
ከ 2 ሰአት በፊት
የትግራይ ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩት የአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ።
በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተነበበው የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ መግለጫ ውሳኔው የተደረሰው በመሬት ላይ ያለውን አሁናዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጥምር ኃይልን “በአስተማማኝ መልኩ ለመከላከል የቦታ እና የአቅጣጫ ማሻሻያ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ብሏል።
ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።
ከሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ወጥተው የቦታ ማሻሻያ እንዳደረጉና ላለፉት ሦስት ቀናትም የትግራይ ኃይሎች ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
ከጦርነት ውጪ በራሳቸው ውሳኔ እንደወጡ ገልጸው “በዚሁ ግንባር ተመሳሳይ ጥቃት የሚከፈት ከሆነ ለህልውናችን ስንል ተመልሰን ልንገባ እንችላለን” ብለዋል።
የአምስት ወራት የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ነሐሴ 21/2014 ዓ.ም. ከቆቦ ለቆ መውጣቱን አስታውቆ ነበር።
በወቅቱም መከላከያ “የሕዝብን ፍጅት” ለማስወገድ ሲባል ከሰሜን ወሎዋ የቆቦ ከተማን ለቅቄ ወጥቻለሁ ማለቱ ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው በወቅቱ “የተከፈተባቸውን ጥቃት ለመከላከል በተደረገ የፀረ- ማጥቃት ዘመቻ” ስፍራዎቹን ተቆጣጥረናል ብለው ነበር።
የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረናቸዋል ያሏቸው አካባቢዎች የቆቦን ከተማን ጨምሮ ጉጉውዶ፣ ፎኪሳ፣ ዞብል፣ መንደፈራ፣ ሮቢት፣ ሽዎች ማርያምና ተኩለሽ የሚባሉ ስፍራዎች ናቸው።
- በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር አካባቢ በርካታ ጦር መከማቸቱን የሳተላይት ምስሎች አሳዩ29 መስከረም 2022
- ‘የትግራይ ኃይሎች በቆቦ የቤት ለቤት ፍተሻ አድርገው ነበር’ ነዋሪ29 ነሐሴ 2022
- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የቆቦ ከተማን ለቅቆ መውጣቱ ተገለጸ28 ነሐሴ 2022
ጦርነቱን በመጀመር አንደኛው ሌላኛውን ወገን የሚከስ ሲሆን የትግራይ ኃይሎች በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ በቆቦ በኩል “ጥቃት የተከፈተው መቀለን ለመቆጣጠር ያለመ ነበር” ብለዋል።
“የአማራ መሬትን ለመያዝም ሆነ መሬቱን የውጊያ ማዕከል የማድረግ እቅድ አልነበረንም” ያለው መግለጫው “እንደ ሕዝብ ህልውና ለማረጋገጥ በፀረ ማጥቃት ተገደን የገባንበትና የጥምር ኃይሉን በማዳከም ወደ ሰላምና ድርድር ለማምጣት ነው” ብሏል።
በባለፉት ሳምንታት ከሳተላይት የተነሱት ምስሎች ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት ክምችት እና መሳሪያዎች የተጠመዱባቸውን ቦታዎች አሳይተዋል።
ከሰሞኑ ኤርትራ ተጠባባቂ ጦሯን ለክተት በማዝመት ትግራይ ውስጥ ጥቃት መፈጸሟ ሪፖርት ተደርጓል።
በነሐሴ ወር ለአምስት ወራት ያህል የዘለቀው የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ ጦርነቱ አገርሽቶ ውጊያው በተለያዩ ግንባሮች ቀጥሏል።
ባለፉት ወራት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሲደረግ የነበረው የሰላም ጥረት ውጤት ሳያመጣ ቀርቶ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ጦርነቱ ቆሞ ድርድር እንዲጀመር ጥሪ ሲያርቡ ቆይተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት 13 ሚሊዮን የሚገመቱ ነዋሪዎችን እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።