ኤልያስ ተገኝ

September 25, 2022

ቆይታ

ከስድስት ወራት በፊት በሁለቱ የአውሮፓ አገሮች በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ሲጀመር፣ የዓለም ኢኮኖሚ እያገገመ ከነበረበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ለመላቀቅ እየተፍጨረጨረ ነበር፡፡ ሆኖም ጦርነቱ የዓለም ኢኮኖሚን ከምርት እስከ አቅርቦት ያለውን ሰንሰለት ቅፅበታዊ በሆነ መንገድ አናግቶታል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን  ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በግጭቱ ሳቢያ በተፈጠረው የወሳኝ ምርቶች ዋጋ ግሽበት፣ በዓመት ውስጥ የሚያወጡትን የግዥ ወጪ በመንፈቅ ውስጥ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባዘጋጀው የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖና ከዚያ ለመውጣት ሊደረግ ስለሚገባው መፍትሔ የዳሰሰ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስርፀትና ፐብሊኬሽን ዳይሬክተር ሆነው ከማገልገል ባለፈ፣ በዩኒቨርሲቲው የተተገበሩ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መርተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ60 በላይ የሆኑ የምርምር ጽሑፎችን በታዋቂ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ በፖሊሲ ውይይት መድረኩ ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ እንዲሁም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ዓይነት ገጽታ ነበረው በሚለው ላይ ኤልያስ ተገኝ ከመንግሥቱ (ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት አልፈውታል፡፡ አገሮቹ ወደ ግጭት ከመግባታቸው በፊት በዚህን ያህል መጠን የዓለምን ኢኮኖሚ ስለመሸከማቸው ይታወቅ ነበር? ወይስ ጦርነቱ ነው ይህንን ያመላከተው?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ሁለቱ አገሮች በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ፣ የእነዚህ አገሮች ግጭት ውስጥ መግባት የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደዚህ ከባድ ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ ለዓለም ገበያ ያላቸው ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ በብዛት የታወቀው በጦርነቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እኔም በግሌ ይህን ያህል ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ብዬ ገምቼ አላውቅም፡፡ የሌሎች የአውሮፓ አገሮች በተለይም የኢነርጂ (ነዳጅ) ዘርፉ ሁለቱ አገሮች ላይ ጥገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ተፅዕኖው እንዲህ ጎልቶ ወደ እኛ አገር ይመጣል የሚል ግምት ብዙ ሰው አልነበረውም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሮቹ ወደ ጦርነቱ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ ያደረሰው ተፅዕኖና አገሮቹ የሰጡት ምላሽ እንዴት  ይታያል?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ተፅዕኖው በዋናነት በተለይም በታዳጊ አገሮች ላይ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የእኛ አገር ደግሞ በፊትም ችግር ውስጥ የነበረ ኢኮኖሚ ስለነበረ፣ ሌላ ነዳጅ የተጨመረው እርሱ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የውስጥ ግጭቱ ከባድ ነው፣ ኢኮኖሚውን በደንብ አንገዳግዶታል፡፡ የዋጋ ንረቱ ከጦርነቱም (ከሩሲያና የዩክሬን) በፊት ነበር፡፡ ሕዝቡ በዚህም በዚያም ሲንገላታ ነበር፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ድርቅም ተከስቶ ነበር፡፡ ይህም የኢኮኖሚ ተፅዕኖው ከባድ ነበር፡፡ በዋናነት የምግብ፣ የነዳጅና የማዳበሪያ ዋጋ ላይ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው ተፅዕኗቸው የከፋ የሚሆነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከነዳጅ ጋር ተያይዞ ያለው ተፅዕኖ ነው ጉዳት የሚያስከትለው፡፡ ያለ ነዳጅ የሚንቀሳቀስ ነገር የለም፣ ነዳጅ ዋጋ ከጨመረ ዋጋው የማይጨምር ዕቃ የለም፡፡ ምርት ከተመረተ ለማጓጓዝ ነዳጅ ያስፈልጋል፣ አሊያም ምርቱን ለማምረት የሚያስፈልግ ግብዓት ለማጓጓዝ ነዳጅ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማዳበሪያን ለማምረት ነዳጅ እንዲሁ አንዱ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡ ስለዚህ ነዳጅ ተፅዕኖው በጣም ከባድ ነው፡፡ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ግብዓቶች ውስጥ አንዱ ማዳበሪያ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ተፅዕኖ ከኢትዮጵያ አኳያ ካየነው በዋናነት ተፅዕኖ የሚታየው በተለይም በስንዴና ዘይት ግዣችን ነው፡፡ አገሪቱ ከውጭ ከምታስገባው አጠቃላይ የስንዴ ምርት 40 በመቶ የሚሆነው የሚቀርበው ከሁለቱ አገሮች ነው፡፡ በዘይትም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡

ከዚያ በተረፈ ተፅዕኖው በሌሎች አገሮችም ላይ ስለሆነ ከሁለቱ አገሮች በማናስገባቸው ምርቶች ላይ እንደዚያው ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ለምሳሌ ማዳበሪያን ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ነው የምታስገባው፣ ነገር ግን እዚያ ዋጋ ሲጨምር ተፅዕኖው በእኛ አገር ላይም የሚንፀባረቅ ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮችን ስናይ በተለይ 25 ያህል የአፍሪካ አገሮች ከውጭ ከሚያስገቡት የስንዴ ምርት ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው ከሁለቱ አገሮች ነው፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ከውጭ ከምታስገባው ስንዴ ሙሉ በሙሉ የምታስገባው ከሁለቱ አገሮች ነው፡፡ ሶማሊያም በተመሳሳይ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ስንዴ ታስመጣለች፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በሁለቱ አገሮች ላይ ጥገኛ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ተፅዕኖው እንግዲህ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ነው የሚንፀባረቀው፡፡ በዚህ ወቅት የሚታየው ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ቀጣይነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ምርታማነትን ለማሳደግ አንዱ ግብዓት ማዳበሪያ ነው፡፡ የማዳበሪያ ዋጋ በዚህ ጊዜ በአገር ውስጥም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አርሶ አደሩ በሔክታር የሚጠቀመውን የማዳበሪያ መጠን ይቀንሳል፡፡ ያ ሲሆን ምርትም በዚያው ልክ የሚቀንስበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ምናልባትም ከሚጠበቀው የምርት መጠን ሃያና ሃያ አንድ በመቶ አካባቢ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል (የማዳበሪያ አጠቃቀም በመቀነስ)፡፡ እነዚህ ዋነኞቹ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹም የአፍሪካ አገሮች የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መባባስን ተከትሎ እየወሰዷቸው ያሉ ዕርምጃዎች እንዴት ይገመገማሉ?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ተፅዕኖውን ለመቋቋም አገሮቹ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በቂ ነው? አይደለም? የሚለውን በሒደት የምናየው ይሆናል፡፡ ችግሩ ግን በአጭር ጊዜ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፍታት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ የንግድ አጋርን ወዲያውኑ መቀየር ይከብዳል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ማስተካከያ እስኪወሰድ ድረስ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ አሁን በራስ አቅም የሚካሄዱ ጥረቶች እየተደረጉ ያሉ ይመስለኛል፣ ያ መጠናከር አለበት (በረዥም ጊዜ መሠራት ካለባቸው ነገሮች ውጪ)፡፡ ለምሳሌ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማዳበሪያ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ሌላ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አሉ፡፡ ምርጥ ዘር፣ የተለያዩ ኬሚካሎችና ፀረ አረም የመሳሰሉ በአገር ውስጥ የሚመረቱ፣ እነሱን በተወሰነ ደረጃ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል ምርትን ለማሳደግ መጣር ያስፈልጋል፡፡ የምንጠቀመው የኃይል አማራጭ የመፈለግና የመቆጠብ የመሳሰሉትን ሥራዎች ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በረዥም ጊዜ ደግሞ ከውጭ የሚመጡትን የማዳበሪያና የነዳጅ ምርቶችን አገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበት አጋጣሚ ካለ አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በምግብ ራሳችንን እንችላለን የሚል ጥረት እየተደረገ ነው፣ መንግሥትም አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የማዳበሪያ ኢንቨስትመንትም ሆነ ሌሎቹም ቶሎ ሊተኩ የማይችሉና አቅም የሚጠይቁ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያ መፈተኗ የገበያ አድማስን ያለ ማስፋት ተፅዕኖ ውጤት ነው ሊባል አይችልም? ከዚህ ቀደም ከአጎዋ ዕገዳ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ተፅዕኖ እንዳለ ስለሚታወቅ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- የገበያ አማራጭ ማስፋት አስፈላጊ እንደሆነ ቀደም ብዬ የገለጽኩ ሲሆን፣ ነገር ግን አማራጩን ወዲያውኑ መቀየር ትንሽ ይከብድ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተሠርተው አማራጭ የንግድ አጋሮችን መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ እንደተጠቀሰው አሜሪካ አጋራችን ከያዘችው የፖለቲካ አቋም ጋር በተያያዘ ምክንያት ከአጎዋ ዕድል እንድንወጣ ተደርጓል፡፡ ይህም በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ከዚያም ሲወጣ ሌላ አማራጭ አገር ቢኖር ኖሮ ጉዳቱ (ተፅዕኖው) የከፋ ላይሆን ይችላል፡፡ አማራጭ መፈለግ ሁልጊዜም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የምንልከውን ብቻ ሳይሆን፣ ማዳበሪያ የምንገዛባቸውን አገሮች ብናበዛ አንዱ አገር ላይ ችግር ሲኖር፣ ሌላው አገር ላይ ቢያንስ አቅርቦቱ ላይ ችግር አይኖርም (ሌላው ምርት ላይ በተመሳሳይ)፡፡ ሌላው አኅጉራዊ ትስስሩን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች እርስ በርሳቸው የንግድ ልውውጣቸውን የሚያጠናክሩበትን ዕድል ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከሁለቱ  አገሮች ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ምርቶችን በመግዛት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ይነስም ይብዛ ወደ እነዚህ አገሮች የምትልካቸው ውስን የግብርና ምርቶች አሉ፡፡ ይህስ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ወደ ሁለት አገሮች የምንልከው ምርት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከምንልከውም አብዛኛውን ድርሻ የሚወስደው ቡና ነው፡፡ ለምሳሌ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ከምታስገባው ምርት ከ90 በመቶ በላይ ቡና ነው፡፡ ያ ማለት የምንልከው ብዙ ነው ማለት ሳይሆን፣ ከዚያች ከትንሿም ብዙ ድርሻ የሚወስደው ቡና ነው ለማለት ነው፡፡ የዩክሬንም ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የምርት ዓይነቶች በዓይነት ብዙ አይደሉም፣ ውስን ናቸው፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ አገሮቹ ከኢትዮጵያ ምርት አለመግዛታቸው ያን ያህል የጎላ ተፅዕኖ አያስከትልም፣ ምናልባትም ከሌሎች አገሮች ምርቱን ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱ አገሮች ጦርነት ባለማባራቱ በቀጣይ የሚጠበቀው ነገር ምንድነው? ለአብነትም እርስዎ ባቀረቡት ጥናት ላይ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ለስንዴ፣ ለማዳበሪያና ለነዳጅ ግዥ ብቻ 3.