
28 መስከረም 2022, 10:42 EAT
ተሻሽሏል ከ 20 ደቂቃዎች በፊት
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተወያዩ።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በተደረገው ምርጫ አብዱላሂ ፋርማጆን ተክተው የተመረጡት አዲሱ ፕሬዝዳንት ዛሬ ረቡዕ መስከረም 18/2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ነው አዲስ አበባ የገቡት።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በሌሎቹ የአካባቢው አገራት ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያም ይጓዛሉ ተብለው ሲጠበቁ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ያደረጉላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ እና ልዑካቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
መሪዎቹ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዳላቸው፣ በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋ አብሮ በመሥራት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠታቸው ተገልጿል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ በኩል ሶማሊያን ለመደገፍ ለተከፈለው መስዋዕትነት ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን እና ሁለቱ አገራት የጋራ ችግሮችን ለመፍታት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ኢትዮጵያ ከአዲሱ የሶማሊያ አስተዳደር ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን እና በተለይም ለኢኮኖሚ ዕድገት አጽንዖት ሰጥተው፣ ጠንካራ እና የተረጋጋች ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ጥንካሬ አስፈላጊ መሆኗን መናገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው ገልጿል።
- አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል?17 ግንቦት 2022
- የቻይና ገንዘብ ዋጋ ከዶላር አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ ከ 2 ሰአት በፊት
- ኢራን ውስጥ በሚካሄደው ተቃውሞ የሟቾች ቁጥር 76 መድረሱ ተነገረከ 4 ሰአት በፊት
ካልተረጋጋችው ሶማሊያ ጋር ረጅም ድንበር የምትጋራው ኢትዮጵያ የአገሪቱን መንግሥት በመደገፍ ታጣቂውን ቡድን አልሻባብን ለመዋጋት በአፍሪካ ኅብረት ሥር ወታደሮቿን በሶማሊያ ውስጥ ካሰማራች ዓመታት ተቆጥረዋል።
መሠረቱን ሶማሊያ ውስጥ ያደረገው ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው ታጣቂው አስላማዊ ቡድን አልሻባብ ከጥቂት ወራት በፊት ከሶማሊያ ድንበር ተሻግሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የኢትዮጵያ መንግሥት የቅርብ ወዳጅ የሆኑትን ሥልጣን ላይ የነበሩትን አብዱላሂ ፋርማጆን በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አሜሪካንን ጨምሮ ለጉብኝት ወደ ተለያዩ አገራት አቅንተዋል።
በተለይም ጎረቤቶቻቸውን ኬንያን እና ጂቡቲን የጎበኙ ሲሆን፣ ከዚያ ባሻገርም ወደ ኤርትራ እና ግብፅ በማቅናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በወቅቱ በኢትዮጵያም ጉብኝት የማድረግ ፍላጎት እንደነበራቸው የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ ሠራዊቱን ከማሰማራት ባሻገር የአገሪቱ መንግሥት ከአልሻባብ ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ ዋነኛ አጋር ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ቆይቷል።
በተለይም አልሻባብ ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች እና ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ሠራዊት መገደላቸውና መማረካቸውን መንግሥት አሳውቆ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በድንበር አካባቢ ያለው የደኅንነት ጥበቃ ለማጠናከር ከአዋሳኝ የሶማሊያ አካባቢ አመራሮች ጋር ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።