አምባሳደር ማይክ ሐመር
የምስሉ መግለጫ,አምባሳደር ማይክ ሐመር

4 ጥቅምት 2022, 07:25 EAT

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት አብቅቶ ድርድር እንዲጀመር ድጋፍ ለማድረግ ወደ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ ጀመሩ።

ማይክ ሐመር ከሰኞ መስከረም 23 አስከ ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም ድረስ ከሁለት ሳምንት በላይ በሚቆየው ተልዕኳቸው ወደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የልዩ መልዕክተኝነት ሚናውን የተረከቡት አምባሳደር ማይክ ሐመር እስከ አሁን ድረስ ከሦስት ጊዜ በላይ ወደ ቀጠናው በመምጣት ሰላም እንዲወርድ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ተደርሶ ለአምስት ወራት ያህል የቆየው የተኩስ አቁም ተሰናክሎ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ልዩ መልዕክተኛው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከአስር ቀናት በላይ መቆታቸው ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አምባሳደር ሐመር ወደ አካባቢው የተመለሱት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ ንግግር እንዲጀመር ለማገዝ አሜሪካ እያደረገች ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል መሆኑን ገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ጦርነቱን በድርድር ለመቋጨት እንዲቻል የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን በመሰየም ረዘም ላለ ጊዜ ጥረት ቢያደርግም ውጤት ሳያሳይ ዘልቋል። በተለይ የትግራይ ኃይሎች በኅብረቱ እና በኦባሳንጆ ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት አሸማጋይነታቸውን ሳይቀበሉት ቆይተው ነበር።

ኋላ ላይ ግን የትግራይ አመራሮች የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትን በመቀበል ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ የሰላም ተስፋው ምንም አይነት እርምጃ ሳያሳይ ባለፈው ዓመትማብዊያ ላይ ጦርነቱ መልሶ አገርሽቷል።  

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ተመልሰው የመጡት ማይክ ሐመር በናይሮቢ በሚኖራቸው ቆይታ ከኬንያ ባለሥልጣናት፣ ከዓለም አቀፍ አጋሮች፣ በቀጠናው ሰላም እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት ከሚያደርጉ እና ሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሏል።

ሐመር ወደ አፍሪካ የተመለሱት ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ባለው ሁኔታ ላይ ዋሽንግተን ውስጥ በተደረገ ውይይት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ነው።

ልዩ መልዕክተኛው የኬንያ ቆይታቸውን ተከትሎ ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ በማቅናት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የሚደረገውን የሰላም ጥረት ለመደገፍ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

ሐመር ቀደም ሲል የነበራቸውን ጉዞ አጠናቀው ዋሽንግተን ላይ በሰጡት መግለጫ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጥረት ውስጥ ተጨማሪ አሸማጋዮች የሚካተቱበት ሁኔታን ማንሳታቸው ይታወሳል።

በዚህም ደቡብ አፍሪካዊቷ ታዋቂ ፖለቲከኛ እና የቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ድላሚኒ ዙማን ስም አንስተው ነበር። በጉዟቸውም ፖለቲከኛዋ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጥረትን በመደገፍ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ሊወያዩ እንደሚችሉ ይገመታል።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታም ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ እና ለድርቅ ተጎጂዎች ሰብአዊ እርዳትን ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር ይገናኛሉ ብሏል ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የወጣው መግለጫ።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በዚህ ጉዟቸው ለጦርነቱ መቋጫ ለማበጀት እና ብሔራዊ እርቅ ለማውረድ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ በሚኖር ተጠያቂነት ላይ አጽንኦት እንደሚሰጡና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይም ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኝበት ተገልጿል።

ከአንድ ወር በኋላ ሁለት ዓመት የሚሞላው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኝነት የሰየመቻቸው ሦስተኛው ዲፕሎማት የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ባለፉት አራት ወራት በአዲስ አበባ እና በመቀለ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ተገናኝተዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ጦርነት ፈርሶ በበርካታ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውጊያዎች ከተቀሰቀሱ በኋላ፣ የአሁኑ የማይክ ሐመር ጉዞ ሁለተኛው ነው።

አስካሁን የቀጠለው ጦርነት ማገርሸቱን ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጠይቀው፣ ውጥረቱን በማርገብ በተለይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደርስ ጥሪ ሲያርቡ ቆይተዋል።

ይህ ጦርነት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚታመን ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙ በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ቁሳዊ ውድመትን ባስከተለው በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።