ካርታ

ከ 6 ሰአት በፊት

በኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በተፈፀሙ ተከታታይ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ጥቃቱን ሸሽተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው የሄዱ የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ጥቃቱን ሸሽተው ወደ አማራ ክልል የሄዱ እና እዚያው ወለጋ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች እንደተናገሩት ጥቃቱ ከተጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 16/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ፣ በሆሮ ቡልቅ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ከነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

ኮሚሽኑ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ተጠያቂ ናቸው በማለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን (ኦነግ-ሸኔ)፣ የአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎችን እና ግለሰቦችን ጠቅሷል።

ጨምሮም የታጠቁ ቡድኖች በሲቪሎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ አሳስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ጥቃቶቹ ተስፋፍተው መቀጠላቸው እንዳሰሰበው መግለጹ ይታወሳል።

ጥቃቶች ከሚፈጸሙባቸው ከወለጋ አካባቢዎች ሸሽተው ወደ አማራ ክልል የገቡ ከጥቃቱ የተረፉ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ ተገድለዋል ብለዋል።

በተለይም ሐሙስ መስከረም 12/2015 ዓ.ም ንጋት 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በተፈፀመ አዲስ ጥቃት ቁጥራቸውን በውል የማያውቋቸው በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።  

እነዚህ የዐይን እማኞቹ እንደሚሉት ጥቃቱን የፈፀመው ታጣቂ ቡድኑ “ኦነግ ሸኔ” እንደሆነ ገልጸው፣ ጥቃቱም  “ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው” ብለዋል።

የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርትም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ በጃርደጋ ጃርቴ እና አሙር ወረዳዎች በፈፀመው መጠነ ሰፊ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል ብሏል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂው ቡድን በዞኑ ውስጥ “በንጹሃን ዜጎች እና በአካባቢው የሚሊሻ አባላት ላይ ግድያን ፈጽሟል” ሲል ቁጥራቸው ያልገለጻቸው ሰዎች መገደላቸውን አሳውቆ ነበር።

በአካባቢው ይንቀሳቀሳል የሚባለው መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን እንደማይፈጽም ሲያስተባብል ቆይቷል።

ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ጥቃቱን “የፋኖ ታጣቂዎች” ናቸው የፈጸሙት ሲሉ ነዋሪዎች ከሰዋል።

ቢቢሲ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ይህንን ጥቃት ያደረሰውን ታጣቂ ቡድን ማንነት ከነዋሪዎች ባሻገር ከተጨማሪ ምንጮች እና ከክልሉ ባለሥልጣናት ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከጥቃቱ የሸሹት ምን ይላሉ?

የአምስት ወር ጨቅላ ልጇን ጨምሮ ከሦስት ልጆቿ ጋር የተፈናቀለችው የጃርደጋ ጃርቴ ነዋሪዋ እናት፣ ሐሙስ መስከረም 12/ 2015 ዓ.ም. ንጋቱ 11፡00 ሰዓት በታጣቂዎቹ የተከፈተው ተኩስ እስከ ምሽቱ 1፡00 ድረስ እንደዘለቀ ትገልጻለች።

ከዚያም ለቀናት ተደብቀው ከቆዩ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት በአካባቢው በነበሩ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች እርዳታ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተናግራለች።

“አጋጣሚ እኛ ከላይ በኩል ስለነበርን የፌደራል ኃይሎች አካባቢውን ለቀው ሲወጡ ይዘውን ወጡ። ከተማ ውስጥ ያሉት የአማራ ብሔር ተወላጆች ግን አልተረፉም። በጥቆማ እና በቤት ለቤት አሰሳ ነው የተገደሉት” ብላለች።

ጃርደጋ ጃርቴን ለቀው ከወጡ በኋላም መስከረም 15/2015 ዓ.ም. አሙሩ ወረዳ ውስጥም ተመሳሳይ ጥቃት እንደነበርና እዚያ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ከእነርሱ ጋር በመሆን መሸሽ እንደቻሉ ተናግራለች።

ይህቺ እናት ከእነርሱ ተለይተው ወደ ኋላ የቀሩት ቤተሰቦቿ እንዳሳሰቧት እና ይሙቱ በሕይወት ይኑሩ እንደማታውቅም አክላለች።

በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ በቁጥር መግለጽ እንደሚከብዳት የተናገረችው ይህቺ እናት “ቤት ውስጥ ዘግተው የተቀመጡ ሰዎችም ጭምር ስለተገደሉ ቁጥሩ በርካታ ነው” ብላለች።

ሌላኛው የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ፣ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑና ከጥቃቱ የሸሹ ግለሰብም ከአንድ ዓመት በፊት በአካባቢውን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የተፈናቀሉት እናታቸው እስካሁን በሐይቅ ከተማ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ እርሳቸውም መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

