
ከ 5 ሰአት በፊት
የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥን አስክሬን የያዘው ሳጥን ከባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት በንጉሥ ቻርለስ፣ በልዑል ዊሊያም እና ሃሪ እንዲሁም በሌሎች ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ታጅቦ ከወጣ በኋላ በዌስትሚኒስቴር አዳራሽ አርፏል።
ከአስከሬን ሳጥኑ ላይ ታዲያ ትኩረትን የሚስበው አንጸባራቂው ዘውድ ተቀምጧል። ይህ ዘውድ የብሪታኒያ ነገሥታት ለበርካታ ክፍለ ዘመናት በሰበሰቧቸው በሺህዎች በሚቆጠሩ ውድ ማዕድናት የተንቆጠቆጠ ነው።
በዚህ ዘውድ ላይ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ውድ ማዕድናት አሉ። 2 ሺህ 868 አልማዞች፣ 273 እንቁ፣ 17 ሳፋየር፣ 11 ኢመራልድ እና 5 ሩቢስ።
“አንዳንድ ጊዜ ከሚያንጸባርቁት ብርሃን የተነሳ ዘውዱን መመልከት ከባድ ይሆናል። በጣም አንጸባራቂ ነው…” ይላሉ ‘ክራውን ጂዊልስ’ የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት የታሪክ ምሁር አን ኬይ።
በጥንት ዘመን ይላሉ የታሪክ ተመራማሪዋ፤ በጥንት ዘመን ዘውድ የሃብት እና የክብር መገለጫ ነበር።
“ግርማዊነትን ይገልጻል፤ የሉዓላዊነት መገለጫም ነው።”

ለንግሥት ኤልዛቤጥ ዳግማዊት አባት ንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ ንግሥና እአአ በ1937 የተሰራው ይህ ዘውድ፤ ከንግሥት ቪክቶሪያ ጀምሮ ጥቅም ላይ ሲውል ከነበረው ዙፋን በተሻለ መልኩ ቀለል ያለ እና ጭንቅላት ላይ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀመጥ ተመጥኖ የተሰራ ነው።
ይህ ዘውድ ክብደቱ ተቀንሶ ተሰርቷል ቢባል 1.06 ኪሎ ግራም ይመዝናል።
ንግሥት ኤልዛቤጥ በሕይወት በነበሩበት ወቅት በዓመት አንዴ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ዕለት ያደርጉት ነበር።
ንግሥቱቷ በወርቃማው ዙፋን ላይ ተቀምጠው እና ዘውዳቸውን ደፍተው የመጪውን ዓመት የመንግሥት ቁልፍ ተግባራትን ያነቡ ነበር።
እአአ 2018 ላይ ንግሥት ኤልዛቤጥ የዘውዱን ክብደት በተመለከተ ቀልደው ነበር። “ጽሑፉን ለማንበብ ወደ ታች መመልከት አይቻልም፤ ወረቀቱን ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ግድ ነው፤ ምክንያቱም ቀና ከተባለ አንገት ሊሰበር ይችላል” ብለው ነበር።
ንግሥቲቷ 90 የዕድሜ ክልልን ከተሻገሩ በኋላ ክብደቱ ያነሰ ዘውድ እንዲጠቀሙ ተደርጎ ነበር። እአአ 2021 ላይ ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፉበት የምክር ቤቱ መክፈቻ ላይ እስከነ አካቴው ዘውድ አላደረጉም ነበር።

የንግሥቲቷ ዘውድ በሌላኛው መጠሪያው ‘ሰከንድ ስታር ኦፍ አፍሪካ’ ተብሎ የሚታወቀውን 317 ኩሊናን ሁለት አልማዝን ጨምሮ ይዟል።
ይህ አልማዝ ከዓለም ትልቁ ከሆነ አልማዝ የተቆረጠ ሲሆን፣ ለንጉሥ ኤድዋርድ 7ኛ የ66ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ ከቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ትራንስቫላ መንግሥት (ከአሁኗ ደቡብ አፍሪካ) በስጦታ መልክ የተሰጠ ነው።
ይህ ዘውድ በ11ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ንጉሥ ኤድዋርድ የጣት ቀለበታቸው ላይ ያደርጉት የነበረው እንቁንም አለበት። ይህ የከበረ ድንጋይ ከዘውዱ የላይኛው ክፍል መሃል ላይ ተለብጦ ተቀምጧል።
በዘውዱ ላይ ያለው ‘ብላክ ፕሪንስ ሩቢ’ የሚባለው ቀይ ውድ ድንጋይ የንግሥት ኤልዛቤጥን ትኩረት ይስብ ነበር።
ይህ ውድ ድንጋይ እአአ በ1415 የእንግሊዝ ኃይሎች በንጉሥ ሄንሪ አምስተኛ እየተመሩ የፈረንሳይ ጦርን ባሸነፉበት አግኒኮርት አውደ ውጊያ ንጉሡ አድርገውት እንደነበረ ይታመናል።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ለቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ዘውዱን በቅርበት ሆኖ የመመልከት ዕድል አግኝታ የነበረችው ፕሮግራም አቅራቢ ክሊቭ ሜሪ “የአልማዞቹ ጥራት የማይታመን ነው” ስትል ተናግራ ነበር።
የዘውዱ ዋጋ ስንት ነው?
የንግሥቲቱ ዘውድ ዋጋው የሚተመን አይደለም። የንጉሣውያን አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አሊስተር ብሩስ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ዋጋውን በገንዘብ መገመት በጭራሽ የማይታሰብ ነው።
ዋጋው ሊተመን የማይችል ማለቱ ሊያግባባ እንደሚችል በመግለጽ፣ በገንዘብ ዋጋውን ለማወቅ በዘውዱ ላይ ባሉት እንቁዎች ልክ ዜሮዎችን መጨመር ይቻላል ይላሉ።
የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ዘውድ ጥቅም ላይ በማይውልበት ወቅት ለንደን ታወር በሚገኘው ጂውል ሐወስ ለሕዝብ ዕይታ ይቀመጣል።
ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ የቀደመ ሥርዓቱን በመከተል በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ይህን ዘውድ ደፍተው ይታያሉ።
ከዚያ በኋላም በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ዕለት እና በሌሎች ይፋዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ዘውዱን ደፍተው ይቀርባሉ።