚችለን የለም” የሚለው የጀብደኝነት፣ የእብሪት ክፉ መንፈስን ከውስጣቸው ያስወግዱ፡፡ እነርሱም እንደሚተኩሱት፣ ሌላውም ይተኩሳል፡፡ እነርሱም ለመግደል ሲመጡ፣ ሌላውም መግደል ይችላል፡፡ ይሄን አይዘንጉት፡፡

አዎን ወልቃይት፣ ራያና ጠለምት አወዛጋቢ መሬቶች ናቸው፡፡ አወዛጋቢም የሆኑት ሕወሃት ራሱ ካመጣው የዘር ፖለቲካ የተነሳ ነው፡፡ ምነው ከሕወሃት በፎት ለምን አላወዛገቡም ? ትግሬው፣ አምራዉን ሁኡም  በሰላም ይኖር አለነበረም እንዴ ? ትግሪኛ፣ አማርኛ እየቀያየሩ እየተናገሩ፣ ሲፈለጉ ሽሬ፣ ሲፈለጉ ጎንደር እየሄዱ እየሸመቱና እየነገዱ ፡፡  አሁን ያለው ችግር የመጣው፣ የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት ፣ የኦሮሞ መሬት ከሚለው የበሰበሰ የዘር አወቃቀር ነው፡፡ ያ ባይኖር ኖሮ “ወልቃይት የትግሬ ነው፣ ወልቃይት የአማራ እርስት ነው” የሚል ውዝግብ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡

አሁን በሕገ መንግስቱ መሰረት፣ ትግሬው ከትግራይ ውጭ ያለው አገሩ አይደለም፡፡ አማራው ከአማራ ክልል ውጭ ያለው አገሩ አይደለም፡፡ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ የመባባል ፖለቲካ ሲቀር፣ ዘር ከመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሲወጣ፣ የጎሳ ህገ መንስት ሲቀየር፣  ያኔ የነ ወልቃይት ውዝግብ፣ ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ ይፈታል፡፡ ትግሬው ወልቃይት ብቻ ሳይሆን ጎንደርም፣ ደሴም አገሩ ይሆናል፡፡ አማራውም መቀሌም፣ አዲግራትም አገሩ ይሆናል፡፡ ያኔ ከደም መፋሰስ ይልቅ በፍቅር አገራችንን የምናሳድግበት አዲስ እድል ይከፈትልናል፡፡

(በነገራችን ላይ ስለ ጀነራሎች ሳነሳ ፣ የቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ፣ ጀነራል አበበ ተከለ ኃይማኖት፣ በአንድ ስብሰባ ላይ፣ የትግራይ ሕዝብ ጥቅም የሚጠበቀው ከአማራው ጋር መስማማት ሲቻል ነው፡፡ የወልቃይት ጥያቄያችንን አንስተን ከአማራው ጋር እንተባበር” ብሎ እንደነበረ ሰመቼ ነበር፡፡ ያኔ ወልቃይት በሕወሃት ስር ነበረች፡፡ ጦርነቱ አልተከፈተም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ከሁሉም አቅጣጫ ነበር ውርዥብኝ የተነሳበት፡፡ ጀነራሉን ያኔ ቢሰሙት ይሄ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር)