

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ
ዜና በማኅበረሰቦችና በክልል መዋቅሮች ውስጥ ያለው አለመተማመን የክልልነት ጥያቄዎች እንዲበራከቱ ማድረጉ ተገለጸ
ቀን: October 2, 2022
በማኅበረሰቦችና በክልል የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ያለው አለመተማመን ለክልል፣ ለዞንና ለልዩ ወረዳ ጥያቄዎች መበራከት አንደኛው ገፊ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡
በተለይ ከሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያሉ አለመተማመኖች ‹‹የሌላውን ከተማ ለምን እናለማለን›› የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩን፣ ይህም በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ በተነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች ውስጥ መንፀባረቁን ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ጥናት አመላክቷል፡፡
ከደቡብ ክልል ወጥቶ ኅብረ ብሔራዊ ክልል ሆኖ የተደራጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም፣ በክላስተር በመደራጀት የክልልነት ሒደት ላይ ያሉ ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎችም ይህንን የመተማመን ችግር መቅረፍ ካልቻሉ፣ እንደ ደቡብ ክልል ዓይነት ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው እንደሚችል በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በተለይ ከሲዳማ ክልል መመሥረት በኋላ ገፍቶ የመጣውን የክልልነት ጥያቄ፣ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄነት በተለየ የተመለከተው ሐሳብ የተነሳው፣ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የመዋቅር ጥያቄዎችን አስመልክቶ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው፡፡
ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው በዚህ መድረክ፣ የቀድሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በደቡብ ክልል የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት ላይ የተሳተፉት የሶሻል አንትሮፖሎጂስቱ ገብሬ ይንቲሶ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹አለመተማመንና የመዋቅር ጥያቄ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ክልልን አስመልክቶ በተጠናው ጥናት ብዙዎቹ የመዋቅር ጥያቄዎች የተነሱት፣ በመዋቅሮቹ ውስጥ በታዩት አድሏዊነትና ኢፍትሐዊነት፣ የሕግ የበላይነት አለመረጋገጥ፣ የደኅንነት ሥጋት፣ ቡድንተኝነትና የጥቅም ትስስር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ድክመት፣ የመሠረተ ልማት እጥረትና የፖለቲካ ልሂቃን ቅስቀሳ ምክንያት እንደሆነ ገብሬ (ፕሮፌሰር) አስታውሰዋል፡፡
የበጀት አጠቃቀም፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና የትልልቅ ፕሮጀክቶች ሥርጭት ፍትሐዊ እንዳልነበረ ጥናቱ ማሳየቱን የጠቀሱት ጽሑፍ አቅራቢው፣ ከሐዋሳ ከተማ በስተቀር ሌሎች ከተሞች እንዲያድጉ ክልሉ አለመደገፉ በቀድሞው የደቡብ ክልል ላይ እምነት ካሳጡት ምክንያቶች ውስጥ እንደሚጠቀስ አስረድተዋል፡፡
በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ባሉ የሥልጣን ውክልና ቦታዎች ላይ ከተወሰኑ ቡድኖችና አካባቢዎች የመጡ ባለሥልጣናት እየተፈራረቁ ሥልጣን የሚይዙበት፣ ታች ያሉ የአስተዳደር መዋቅሮች በክልሉ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ማድረጉንም በምሳሌነት አውስተዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃቶች ሲፈጸሙ ክልሉ ቀድሞ ደርሶ ሕዝቡን ከመታደግ አኳያ ዳተኝነት መታየቱ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጭምር የፈጸሙ አመራሮች መጠየቅ ሲገባቸው ቡድናዊ ከለላ እየተደረገላቸው በሥልጣን ላይ መቆየታቸው፣ ከኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ባሻገር መተማመንን የሸረሸሩ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ገብሬ (ፕሮፌሰር) በጽሑፋቸው፣ ‹‹በአጠቃላይ በደቡብ ክልል የሚነሱት ክልል የመሆን ጥያቄዎች በዋናነት በነባሩ አደረጃጀት ላይ እምነት በማጣት ነበር፤›› የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተፈጠረውን መተማመን በመሸርሸር ‹የራሳችንን ክልል ከመሠረትን ችግሮቹን መፍታት እንችላለን› ወደ የሚል ሐሳብ ማደጉን፣ እንዲሁም ይህንንም የሚደግፍ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩና አጀንዳውን በቀላሉ ሕዝባዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑ የክልልነት ጥያቄዎችን እንዲበራከቱ ምክንያት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ጽሑፍ አቅራቢው ገለጻ፣ መዋቅሮች የክልልነት ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውና ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም፣ ጥያቄውን ላቀረበው መዋቅር ሁሉ ፈቃድ መስጠት በራሱ የሚያስከትላቸው የራሱ ሥጋቶች አሉት፡፡ ለልማት መዋል የነበረበት ሀብት ለመዋቅር ዝርጋታ የሚውል መሆኑንና አዲስ ክልል በተመሠረተ ቁጥር ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የድጎማ በጀት የሚያገኙት ድርሻ እየቀነሰ የሚመጣ መሆኑን በምሳሌነት አስረድተዋል፡፡
በዚህም ሳቢያ መተማመንን በማስፈን ለመዋቅር ጥያቄ ምክንያት የሚሆኑ መንስዔዎች ማስወገድን ቀዳሚው መፍትሔ አድርገው ያቀረቡት ገብሬ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹አዲስ የአስተዳደር መዋቅር በማምጣት የተፈለገው ዓላማ በነባሩ መዋቅር የሚሳካ ከሆነ፣ የአደረጃጀት ጥያቄ ሕዝባዊ አጀንዳ የሚሆንበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፤›› የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
ይሁንና ነባሩ መዋቅር በሕዝቦች ማኅበራዊ መሠረት ውስብስብነትም ሆነ በራሱ የአደረጃጀት ቁመና የመልማት ጥያቄዎችን መመለስ የማይችል ከሆነ፣ የመዋቅር ጥያቄውን መፍቀድ ግድ እንደሚል በጽሑፋቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹አዲሶቹ ኅብረ ብሔራዊ ክልሎችም ሆኑ ሌሎች መሰል የአስተዳደር መዋቅሮች፣ ከቀድሞ የደቡብ ክልል ስህተት በመማር መተማመንን በሁሉም መግለጫው ማስፈን ካልቻለ፣ አለመተማመን በተገላቢጦሹ ይሰፍንና የመበታተን አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል፤›› የሚል ሥጋት በገብሬ (ፕሮፌሰር) ጽሑፍ ማጠቃለያ ላይ ቀርቧል፡፡
በውይይቱ ላይ ሌላውን ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር አስናቀ ከፋ (ዶ/ር)፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ባከበረ መንገድ የፌዴራል ሥርዓቱን የአደረጃጀት መርሆዎች መከለስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ትልልቅ ክልሎችን በመከፋፈል የክልሎችን ቁጥር ማብዛትና ፖለቲካው ውስጥ ከብሔረሰብ ያለፈ ኅብረት እንዲፈጠር የሚረዱ የምርጫና የመንግሥት መዋቅሮችን መቀየስ፣ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ እንደሚረዳ አስናቀ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ይሁንና የክልልነት ጥያቄዎች በሚነሱበት ጊዜ ጉዳዩን የጥያቄ አቅራቢው ብቻ የሚያደርገው አሠራር ተቀይሮ፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሒደቱን ከማሳለጥ በዘለለ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደማይገባ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ልዩ ወረዳዎች የሚቋቋሙባቸውን መሥፈርቶች ማውጣት ተገቢ መሆኑን በጽሑፋቸው አሥፍረዋል፡፡