

ዜናበብልፅግና ጉባዔ ዕጩ ተመራጭ አስመራጭ ሆኖ መሰየሙ ትክክል እንዳልነበር ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
ቀን: September 14, 2022
- ፓርቲው በአራት ወራት ውስጥ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ተጠይቋል
- መተዳደሪያ ደንቡን አስተካክሎ እንዲያፀድቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል
ገዥው የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔውን ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት፣ ዕጩ የሆነ ሰው በአስመራጭነት መሰየሙ ትክክል እንዳልነበረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በጉባዔው ላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አመራረጥን በተመለከተ፣ ዕጩ የሆነ ሰው አስመራጭ የሚሆን ከሆነ፣ በተለይም አስመራጭ የነበሩት የአገር መሪ በመሆናቸው በምርጫው ሒደት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር አሠራር መሆኑን አስታውቋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት አድርጎ በመረጠበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው አስመራጭ ሆነው ከመድረክ ሐሳብና አስተያየት ሲቀበሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ የምርጫ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንድ ፕሬዚዳንትና ለሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ዕጩዎችን ከጉባዔ አባላት በጥቆማ በመቀበል፣ ‹‹ዓብይ ዕጩ መሆን አለበት ወይስ የለበትም›› የሚሉ ተሳታፊዎች ሐሳብ እንዲሰጡ፣ ከተሳታፊዎት ፊት ለፊት ተቀምጠው ምርጫውን ሲያካሂዱ ተስተውሎ ነበር፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ምርጫ ከተካሄደ ከስድስት ወራት በኋላ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፓርቲው በጠቅላላ ጉባዔ የምርጫ አካሄዱን አስመልክቶ ለምርጫ ዕጩ ሆኖ የሚቀርብ ሰው፣ አስመራጭ እንዳይሆን የሚከለክል አንቀጽ በማስፈር፣ መተዳደሪያ ደንቡን አስተካክሎ ወደፊት በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያፀድቅ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲውን ወክለው በምርጫው የሚሳተፉ አካላት ስለሚመረጡበት ሁኔታ ማዕከላዊ ኮሚቴው መመርያ እንደሚያወጣ በተገለጸው መሠረት፣ መመርያ ወጥቶ ለቦርዱ እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡
የፓርቲ የምርጫ ሥርዓት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ በግልጽ ሊካተት የሚገባው ጉዳይ ቢሆንም በዝርዝር የምርጫ አስፈጻሚ የሆነው አካል ማን እንደሆነ፣ ይህ አካል እንዴት እንደሚመረጥ፣ የምርጫው አካሄድ ምን እንደሚመስል፣ ለምሳሌ የዕጩ ጥቆማ፣ በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ፣ ድምፅ ቆጠራ፣ ውጤት ማዳመር፣ ውጤት አገላለጽና ሌሎች ሒደቶች በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ያልተካተቱ በመሆናቸው፣ በሚቀጥለው ስብሰባ አስፈላጊ ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ ቦርዱ ጠይቋል፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት በተደረገው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ የቦርዱ ታዛቢዎች መከልከላቸውን በመጥቀስ፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የቦርዱ ታዛቢዎች አለመገኘታቸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አመራረጥን እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ቦርዱ አስታውሷል፡፡
የቦርዱ የውሳኔ ሪፖርት እንደሚያሳየው የፓርቲው የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት ብዛት ስብጥርና አመራረጥን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመርያ የለውም፡፡ በተጨማሪም ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት ፓርቲዎቸ በሚያደርጓቸው ጉባዔዎች፣ ቦርዱ ትዝብት ሲያደርግ ባለሙያዎች በጽሑፍ ከሚይዙት ዘገባ በተጨማሪ በቪዲዮ እንዲቀረፅ የሚፈቅድ ቢሆንም፣ ብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ይህን እንዳያደርጉ መከልከሉን በመግለጽ ይህንን ‹‹ተቀባይነት የሌለው›› ተግባር በድጋሚ እንዳይፈጽም ዕርምት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን አባላት በአዋጁና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ የተመረጡ ሳይሆን፣ ለጠቅላላ ጉባዔ ብቻ ቀርበው የተሾሙ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ቦርዱ ይህን ደብዳቤ ከጻፈበት ከመስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአራት ወራት ውስጥ እስከ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም. አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት፣ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አባላት ምርጫ እንዲያካሂድ ቦርዱ አሳስቧል፡፡