

September 18, 2022
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል በሚደረጉ ግጭቶች መፈናቀልና ውድመት ያስተናገደው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ለ2015 በጀት ዓመት 6.7 ቢሊዮን ብር የተያዘለት ቢሆንም፣ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ለመተግበር ግን 38.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታወቀ፡፡
ለ2015 በጀት ዓመት 6.7 ቢሊዮን ብር በጀት ያፀደቀው ክልሉ፣ አሁን ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው ገንዘብ የዘንድሮ በጀቱን ስድስት እጥፍ ገደማ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልፈውን በጀት ከዕርዳታ ድርጅቶችና ከኅብረሰተቡ ለማሰባሰብ ያቀደው የክልሉ መንግሥት፣ ገቢ የማሰባሰብ ሥራውን ለመምራት የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መመርያ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተዘጋጀው የመልሶ ግንባታና መቋቋም ዕቅድ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የመልሶ ማቋቋም ስትሪንግ ኮሚቴ የፀደቀ ሲሆን፣ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ እንደሆነና ትግበራውም በሦስት ምዕራፎች እንደሚከፋፈል፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ የመልሶ ግንባታ ዕቅዱን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ የዋለው የጉዳት ጥናት የተካሄደው በወረዳና ቀበሌ ድረስ ያሉ የመንግሥት ቢሮዎች በየዘርፋቸው ያቀረቡትን የጉዳት መጠን በማዋቀር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መሪነት የተካሄደ ጥናት እንደ ግብዓትነት ተወስዷል፡፡ ኮሚሽኑም በተሳተፈበት የዩኒቨርሲቲው ጥናት በክልሉ በተካሄዱ ግጭቶች ሳቢያ 79.4 ቢሊዮን ብር ውድመት መድረሱን አሳይቷል፡፡ ጥናቱ 16 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት በግጭት ምክንያት መውደሙንና ሳይመረት መቅረቱን፣ መገኘት የነበረበት የሰብል ምርት 44 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ አመላክቷል፡፡ መሰብሰብ የነበረበት የመንግሥት ገቢንም በተመለከተ በሁለት ዓመት ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደታጣ በጥናቱ ተገልጿል፡፡
‹‹የእኛ ጥናት አሁን ልንመልሰው የምንችለው ውድመት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፤›› ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ በኮሚሽኑ የተደረገው ጥናት ከሰብል ምርትና ገቢ የታጣውን ገንዘብ እንዳላካተተ አስረድተዋል፡፡ የኮሚሽኑ ጥናት የወደሙ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውሰውም፣ በሁለቱ ጥናቶች መካከል ያለው የገንዘብ ልዩነት የመጣው በዚህ የተነሳ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መሪነት የተደረገ ጥናትን መሠረት ያደረገው የክልሉ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ በስድስት ዘርፎች የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የሚዘረዝር መሆኑ ተገልጿል፡፡ አደጋ ሥጋት አመራር፣ በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት፣ በጤና ጥበቃና በትምህርት ዘርፎች በዕቅዱ ውስጥ ከተካተቱት ዘርፎች መካከል ናቸው፡፡
በክልሉ በሚገኙት መተከል፣ ካማሺና አሶሳ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት 475,384 ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ ከተፈናቃዮዎቹ መካከል ከ77,500 የሚልቁት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው ሕፃናት ሲሆኑ፣ 20 ሺሕ ገደማ የሚያጠቡ እናቶች መኖራቸውም ተገልጿል፡፡ ጥናቱ የፀጥታ መደፍረሱ ለ43,640 ቤቶች መውደም ምክንያት መሆኑን አስቀምጧል፡፡
ከ2011 ዓ.ም. አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የንፁኃን ግድያና ግጭት ሲያስተናግድ የከረመው ክልሉ፣ 113 ሺሕ ገደማ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሆኑ በዕቅዱ ላይ ተመልክቷል፡፡ ለተማሪዎቹ ከትምህር ገበታ ውጪ መሆንና የነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ በዋነኛነት ደግሞ የትምህር ቤቶች መውደም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
የክልሉ መልሶ ግንባታ ዕቅድ እንደሚያሳየው ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች 201 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ፣ 86 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ 126 የጤና ኬላዎችን ጨምሮ 142 የጤና መሠረተ ልማቶችም ክልሉ በግጭቶች ሳቢያ እንደወደሙ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በሰፋፊ እርሻዎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የእርሻ መሬት የሚያቀርበው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የ109 የግብርና ተቋማት ማከማቻ መጋዘን እንደተዘረፉበት፣ እንዲሁም በከፊልና ሙሉ በሙሉ እንደወደሙበት ታውቋል፡፡ 291 የአርሶ አደር ማሠልጠኛ ተቋማትና 140 የእንስሳት ጤና ኬላዎችም ተመሳሳይ ዕጣ እንደደረሰባቸው ጥናቱ አሳይቷል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዚህ ዓይነት መልኩ ጉዳቶችን በዘረዘረው መልሶ መቋቋሚያ ዕቅድ ትግበራ ላይ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ መኖሪያ ቀያቸው ማስመለስና በዘላቂነት የማቋቋምን ቅድሚያ ሰጥቶታል፡፡ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ በከፊል የወደሙትን መጠገንና የተጓደሉ የውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላትም የዕቅዱ አካል ነው፡፡
በክልል ደረጃ ካለው ስቲሪንግ ኮሚቴ ባሻገርም በወረዳ ደረጃ ስቲሪንግና ቴክኒካል ኮሚቴዎች ተዋቅረው መልሶ ግንባታውን እንደሚያስፈጽሙ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
ዕቅዱን በአደጋ ሥጋት አመራር፣ በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት፣ በጤና ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሀብት ልማት፣ በሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ዘርፍ እንዲሁም በሰላም ግንባታና ፀጥታ ዘርፎች ለመተግበር 38,504,430,908 ብር እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ይኼንን ያህል ገንዘብ ለመልሶ ግንባታ የመበጀት አቅም እንደሌለው የገለጹት ኮሚሽነሩ አቶ ታረቀኝ፣ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ዕቅዱን ወስደው ሀብት እንዲያሰባስቡ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች መልሶ ግንባታውን ለማገዝ ያላቸውን ፈቃደኝነት አሳይተውናል፤›› ብለዋል፡፡ ዲያስፖራዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች አካላትም በሚገኝ ገቢ ዕቅዱን ለማሳካት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን ይፋ ያደረጉት የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ፕሮጀክትም የክልሉን ዕቅድ ያግዛል የሚል ዕቅድ ተይዟል፡፡ የፌደራል መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን ያስጀመረው በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ሊካሄድ ከታቀደባቸው ስድስት ክልሎች ውስጥ አንደኛው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡ የፀጥታ ችግር ባልተቀረፈባቸው አካባቢዎች ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በሦስተኛ ወገን ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት (UNOPS) እንዲተገብር ውክልና ሰጥቷል፡፡
የጤናና ትምህርት ሚኒቴሮች በስድስቱም ክልሎች የደረሰውን ጉዳት አጥንተው በአምስት ዓመት ለሚተገበረው የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ወጪ የሚገልጽ ሪፖርት አዘጋጅተዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትምህርት ቤቶች ላይ ከደረሰው ጉዳት ለማገገም 96.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ሲገልጽ፣ ጤና ሚኒስቴር ደግሞ በክልሉ የጤና ዘርፍ እንዲያገግም 22.35 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በሪፖርቱ ላይ አስታውቋል፡፡