እኝህ የዓይን እማኝ፣ ጥቃቱ በቤተክርስቲያን የተጠለሉት ላይ እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ እንደተፈፀመ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“ተኩሱ ሲከፈት ቤታችንን ከውጭ ቆልፈን ነበር የተቀመጥነው። በሩን ሲደበድቡ ቆይተው ሄዱ። ከዚያ ትንሽ እንደቆየን ሚሊሻዎች [የታጠቁ የአማራ ተወላጆች] ሲዋጉ ዋሉ። ከዚያም ሐሙስ ሌሊት 8፡00 ሰዓት ወጥተን የፌደራል ካምፕ ውስጥ ተጠለልን። የፌደራል ኃይሎችም እኛን አስጠልሎ ሲዋጋ ዋለ። ከዚያም ቅዳሜ ሌሊት ወደ አሙሩ ይዘውን ወጡ። አሙሩም በታጣቂዎች ተወርሮ ነበር” ብለዋል።

“ይህንን ዕድል ያላገኘው ሰው እና ጉዞው በእግር ስለነበር መራመድ ያልቻሉት አዛውንቶች መንገድ ላይ ቀሩ” ሲሉም እርሳቸው ከሌሎች ጋር በመሆን ለቀናት በእግራቸው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው አማራ ክልል፣ ቡሬ ከተማ መግባት መቻላቸውን ተናግረዋል።

“ከአካባቢው የመከላከያ ኃይል ሲነሳ ሸኔ አካባቢውን ወረረ” የሚሉት ግለሰቡ፣ ይህ ጥቃት የተፈፀመው ላሰማነው የድረሱልን ጥሪ ቀድሞ ምላሽ ስላልተሰጠንና የመውጣት ዕድሉን ስላላገኘን ነው ሲሉም ይወቅሳሉ።

የዐይን እማኙ ይኖሩበት በነበረው ቀበሌ ከ500 በላይ ሕዝብ እንደሚኖር ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑት ብቻ መውጣት እንደቻሉ እና እዚያው የቀሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን በአጎራባች ቦታ ከሚኖሩ ሰዎች መስማታቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ተወላጅ ታጣቂዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው እንደወጡ የገለጹ የአሙሩ ወረዳ ነዋሪዎችም በወረዳው በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች ሰላም የለም ይላሉ።

ያነጋገርናቸው የአሙሩ ነዋሪ “ጥቃቱ ሲፈፀም መጀመሪያ ወደ ወረዳው ሸሽን። ከዚያ ሲያባርሩን ደግሞ ወደ ጫካ ሸሽተናል። ከአሙሩ ወረዳ ዋስትና የሆነን አካል ለም። ወደፊትም ይኖራል ብለን አናስብም። ስጋት ውስጥ ነው ያለነው” ብለዋል።

በጥቃቱ ሰዎች መገደላቸውን፣ ትምህርት ቤት ሳይቀር ንብረት ላይ ዘረፋ እና ውድመት መድረሱንም ተናግረዋል።

“ሸኔን ታስታጥቃላችሁ፣ ትመግባላችሁ፣ ታስጠልላላችሁ እያሉ ይከሱናል። ሰላማዊ ሕዝብ ሲያጠቁ ሸኔን መታን ይላሉ። ፋኖዎቹ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን መሬት አለን ብላችሁ አትቀመጡ ከዚህ ሂዱ እያሉን ነው። አቤት ብንልም መልስ አላገኘንም” ብለዋል።

“ጭራሽ መሣሪያ ሰብስቦ እነሱን አስታጠቀ። ሕዝቡ ተጎድቻለሁ ቢል ሸኔን ከውስጣችሁ እስከምታወጡ ምንም ማድረግ አንችልም ይላል። እኛ ሸኔን እንደከብት ማሰር እንችላለን ወይ?” ሲሉም እኝሁ የዐይን እማኝ ይጠይቃሉ።

ሌላኛው የዐይን እማኝ በበኩላቸው በአካባቢው ያለው ቀውስ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየ ነው ይላሉ።

“ነዋሪው ከገዛ ቀየው እየተፈናቀለ፣ እየተዘረፈ፣ እየተገደለ እና ለሰው የማይገባ ነገር ነው እየተፈፀመበት ያለው። ነገሩ ለእኔም ሆነ ለሕዝቡ ግልጽ አይደለም። ሕዝቡ እኮ እርስ በርሱ ተጋብቷል። አሁን ይሄ ለምን መጣ? ነው ጥያቄው። ሸኔ ሕዝቡን ይዞ እያስቸገረ ነው ከተባለም እርምጃ መውሰድ ያለበት መንግሥት እንጂ ሌላ አካል አይደለም” ሲሉም መንግሥት ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

በአካባቢው ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ‘ፋኖ’ ስለመኖሩ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ጥቃቶች ሲፈፀሙ “የአማራ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች” በሚል ስማቸው አብሮ ይነሳል።

እዚያ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ግን በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ፋኖ እንደሌለ እና ራሳቸውን ለመከላከል በሚል መሣሪያ የታጠቁና መንግሥት የሚያውቃቸው በቁጥር ጥቂት ሚሊሻዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።

