
ከ 37 ደቂቃዎች በፊት
ኤርትራ የተጠባባቂ ጦር መጥራቷን በተመለከተ የተሰራጨው ዜና የተጋነነ እና ከእውነታው የራቀ ነው ሲሉ የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አስተባበሉ።
ባለፈው ሳምንት ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ የዜና አውታሮች በኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ ተጠባባቂ የጦር ኃይሉ አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደተጠሩ መዘገባቸው ይታወሳል።
በዚህም ከአገሪቱ መንግሥት በቀረበው ጥሪ መሠረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙ እና ከመደበኛው ሠራዊት ውጪ ለሆኑ የተጠባባቂ ኃይሉ አባላት ጥሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ምንጮች እንዳሉት በርካቶች ሐሙስ መስከረም 05/2015 ዓ.ም. በመዲናዋ አሥመራ እንደተሰባሰቡ ገልጸዋል።
ነገር ግን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ የማነ ገብረመስቀል “ኡልሪህ ከፕል” ከተባለ የጀርመን ድረ ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ፣ ለተጠባባቂው ኃይል የቀረበውን ጥሪ በተመለከተ “ሆን ተብሎ እውነታው እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል” ብለዋል።
ኤርትራ አጠቃላዩን ሕዝቧን ወደ ሠራዊቷ እያስገባች አይደለም። መሬት ላይ ያለው እውነታ ሆን ተብሎ እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የተወሰኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላት የተጠሩ ቢሆንም ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው” ብለዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የካናዳ መንግሥት በትዊተር በኩል ያሰራጨውን የጉዞ ማሳሰቢያን ጠቅሶ እንደዘገበው በኤርትራ አጠቃላይ ጥሪ ለሠራዊቱ አባላት መቅረቡን አመልክቷል።
“በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ተከትሎ የአካባቢ ባለሥልጣናት ለሠራዊቱ በአጠቃላይ የክተት ጥሪ አቅርበዋል” ብሏል ከካናዳ መንግሥት ኤርትራን አስመልክቶ የወጣው የጉዞ ማሰሰቢያ።
ይህ የትዊት መልዕክት እንዳለው ጥሪው አስከ 60 ዓመት የሚሆኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላትን ይመለከታል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ጨምሮም የካናዳ መንግሥት በኤርትራ የሚገኙ ዜጎቹ እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ እና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንን እንዲከታተሉ መክሯል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ተሳታፊ እንደነበሩ በስፋት የተዘገበ ሲሆን፣ በትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉ ግድያዎችና ከባድ የመብት ጥሰቶችን በመፈጸም በዓለም አቀፍ የመብት ተቋማት ይከሰሳሉ።
- የህወሓት የሰላም ጥሪ እና የመንግሥት ዝምታ17 መስከረም 2022
- በኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 በታች የሆኑ ተጠባባቂ ኃይሎች በአስቸኳይ ጦሩን እንዲቀላቀሉ ታዘዙ16 መስከረም 2022
- ስላገረሸው ጦርነት እና ስለህወሓት የሰላም ጥሪ እስካሁን የምናውቀው15 መስከረም 2022
በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛምቶ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።
የፌደራሉ ሠራዊት በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎችን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ ሁለቱም ኃይሎች ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ተኩስ ለማቆም ስምምነት አድርገው ቆይቷል።
ነገር ግን ይህ የተኩስ አቁም ለአምስት ወራት ተግባራዊ ሆኖ ከቆየ በኋላ ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት ማብቃቱ ይታወሳል።
ለዚህም አንደኛው ወገገን ሌላኛውን ጦርነቱን በመጀመር ይከሳል።
መልሶ ያገረሸው ጦርነት በተለያዩ ስፍራዎች ላይ እየተካሄደ መሆኑ ሲነገር፣ የትግራይ ኃይሎች ከፌደራሉ ሠራዊት በተጨማሪ የኤርትራ ጦርም ጥቃት ከፍቶብናል ሲሉ ከስሰዋል።
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጥምር ጦር ሽራሮን ጨምሮ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
የኤርትራ መንግሥት ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በዋና ከተማዋ አሥመራ፣ የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ከረን፣ በምዕራባዊዋ ተሰነይ እና በሌሎችም አካባቢዎች ውስጥ ላሉ የተጠባባቂ ኃይል አባላቱ ጥሪውን አቅርቧል።
አንድ ዲፕሎማት ለሮይተርስ እንደተናገሩት “በኤምባሲዎች፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጊቢ እና በመኖሪያዎች ውስጥ የሚሰሩ የጥበቃ ሠራተኞች በስፋት እየተካሄደ ባለው ምልመላ ምክንያት እነሱም ሊካተቱ እንደሚችሉ በመግለጽ ስጋት ውስጥ ናቸው” ብለዋል።
የሠራዊት እንቅስቃሴ ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ ካለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተጨማሪ የደኅንነት ጥበቃ እርምጃዎች በመላዋ ኤርትራ ሊወሰዱ ይችላሉ ካለው የካናዳ መንግሥት በተጨማሪ፣ የብሪታኒያ መንግሥትም በኤርትራ ላሉ ዜጎቹ የጉዞ ማሳሰቢያ አውጥቷል።
የብሪታኒያ የጉዞ ማሳሰቢያ እንዳለው የኤርትራ መንግሥት ጥሪውን ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መሆኑን አመልክቶ በዚህም ዜጎቹ “በዚህ ወቅት በጣም ጠንቃቃ” መሆን እንዳለባቸው መክሯል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ለጀርመኑ ድረ ገጽ ከተናገሩት ባሻገር የኤርትራ መንግሥት የተጣባባቂ ጦሩ እንዲከት ስላቀረበው ጥሪ በይፋ ያለው ነገር የለም።
ይህ የክተት ጥሪ የተሰማው ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ባገረሸበት ወቅትና በጦርነቱ የኤርትራ ጦር ተሳታፊ መሆኑ ህወሓትን ጨምሮ በተለያዩ ወገኖች እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ኤርትራ እንቅፋት ሆናለች በማለት ከሶ ነበር።
ነገር ግን ብራስልስ ውስጥ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በኅብረቱ የቀረበውን ክስ አጣጥሎ፣ “ለዘመናት በቆየ ጦርነቶች የተጎዳችው ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን ቁርጠኛ ፍላጎት” አላት በማለት ህወሓትን ጦርነቱን መልሶ በመቀስቀስ ከስሷል።
ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላ ዜጎቿ ለዓመታት በሚቆይ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ውስጥ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው። ይህም በርካታ ወጣቶች ከአገራቸው እንደሰደዱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ 18 2014 ዓ.ም መልሶ የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ኤርትራ ተጠባባቂ የሠራዊት አባሎቿን ለክተት እንድትጠራ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል።