ፖለቲካ ዜና

ኤልያስ ተገኝ

September 11, 2022

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) መንግሥት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲሁም ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች ፀጥታ በትኩረት በመከታተል አስፈላጊውን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀ፡፡

ጉባዔው በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስተወቀው፣ መንግሥት ማንነት ላይ መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና የደኅንነት ሥጋት አለባቸው የሚባሉ አካባቢዎችን በመለየት እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታዎችን በትኩረት በመከታተል የሰዎች በሕይወትና በሰላም የመኖር፣ ንብረት የማፍራት መብቶች እንዲጠበቁ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብሏል፡፡

በኦሮምያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን አሞሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የሸኔ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ማንነት ላይ መሠረት በማድረግ በርካታ የአካባቢውን ንፁኃን ሰዎች መግደሉንና በርካታ ሰዎችን ማፈኑን በመግለጫው የዳሰሰው ኢሰመጉ፣ ድርጊቱ የተፈጸመውም አካባቢው ላይ የነበረው የፀጥታ ኃይል ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. አካባቢውን ለቆ ወደ ሌላ ግዳጅ ከሄደ በኋላ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ከነሐሴ 23 እስከ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በርካታ ንጹኃን የአካባቢው ተወላጆች መገደላቸውን፣ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም በአጋምሳ ከተማ የነበሩ በርካታ ሰዎች አካባቢውን ለቀው በመሄድ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ኢሰመጉ አካባቢው ላይ ከነበሩ ሰዎች ካሰባሰበው መረጃዎች ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

ኢሰመጉ በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን አሞሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲቋቋሙ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታና ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲደረግ፣ እንዲሁም ደኅንነታቸው ተጠብቆ፣ ንብረት አፍርተው በነፃነት እንዲኖሩ ዋስትና እንዲሰጥና የሚሰጡ ድጋፎችም ለሚያስፈልጋቸውና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት በሰጠ መልኩ እንዲሆን ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

ከዚህም በሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ አንቂዎች ችግሮችን በውይይት የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠርና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተያያዘም ኢሰመጉ ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በተለይም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሕግ የማስከበር ዘመቻ በሚል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሕግ አግባብ ውጭ እየታሰሩ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሦስት የአገሪቱ ክፍሎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በመሆን ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች በዋስ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸውን ተጠርጣሪዎች ከሕግ አግባብ ውጪ ይዘው ያቆዩ እንደነበር ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሶ፣ የክልል መንግሥታት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ከእዚህ መሰል ድርጊት እንዲቆጠቡና ማሻሻያ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ ሲወተውት መቆየቱን ገልጿል፡፡

ኢሰመጉ በተለይም ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲወጡ የወሰነላቸው 14 ሰዎች መግለጫውን እስካወጣበት ጊዜ በእስር ላይ መሆናቸውን ማረጋገጡን ገልጾ፣ በተጨማሪም ሁለት የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ከታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ በኋላ በዋስ እንዲለቀቁ ቢወስንም ዓቃቢ ሕግ በመቃወሙ ዋስትና ተከልክለው ለዘጠኝ ወራት ያለ ምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝና ክስ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ወረደሳ ፖሊስ ጣቢያ ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረው የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮችና አባላት ፍርድ ቤት ነፃ እንዲወጡ ቢወስንም፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንና የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ከሕግ ውጪ መግለጫውን እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ ካሰባሰብኩት መረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን የአካል ነፃነት መብት መንግሥት እንዲያከብርና እንዲያስከብር እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ለፍርድ ቤት ውሳኔ ተገዥ እንዲሆኑ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶ ጉባዔ ጥሪ አቅርቧል፡፡