አላባራ ስላለው ጥቃት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምላሽ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባልደረባ አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኘው ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ ትክክለኛ ቁጥሩን ማወቅ ባይቻልም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አሙሩ ወረዳ ውስጥ 60 ሰዎች ተገድለው ነበር፣ ከዚያም ሀሮ ቡልቅ የሚባል አካባቢ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፅሟል። በቅርብ ጊዜም ሌሎች ጥቃቶች ተፈፅመዋል” ብለዋል።

በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በአካባቢው የሚገኙ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታጣቂዎች “ማንነትን መሠረት አድርገው” ጥቃት ስለመፈፀማቸው መረጃ እንደደረሳቸው አቶ ኢማድ አክለዋል።

አቶ ኢማድ ጨምረውም ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ መንግሥትም የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።

ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈፀማቸውን በመጥቀስ ኮሚሽናቸው መንግሥት ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብሎ ያምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ኢማድ፣ “ጥረቶች እንዳሉ እናምናለን። ነገር ግን የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች በመኖራቸው ክፍተቶች እንዳሉም እናምናለን። እነዚህ ክፍተቶች ለምን እንደተፈጠሩ በመገምገም ዜጎች ለእንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች እንዳይጋለጡ ችግሩን የሚመጥን እርምጃ እንዲወስድም እንመክራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ በተለያዩ ጊዜያት ያነጋገራቸው ከጥቃት የተረፉ፣ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እና ጥቃቱ ሲፈፀም በሥፍራው የነበሩ ሰዎች፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት ለታጣቂዎቹ ከለላ እንደሚሰጥ አለፍ ሲልም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በቅሬታ ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ባልደረባ አቶ ኢማድም ተመሳሳይ ክሶችን እንደሚሰሙ ገልጸው፣ “በተለይ በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሥፍራው ተገኝተን ጥናት አላደረግንም፤ ነገር ግን ጥረቶች እንዳሉ ሁሉ ክፍተቶች እንዳሉ እንረዳለን። ክፍተቶቹ ለምን ተፈጠሩ? የሚለውን መመለስ ያለበት ግን መንግሥት ነው” ብለዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

የአማራ ክልል ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን በቅርብ ጊዜ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን አረጋግጠው፤ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ እያሱ እንደሚሉት ከ30 ዓመታት በላይ ከኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃት ሸሽተው የተፈናቀሉት ሰዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተወስደው እንዲጠለሉ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈፀሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ሸሽተው በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የተጠለሉ ዜጎች ይገኛሉ።

ለእነዚህ ዜጎች በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነም በተደጋጋሚ ተገልጿል።

አቶ እያሱ፣ በቅርቡ ዳግም ያገረሸውን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከእርዳታ ድርጅቶችም ሆነ ከፌደራል መንግሥት የቀረበ እርዳታ ባላመኖሩ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ግቢ ዳሬክተር የሆኑት ዶክተር በየነ በላይ፣ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶችን ሸሽተው እንደመጡ የነገሯቸው ተፈናቃዮች በግቢው ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዶ/ር በየነ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ ከመስከረም 16/2015 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ወደ ግቢው መግባታቸውን እና እስከ መስከረም 18/2015 ዓ.ም ድረስ ተመዝግበው የገቡት 3 ሺህ 722 ሰዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቁጥሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱንና ግቢው በመጨናነቁ የዞን አመራሮች ሌላ ቦታ ያሳረፏቸውና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለው የሚገኙ መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በግቢው ውስጥ ከተጠለሉት ውስጥ “ሕጻናት፣ ሴቶች፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ ነፍሰጡሮች” እንደሚገኙበት የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ዩኒቨርሲቲው የ12 ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ ይህ መከሰቱ ፈተና እንደሆነባቸውም አክለዋል።

መጀመሪያ የመጡት ተፈናቃዮች ከጃርዳጋ ጃርቴ ወረዳ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር በየነ፣ ከዚያ በኋላ በተከታታይ በርካታ ሰዎች እየመጡ በመሆናቸው ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሳይስፋፋ እንዳልቀረ ግምታቸውን ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎች “የታጠቀ ኃይል እንዳፈናቀላቸው፣ ብዙ ሰው እንደሞተባቸው፣ የሞተውን ሰው እንኳን መቅበር እንዳልቻሉ፣ ንብረታቸው እንደወደመባቸው እና ከቤተሰብ አባላቶቻቸው ጋር እንደተጠፋፉ እንደነገሯቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ዳሬክተሩ እንደሚሉት እስካሁን ተፈናቃዮቹን እየተደገፉ ያሉት በዋናነት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እና የአካበቢው ማኅበረሰብ እየተደራጀ በሚያመጣው ምግብ ነው።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል።

የፌደራል መንግሥት፣ ለጥቃቱ ተጠያቂ ነው በሚለው እና ‘ኦነግ ሸኔ’ እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።

ይሁን እንጂ አሁንም ሕጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዳላባራ ነዋሪዎች ይናገራሉ።