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣች ተገልጿልና በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ኢትዮጵያ በተለይም ከነዳጅና ከማዳበሪያ ጋር በተገናኘ፣ ከዚህ ቀደም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የምታወጣውን በግማሽ ዓመት አውጥታለች፡፡ ይህ ማለት አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ የምታገኘውን ዶላር በእነዚህ ሦስት ምርቶች (ምግብ፣ ነዳጅና ማዳበሪያ) እያስወጧት ነው፡፡ በሒደት ምን ይሆናል የሚለው ሲታይ በአገር ደረጃ በሚወሰደው ዕርምጃ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ለአብነትም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ዘይትና ስንዴ የማምረትና የማቅረብ ጥረቶችን ማጠናከር ከተቻለ ተፅዕኖውን የመቀነስ ዕድላችን ሰፊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ዕድል ያላት አገር ናት፡፡ መሬት፣ የውኃ ሀብት፣ የሰው ኃይል አለ፡፡ እነዚህን አስተባብሮ ሠርቶ ወደ አገር የሚገባውን መቀነስ መቻል ጥሩ ነው፡፡ ትልቁ እንቅፋት የሚሆኑት የነዳጅና የማዳበሪያ ምርቶች ናቸው፡፡ ኬሚካል ማዳበሪያን በተፈጥሯዊ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶች እየተኩ ማቻቻል ቢሞከር፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ያህል ምርት ማምረት ባይቻል እንኳን የሚቻለውን ያህል በማግኘት ተፅዕኖውን መቀነስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ አገሮች ግጭት ከቀጠለ ተፅዕኖው መቀጠሉ አይቀርም፡፡ የዓለም አገሮች ከኮሮና ተፅዕኖ እ.ኤ.አ. በ2023 እንወጣለን፣ በፊት ወደ ነበርንበት እንመለሳለን ብለው ይሠሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ሲከሰት ያ ትንቢት በፍፁም እንደማይሠራ ታውቋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ያደጉት አገሮችም ከኮቪድ በፊት ወደ ነበሩበት ሁኔታ አይመለሱም፡፡ ስለሆነም በዓለም ደረጃ የሁለቱን አገሮች ጦርነት አስታኮ የተፈጠረው ቀውስ ተፅዕኖው ትልቅ ስለሆነ፣ በዚህ ሒደትም ተጎጂዎቹ ብዙ አገሮች ስለሆኑ ሁለቱ አገሮች ሽኩቻቸውን በሒደት እያለዘቡ ሄደው ጦርነቱን ያቆማሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡-  ባቀረቡት ጥናት ላይ በረዥምና በአጭር ጊዜ ሊደረጉ የሚገቡ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ካሏቸው  መካከል  ምርትና ምርታማነትን በተመለከተ፣ እንዲሁም ከነዳጅ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡ በዚህ ላይ መሠራት የሚገባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ነዳጅ በዋጋ ጭማሪ ምክንያት አቅርቦቱ ዝቅተኛ ስለሆነ አማራጮችን መፈለግ አለብን፡፡ አማራጭ ስንፈልግ ከተቻለ የነዳጅ ፍላጎትን መቀነስ ነው (ሌሎች አገሮች እያደረጉ እንዳሉት)፡፡ ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በቅርቡ የነዳጅ ፍላጎታችንን በ15 በመቶ መቀነስ አለብን ብለው እየሠሩ ነው፡፡ አባል አገሮች የየራሳቸውን ስትራቴጂ ወስደው ፍላጎቱ ቢያንስ በ15 በመቶ ቢቀነስ ብለው ከሠሩ፣ ኢትዮጵያም የራሷን ስትራቴጂ ፈልጋ መቀነሱ አንድ አማራጭ ነው (ብቸኛ አማራጭ ባይሆንም)፡፡ እንዴት ነው መቀነስ የሚቻለው? ሲባል አንደኛ ነዳጅ ቆጣቢ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚገዛውን ነዳጅ መንግሥት ደጉሟል ማለት በተወሰነ ደረጃ ለግለሰቡ ገዝቷል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም እንደፈለጉ መሆን አይገባም፡፡ ነዳጅ ቆጣቢ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለትንሹም ጉዞ ተሽከርካሪ ማስነሳት ተገቢ አይደለም፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች አካባቢ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ቆመው ይታያሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች እንዴት ነው የሚቀነሱት የሚለው ቢከብድም፣ ነገር ግን አጠቃቀሙን መቀነስ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ሁለተኛው በነዳጅ የሚሠሩ ነገሮችን (በፀሐይና በንፋስ ኃይል የሚሠሩ ማሽኖች ሊሆኑ ይችላሉ) መተካት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አማራጮችን ተጠቅሞ ተግባራዊ እየተደረጉ አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ በኬንያ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ትልልቅ የሕዝብ አውቶቡሶችና ሞተር ብስክሌቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የዚህ ዓይነት አማራጮችን በመጠቀም በተወሰነ ደረጃ የነዳጅ አጠቃቀምን መቀነስ አንድ አማራጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሩሲያና ከዩክሬን ጦርነት ተፅዕኖ በተጨማሪ በ2014 ዓ.ም. አገሪቱ የተለያዩ ሁነቶችን አስተናግዳለች፣ የተጠናቀቀው ዓመት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ዓይነት ዓመት ነበር? በበጎም ሆነ በፈተና የሚጠቀሱት ክስተቶች የትኞቹ ናቸው?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ያለፈውን ዓመት ከአገሪቱ ኢኮኖሚ አንፃር ብንመዝነው ጥሩ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ኢኮኖሚ ስናስተናግድ ቆይተናል ብዬ እገምታሁ፡፡ ያ የሆነበት ምክንያት የጦርነቱ ተፅዕኖ ከባድ ነበር፡፡ በእሱ ላይ ደግሞ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ተጨምሮበት የዋጋ ግሽበቱ በ30 በመቶ ቤቶች ውስጥ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም የምግብ የዋጋ ግሽበት ሲታይ ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ የዘለለባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ በዚያም የተነሳ ኅብረተሰቡ ተማሮ የቆየበት ነው፡፡ ዓመቱ ግጭት በየቦታው ሲካሄድ የነበረበት ነው፡፡ የአገሪቱ የዕዳ ጫና በጣም ከባድ ሆኗል (ለረዥም ጊዜ ተንከባልሎ የመጣ ቢሆንም)፡፡ አሁንም አገሪቱ ትልቅ ዕዳ ውስጥ ናት፡፡ የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ክፍተቱ እየሰፋ ሄዷል (ወደ ውጭ የሚላከውና ከውጭ የሚገባው ሲተያይ)፡፡ ከውጭ ብዙ ምርቶችን የምታስገባው አገራችን የምትልከው ትንሽ ነው፡፡ የተለያዩ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ብዙ ዶላር የሚፈለግ ሲሆን፣ ምርታችን ወደ ውጭ ተልኮ የሚገኘው ዶላር ደግሞ ትንሽ ነው፡፡ የመንግሥት የውስጥ ወጪና ገቢ የተራራቀ በመሆኑ ወጪ ይበዛል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ያስተናገድንበት ዓመት ነበር፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ በአገሪቱ ዝቅተኛ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ የእንስሳት ሀብታችንን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን በአካባቢዎቹ የሚኖረውን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል፡፡ በአጠቃላይ ዓመቱ ጥሩ አልነበረም፡፡

በሌላ በኩል እነዚህን ችግሮች በመከሰታቸው ራሳችንንና አቅማችንን እንድናይ፣ ለዚያም መፍትሔ መፈለጉ ግዴታ እንደሆነ የተገነዘብንበት ዓመትም ይመስለኛል፡፡ ለቀጣይ ዓመት ብዙ መሥራት እንዳለብን ያመላከተ ዓመት ስለሆነ ጥሩ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዓመቱ መንግሥት ሲሠራቸው የነበሩ ተግባራትን ተመልክተናል፡፡ እየታዩ ያሉት ማሻሻያዎች ለምሳሌ በቴሌኮም ዘርፉ ያለው ማሻሻያ ጥሩ ነው፡፡ የቴሌኮም ዘርፉ አብዛኛውን ዘርፍ የሚያሳልጥ ስለሆነ፣ የውጭ ቴሌኮም ኩባንያ የመግባት ተስፋ ተደምሮ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ እንዲሁ ለግሉ ሴክተር ክፍት ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ በዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት በእጅጉ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው የውስጥ ግጭታችንም ወደ መቋጫ እየሄደ ያለ ይመስላል፡፡ በዚህም አዲሱ ዓመት ከ2014 ዓ.