
FDRE Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር
ሀሰተኛ ሰነድ መፍጠር፤ መገልገል እና የወንጀል ተጠያቂነት
መግቢያ
ሰዎች በተለያየ መንገድ የተለያዩ ወንጀሎችን ይሰራሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በስፋት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል ሀሰተኛ ሰነድ መፍጠር፡ ሰነዶችን ወደሀሰት መቀየር፡ ሰነዶችን ማጥፋትና በሀሰተኛ ሰነዶች መገልገል ሲሆኑ በሀገርም ሆነ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ ወንጀል አሁን ባለው የቴክኖሎጂ እድገት አማካኝነት በረቀቀ መንገድ እየተፈጸመ ቢሆንም ማህበረሰቡ በሰነድ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምን እንደሆኑና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት ምን እንደሆነ ግንዛቤ ቢያገኝ ወንጀሉን ለመከላከል እንዲችልና የወንጀል ድርጊቱን ከመፈጸም እንዲቆጠብ የሚያደርግ ስለሆነ ይህ አጭር ጽሁፍ ሊቀርብ ችልዋል፡፡
ሀሰተኛ ሰነድ መፍጠርና መገልገል
አንድ ሰው ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲል ወይም የሌላን ሰው መብት ለመጉዳት በማሰብ ሀሰተኛ ሰነድ ሊፈጥር፤ ሰነዶችን ወደ ሀሰተኛ ሰነድ ሊለውጥ ወይም ሰነድ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባር መፈጸምም ሆነ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የወንጀል ድርጊት መሆኑን በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ዓ.ም ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በወንጅል ህጉ አንቀጽ 375 እንደተደነገገው ማንም ሰው የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማሰገኘት በማሰብ፡
ህጋዊ ክርክሮች ሲካሄዱ በማስረጃነት የሚቀርቡ፤ አንድን ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ወይም የሚያረጋግጡ የሚመስሉ እንደ ጽሁፍ፤ ሌሎች ሰነዶች ግዙፍ ነገሮች የመሳሰሉትን መፍጠር፡
ሀሰተኛ ሰነድ ለማዘጋጀት በሌላ ሰው የጣት ፊርማ ፤ ፊርማ፤ ምልክት ወይም ማህተም መጠቀም፡
እውነተኛውን ጽሁፍ በመለወጥ ወይም በመደለዝ በሀሰተኛ ፊርማ፤ ማህተም ወይም የሌለውን ስልጣን ወይም ችሎታ እነዳለው አስመስሎ በመፈረም ሀሰተኛ ሰነድ መፍጠር፡
አንድን ሰነድ፤ በተለይም የፈራሚውን ስም ወይም ፊርማ ወይም የሰነዱን ይዘት፤ አሀዝ፤ ፍሬ ነገር ወይም ዝርዝር መግለጫ በሙሉ ወይም በከፊል በመለወጥ፤ በማሻሻል፤ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም በማጥፋት፤ ወደሐሰተኛነት መለወጥ የወንጀል ድርጊት ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ድርጊቶች በጠቅላላው በሰነዶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲሆኑ በረቀቀ መንገድና በልዩ ሁኔታ ሀሰተኛ ሰነድ በመፍጠር የሚፈጸሙ ወንጀሎች ያሉ ሲሆን እነዚህ የወንጀል ተግባራትም፤ የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፡-
አንድ ሰነድ በሚዘጋጅበት ጊዜ ህጋዊ ውጤት ያለውን ወይም ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውንም ሀሰተኛ ፍሬ ነገር ማስገባት ወይም እንዲገባ ማድረግ
የአንድን ሰነድ ይዘት በተመለከተ በማሳሳት ሌላ ሰው ሌላ ሰነድ ወይም የተለየ ይዘት ያለው ሰነድ ላይ የፈረመ መስሎት እንዲሳሳት ማድረግ
ፍቃዱ ባልሆነ ወይም በሌለ ሰው ስም ሰነድ መስጠት ሲሆኑ
እነዚህ ተግባራት የወንጀል ድርጊት መሆናቸውን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 376 እና 377 ላይ ተደንግገው ይገኛሉ። ከላይ የተዘረዘሩትን የወንጀል ተግባራት በመፈጸም ሀሰተኛ ሰነድ የፈጠረ በተፈጠረው ሀሰተኛ ሰነድ የተገለገለ ማንኛውም ሰው ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ ማለትም ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እስራቱ ከአስር አመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት ይሆናል።
መንግስታዊ ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወደ ሀሰት መለወጥ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል
ሌላው ሀሰተኛ ሰነድ የሚፈጠረው በመንግስትና በህዝባዊ ድርጅት ሰነዶች ላይ ሲሆን በእነዚህ ተቋማት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል ከፍ ያለ ጉዳት በመንግስትና ህዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርስ በመሆኑና አላግባብ መበልጸግን የሚያመጣ ስለሆነ በልዩ ህግ እንዲገዛ ተደርጓል። በዚህም መሰረት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 ዓ.ም አንቀጽ 23 እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማንኛውንም መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፡-
አንድን ጽሁፍ፤ መዝገብ ወይም ማንኛውንም ሰነድ የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት በማስመሰል ማዘጋጀት ወይም መፍጠር
በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅት መዝገብ፤ ጽሁፍ ወይም ሰነድ የሰፈረን እውነተኛውን ጽሁፍ በመለወጥ ወይም በመደለዝ፤ በሀሰተኛ ፊርማ፤ በእጅ በተደረገ ምልክት ወይም በጣት ፊርማ፤ በማህተም ወይም የሌላውን ስልጣን ወይም ችሎታ እንዳለው አስመስሎ በመፈረም ሀሰተኛ ሰነድ መፍጠር
አንድን የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነድ በተለይም የፈራሚውን ስም ወይም ፊርማ ወይም የሰነዱን ይዘት፤ አሀዝ፡ ፍሬ ነገር ወይም ዝርዝር መግለጫ በሙሉ ወይም በከፊል በመለወጥ፤ በማሻሻል፤ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም በማጥፋት ወደ ሀሰተኛነት መለወጥ ወይም ማናቸውንም ሀሰተኛ ፍሬ ነገር ማስገባት ወይም እንዲገባ ማድረግ።
የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትልና ወንጀሉን ፈጽሞ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ ከሶስት አመት እሰከ አስር አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሶስት ሽህ ብር እስከ ሰላሳ ሽህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊያስቀጣ እንደሚችል በሙስና አዋጁ ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።
ከላይ የተዘረዘሩት የወንጀል ተግባራት የተፈጸሙት ሰነዶችን እንዲያዘጋጅ እንዲመዘግብ እንዲጠብቅ ወይም ቅጅዎችን እንዲሰጥ ሀላፊነት በተሰጠው የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ አንደሆነ ወይም ሰነዱን በመገልገል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም በግለሰብ በመንግስት ወይም በህዝባዊ ድርጅት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉ አፈጻጸም ከባድ ከሆነ ቅጣቱ ከአምስት አመት እስከ ሃያ አመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከአምስት ሽህ ብር እሰከ ሃያ አምስት ሽህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲሆን የወንጀሉ አፈጻጸም በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ ቅጣቱ እስከ እድሜ ልክ እስራት እንደሚሆን በሙስና አዋጁ አንቀት23 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ሌላው ከሰነዶቹ ልዩ ባህሪ አንጻር የብቃት ማረጋገጫ (ምስክር ወረቀቶች) ግላዊ ሁኔታን የሚገልጹ ሰነዶች በተለይም የነዋሪነት መታወቂያ፤ ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃ፤ የልደት ምስክር ወረቀት እና ሌሎች ግላዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ የወንጀል ድርጊት የሚፈጸም ሲሆን፡ በዚህ መሰረትም ማንም ሰው ጥቅምን ወይም መሻሻልን ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፡-
ተገቢ መብት ለማስገኘት የሚችሉ ጽሁፎችን፤ ግላዊ ሁኔታን የሚገልጹ ማስረጃዎችን ወይም ማንኛውንም ጉዳይ የሚመለከቱ ምስክርነት ማረጋገጫ ሰነዶችን ወደ ሀሰተኛነት መለወጥ ወይም አስመስሎ መስራት ወይም እያወቁ ይህን የመሳሰለውን ሰነድ እንዲገለገልበት ለሌላ ሰው መስጠት፡
ወደ ሀሰት የተለወጠን ወይም መስሎ የተሰራውን ሰነድ ወይም ለራስ አገልግሎት ያልታሰበን ወይም እራስን የማይመለከትን ትክክለኛ ሰነድ እያወቁ መገልገልየተከለከለ ተግባርና በወንጀል የሚያስጠይቅ ሲሆን ይህን የወንጀል ድርጊት ፈጽሞ የተገኘ ሰው በቀላል እሰራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል። ይህ ከላይ የተገለጸው ሀሰተኛ ሰነድ የግል ጉዳይን የያዘ ከሆነ ቅጣቱ ከአንድ አመት ያልበለጠ ቀላል እስራት እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 385 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ሀሰተኛ ሰነድ ለተለያየ አላማ በተለያየ መንገድ የሚዘጋጅ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ ሀሰተኛ ሰነድን በመፍጠርና በመገልገል ከፍተኛ የሆነ ወንጀል እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ወንጀሉ በመፈጸሙ ምክንያት በሀገር ላይም ሆነ በግለሰቦች ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ወንጀል በብዛት የሚፈጸመው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከመንግስት ተቋም በሚሰጡ በመታወቂያዎች ላይና በሌሎች የግል ሰነዶች ማስረጃዎች ላይ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግስትም ሆኑ ሌሎች ድርጅቶች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚቀርቡላቸው ሰነዶች ይዘትም ሆነ ቅርፅ በጥንቃቄ በመመርመር አጠራጣሪ ነገሮችን ከሚመለከታቸው አካላት በማረጋገጥ አገልግሎት ሲሰጡ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡም ሆነ ግለሰቦች እንደዚሁ የሚገለገሉባቸው ሰነዶች ህጋዊና ትክክለኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ፣ ውሎችንም ሆነ ሌሎች ህጋዊ ግንኙነቶችን ሲያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የሚስተዋሉ ችግሮች ሲኖሩም ለሚመለከታቸው የህግ አስከባሪ አካላት በመጠቆም ወንጀሉን በጋራ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአቋራጭ ለመበልፀግ ከመሞከር እና ከሚከተለው የህግ ቅጣት ለመጠበቅ ከዚህ መሰል ድርጊት መቆጠብ ይገባል እንላለን፡፡
በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና የተዘጋጀ
Like
Comment
Share
