ፖለቲካ ዜና

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

September 11, 2022

‹‹በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሁሉ በአፅንኦት የምንመክረው ዓብይ ምክር፣ በግጭት ችግሮቻችንን መፍታት በፍፁም አንችልም፣ በመራራቅም ማደግ አንችልም፣ በተለያየን ቁጥር ድህነታችንን ከማስቀጠልና ደካሞች ከመሆን በስተቀር የምናገኘው አንዳች ፋይዳ የለም፤›› ሲሉ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አስታወቁ፡፡

ፓትርያርኩ፣ ‹‹እውነቱ ይህ ከሆነ ከገባንበት ያላስፈላጊ ግጭት በፍጥነት ወጥተን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ወደሚያስችል ወደ ምክክርና ውይይት እንግባ፤›› የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ሰው ጤና፣ ዕውቀትና ሰላም ካለው ሀብታም መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ ‹‹ሰላም ከሌለ ነገሩ ሁሉ ጨለማ ይሆንበታል፡፡ አካላዊና አዕምሯዊ ጤናውም ይደፈርስና ሳያጣ ያጣ ወደመሆን ይቀየራል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ላይ እየተከሰተ ያው ሀቅ ይሄው ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የሰላም ዕጦት በኢትዮጵያ በርከት ላሉ ዓመታት እየተደጋገመ በመከሰቱ፣  ሕዝቡ ሳያጣ ያጣ መሆኑንና ኢትዮጵያን በመሰለ ለምና ምድራዊት ገነት አገር በዓለም ውስጥ የድህነት ተምሳሌት ሆኖ መገኘት፣ የሁሉንም ህሊና ሊኮረኩረው እንደሚባ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሮጌውን አስተሳሰብ እንዳለ ተሸክመን ለመቀጠል እየዳዳን ከሆነ፣ አዲስ ዓመት ማለቱ የአፍና የጆሮ ቀለብ ከመሆን በቀር የሚሰጠን አንዳች ትርጉም የለም፡፡ ስለሆነም አዲሱን ዓመት አዲስ የሆነ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የስምምነትና የአንድነት፣ የይቅርታና የምሕረት፣ የፍትሕና የእኩልነት መርህ አንግበን ፍፁም ሰላምን ለማንገሥ በቁርጥ ማሰብና መነሳሳት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በአንድ አዳራሽና በአንድ ጠረጴዛ በመገናኘት ችግሮችን በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፓትርያርኩ አያይዘውም የ2015 ዓ.ም. አዲስ ዓመትን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፣ በኢትዮጵያ ገጠርና ከተማ የሚኖሩ፣ ከአገር ውጭ በተለያዩ አኅጉር የሚገኙ፣ ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ ለቆሙ፣ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ለሚገኙ፣ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የሕግ ታራሚ ዜጎች ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› ብለዋል፡፡