ም. የተሻለ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በተጠናቀቀው ዓመት ለነበሩት ዓበይት የኢኮኖሚ ክስተቶች  መንግሥት  የወሰደው እርምጃዎች እንዴት ይገለጻል? መወሰድ ኖሮባቸው ያልተወሰዱ ምን ዓይነት ጉዳዮች አሉ?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- በተጠናቀቀው ዓመት መንግሥት ሲሠራ ያየናቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ኢኮኖሚውንም ሆነ ዲፕሎማሲውን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የውስጥ ግጭቱን ለመቀነስ እያካሄዳቸው ያሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከኢኮኖሚው ጋር በተገናኘ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በስንዴ ምርት በአጭር ጊዜ ራስን ችሎ ወደ ውጪ ኤክስፖርት ይደረጋል የሚል ዕቅድ ይዞ ተነስቷል፡፡ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያና የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ እየተሠራ ነው፡፡ መንግሥት ዕቅዱ በተወሰነ ደረጃ ይከለሳል የሚል ሐሳብ አለው፡፡ አሶሴሽናችንም እነዚህ ዕቅዶች መከለስ አለባቸው የሚል አቋም ይዞ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ተነግሯቸዋል፡፡ ዕቅዱ አገሪቱ አሁን እያስተናገደቻቸው ያሉ ችግሮች ባልነበሩበት ወቅት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኮቪድና ግጭት ዕቅዱ ሲዘጋጅ ያልነበሩ በመሆናቸው ጦርነቱ በአገሪቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሏል፡፡ ስለሆነም ያንን መከለስ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛውን ትኩረት በማገገሚያ ስትራቴጂዎች ላይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት በራሱ ትልቅ ጥረት ስለሚጠይቅ በዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የእኛን አሶሴሽን ጨምሮ ሌሎች የሙያ ማኅበራትም መረጃን የተመረኮዘ ጽሑፎችን ሲያወጡ፣ በመንግሥት በኩል የማየትና ከተቻለም የመተግበር አዝማሚያ ቢያሳይ፣ እንዲሁም የማሳተፉን ጉዳይ ቢጨምር ጥሩ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ እኛም እየተጋበዝን ሐሳባችንን እንሰጣለን፣ አንዳንዴ ደግሞ እኛ ብንሳተፍ ጥሩ ነበሩ የምንላቸውና በዜና የምንሰማቸው አሉ፡፡ የእኛም ማኅበር ኢትዮጵያዊ ማኅበር ስለሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሻሻል፣ የኅብረተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል የእኛም ፍላጎት ስለሆነ መደገፍ ያለብንን እየደገፍን መንግሥት የተሻለ ነገር እንዲሠራ ፍላጎታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቅሉ ሲገለጽ 2015 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ዓይነት ዓመት ሊሆን ይችላል? ተስፋ ያለው ነው? ወይስ ሥጋት ያጠላበት?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ትንሽ ከበድ ቢልም እንደ ግለሰብ አዲሱ ዓመት ከ2015 ዓ.ም. የተሻለ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አንደኛው የሩሲያና የዩክሬን ግጭት ወይም ተፅዕኖ ብዙ የሚቀጥል አይመስለኝም፣ ወይ ራሳቸው መፍትሔ ይፈጥራሉ፡፡ ካልሆነም ሌሎች አገሮች በሚያደርጉት ትብብር ሌሎች አማራጮችን ልናገኝ ስለምንችል በአጭር ጊዜ እንደተጎዳነው ጉዳቱ ላይቀጥል ይችላል፡፡ ከዚያም ባሻገር በአገሪቱ ከላይ በገለጽኩት ሁኔታ በመንግሥት የተወሰዱት ዕርምጃዎች ኢኮኖሚው ላይ ጥሩ ተፅዕኖ ስለሚያስከትሉ፣ 2015 ዓ.ም. የተሻለ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የውስጥ ጦርነቱም ወይ ይቀዛቀዛል ወይ ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደ ኢኮኖሚ ተመራማሪነትዎ በ2015 ዓ.ም. ተስፋ የሚያደርጉት ምንድነው? መልካም ምኞትዎንና ተስፋዎን ቢገልጹልን?

ፕሮፌሰር መንግሥቱ፡- ለዚህ ሕዝብ ምን ትመኛለህ ብባል፣ ሕዝቡ ለረዥም ጊዜ ተሰቃይቷል ማለት ይቻላል፡፡ የአኗኗር ሁኔታውና የዋጋ ግሽበቱ ሰው መኖር የሚያቅተው ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ከዚህም የተነሳ የተለያዩ ወንጀሎች በተለይ ስርቆት እየተስፋፋ የሄደበት ነው፡፡ ሰው መኖር ሲያቅተው አንዱ እየበላ ሌላው ሳይበላ ሲቀር ዝርፊያና የመሳሰሉት ነገሮች እየተስፋፉ ሄደዋል፡፡ በዚህ ከቀጠለ በጣም የከፋም ሊሆን ስለሚችል ተስፋ የማደርገው ይህች አገር በኢኮኖሚ ራሷን የምትችልበት፣ ከሌሎች አገሮች ጥገኝነትን በተወሰነ ደረጃ የምትቀንስበት፣ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን ባይቻልም ጥገኝነቱ ቀንሶ፣ ቢያንስ የሕዝቡ አኗኗር እንዴት ልዋል? ምን ልብላ? ልጠጣ? የሚለው ነገር የማያሳስበው አገር ብትኖረን ደስ ይለኛል፡፡ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፣ የሁሉንም አስተዋጽኦ፡፡ ማለትም የመንግሥትንም ሆነ የሕዝቡን፣ እንዲሁም የተቋማትንም አስተዋጽኦ ይጠይቃል፡፡ ተባብሮ ከተሠራና ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ ካደረገ የማይሻሻልበት ምክንያት የለም፡፡ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ካልወጣን ሁሌም እንደፈለጉ የሚያደርጉን አገሮች ይበዛሉ፣ የሆነ ዕርምጃ በወሰድን ቁጥር (ለምን ይህንን ትወስዳላችሁ?)፡፡ በአብዛኛው የዓለም አገሮች የሚከሰቱ ግጭቶች መንስዔአቸው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አገር ለማደግ በሚፍጨረጨርበት ጊዜ ያንን የማይፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ፡፡

በዚህ ዘመን ከዚህ ዓይነት ጉዳይ ማምለጥ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ያን ያህል ፈተና አልነበረባቸውም በእኔ ዕይታ፡፡ አሁን አደጉ የሚባሉ አገሮች ትኩረት አድርገው ሠርተው ኢኮኖሚያቸውን አሳደጉ፡፡ ከዚያ በኋላ ወታደራዊ አቅማቸውን ወደ ማጠንከርና ሌሎች አገሮች ላይ ተፅዕኖ ወደ ማድረግ ሄዱ፡፡ በዚህ ዘመን መጀመርያ ኢኮኖሚያችንን እናሳድግ የሚባልበት ሁኔታ አማራጩ ዝቅተኛ ነው፡፡ በኢኮኖሚ እንደግ ሲባል ብዙ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ሌሎች አገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያለውን ብንመለከት ‹‹ግድቡ የውኃ አቅርቦትን ይቀንሳል›› የሚለው ጉዳይ አይደለም ዋነኛ መነሻ ጉዳዩ፣ ከዚያ ጀርባ ያለው ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ቀና እንዳትል የሚፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ፡፡ የሚረዱ የማይመስሉ ያደጉ አገሮች ሳይቀሩ ይህን ነገር አይፈልጉም፡፡ በመሆኑም ከዚያ ለመውጣት ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ያንን ፈተና አልፈን ራሳችንን የምንችልበት ደረጃ ብንደርስ ደስ ይለኛል፡፡ በቀደመው ጊዜ ከላይ እንደገለጽኩት አንዳንድ አገሮች በኢኮኖሚ አድገው ከዚያ ወታደራዊ አቅም ገነቡ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ኢኮኖሚውን ትተው በወታደራዊው አቅም ጠንክረው ወጥተው በኢኮኖሚ ግን ሕዝባቸው ያልተንቀሳቀሰባቸው አገሮች አሉ፡፡ ዛሬ ኢኮኖሚውን ትተን በወታደራዊ አቅም ይጀመር ቢባልም አቅሙ የለም፡፡ በኢኮኖሚም ይጀመር ቢባል ተፅዕኖው ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ቀስ ብለው ሁለቱንም እያጠናከሩ የመሥራት ስትራቴጂን ተግባራዊ እንዳደረጉት ቻይናና መሰል አገሮች ካልተሄደ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