የጅማ ቦሣ 04 ቀበሌ ታዳጊ ሕጻናት የኪነት ቡድን አባላት

ከ 5 ሰአት በፊት

ቡና አፍቃሪዎች ከቡናው መዓዛ እኩል የሚያስታውሱት ኅብረ ዝማሬ ነው።

ለአንዳንዶች፣ እንደ ትኩስ ወፍራም ቡና ከእንቅልፋቸው የሚያነቃ ዝማሬ ብቻ ሳይሆን የሰዓት መቁጠሪያቸውም ነበር።

በወቅቱ ዝነኛ የነበረው የኢትዮጵያ ሬድዮ ከ1970ዎቹ መጀመርያ አንስቶ ዘወትር ማለዳ ከዜና እወጃ ቀጥሎ ያስደምጠው ነበር።

                        “የኢኮሚ ዋልታ ቡና ቡና የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና፣

                          የእድገታችን ገንቢ ቡና ቡና፣ አውታር ነው  ቡናችን ቡና ቡና።

                           በዓለም ገበያ፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ላገር የሚያስገኘው ቡና ቡና፣

                           በጥራት በጣዕሙ ተደንቆ ተወዶ በጣም የታወቀው ቡና ቡና”

ይህ ጣፋጭ ዜማ በሕጻናት አንደበት ነበር የተቀነቀነው።

ሕጻናቱ ደግሞ የጅማ ከተማ ያበቀላቸው፣ በመምህር ታረቀኝ ወንድሙ የኪነጥበብ አድባር ውስጥ የተጠለሉ ነበሩ።

ይህ የሕጻናት የኪነት ቡድን የ’ጅማ ቦሣ አራት የኪነት ቡድን’ ይሰኛል።

ይህንን ግን ማን ያስታውሳል? ከዚያ ይልቅ “ቡና ቡና” የሚለው ቅጽል ስያሜያቸው ገናና ነው።

የጅማ ቦሣ አራት ምስረታ

የጅማ ቦሣ 04 ቀበሌ ታዳጊ ሕጻናት የኪነት ቡድን የተመሰረተው በ1970 ዓ.ም ነው።

በርግጥ ምልመላው የተካሄደው በ1969 መሆኑን መምህር ታረቀኝ ያስታውሳሉ።

የጅማ ቦሣ የኪነት ቡድን አባላት ከስማቸው እና ከዝናቸው ጋር ተጣብቆ የኖረውን ‘ቡና ቡና’ የሚለውን መዝሙር ብቻን አልተጫወቱም።

እንዲያውም ለመጀመሪያ ጊዜ የዘመሩት በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረውን ወታደራዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም የሚያወድሰውን “ለአብዮቴ” የተሰኘውን መዝሙር እንደሆነ አቶ ታረቀኝ ይጠቅሳሉ።

“ለአብዮቴ ለአብዮቴ 

ይፍሰስ ደሜ ይከስከስ አጥንቴ” እያለ ይፈስሳል መዝሙሩ።

ከዚህ በኋላ ይላሉ፣ አቶ ታረቀኝ ቡድኑ ከ60 በላይ መዝሙሮችን ተጫውቷል።

ሁሉም መዝሙሮች ግን አብዮታዊ አልነበሩም።

ልማት፣ ሴቶች፣ ሥነ ምግባር እና ወዘተርፈ ርዕሰ ጉዳዮቻቸው ነበሩ።

በርካቶቹ መዝሙሮችም በኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስቱድዮ ተቀርጸው ለሕዝብ መተላለፋቸውን ይናገራሉ።

የጅማ ኪነት ቡድን እንዴት ተመሰረተ?

መምህር ታረቀኝ ወንድሙ አስተማሪ ነበሩ።

የዘወትር ትጋታቸው በልጆች አእምሮ ውስጥ የእውቀት ዘር መዝራት ነበር።

የዕለት ሥራቸውን አከናውነው ሲያበቁ ትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሜዳ ሄደው ንፋስ ይቀበላሉ፤ እግራቸውንም ያፍታታሉ።

ሜዳው “ኪቶ ሜዳ” ይሰኛል።

ታድያ በ1969 ዓ.ም በዚህ ሜዳ ላይ ወታደራዊ ሰልፍ የሚለማመዱ ታዳጊዎችን ተመለከቱ።

ሰልፉን የሚለማመዱት መስከረም 2/1970 ዓ.ም ለሚከበረው የአብዮት በዓል ነበር።

መምህር ታረቀኝ ከወታደራዊ ሠልፉ በተጨማሪ መዝሙር ቢኖረው የሚል ሃሳብ ሽው አላቸው።

ይህንን ሃሳብ በወቅቱ ለነበሩት ካድሬዎች ሲያቀርቡ ተቀባይነት አገኘ።

ከዚያም በነሐሴ ወር 1969 ዓ.ም. እድሜያቸው ከ8 እስከ 15 የሚሆኑ 30 ሕጻናትን በመመልመል “ጅማ ቦሣ” የኪነት ቡድንን መሰረቱ።

15 ወንድ 15 ሴቶች ተመርጠው ሰላሳ መሙላታቸውን አባላቱ ያስታውሳሉ።

የኪነት ቡድኑ ጅማ 04 የሚለውን መጠሪያ ያገኘው አብዛኛዎቹ ሕጻናት ቀበሌ 04 የሚኖሩ በመሆናቸው ነው።

“ቦሣ” ደግሞ በወቅቱ በጅማ ካሉ 27 ቀበሌዎች መካከል የአንዱ መጠሪያ ነው።

ታድያ እነዚህ 30 ታዳጊዎችም “ለአብዮቴ ይፍሰስ ደሜ፣ ይከስከስ አጥንቴ” እያሉ መስከረም 2/1970 ዓ.ም. ለጅማ ሕዝብ ዘመሩ።

የጅማ ሕዝብ በተራው ሞቅ አድርጎ በአድናቆት አጨበጨበላቸው።

በወቅቱ ጅማ ከነበሯት ቀበሌዎች የመጡ 27 የኪነት ቡድኖችም ቀኑባቸው።

አቶ ታረቀኝ ይህ መዝሙር በጅማ ከተማ በሚገኙ በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መዘመሩን ያስታውሳሉ።

ከዚህ በኋላ ይህ የኪነት ቡድን ከጅማ ከተማ ወጥቶ በመላ አገሪቱ በመዘዋወር ሥራዎቹን ማቅረብ ጀመረ።

ቡድኑ የወቅቱን የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ርዕዮተ ዓለም የሚያንጸባርቁ በርካታ መዝሙሮችን  በየመድረኩ በማቅረብ ስሙ ገነነ።

የጅማ ቦሣ 04 ቀበሌ ታዳጊ ሕጻናት የኪነት ቡድን

“የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና”

በ‘አብዮቴ’ ጉሮሮውን ያሟሸው የኪነት ቡድን በየመድረኩ ግብዣ ይቀርብለት ጀመር።

ስብሰባዎች እና ኮንፍረንሶች ላይ ተገኝቶ አብዮታዊ እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ ይዘት ያላቸውን መዝሙሮችን ማቅረቡን ቀጠለ።

ታድያ በአንዱ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የቡናና እና ሻይ ባለሥልጣናት ተሳታፊ ነበሩ።

እናም ይህ የኪነት ቡድን ስለ ቡና መዝሙር ቢያዘጋጅ የሚል ሃሳብ አቀረቡ።

ይህንኑ ሃሳብ ለአቶ ታረቀኝ የወቅቱ የጅማ አስተዳዳሪ ጠርተው ነገሯቸው።

ይህ ጥያቄ እስኪቀርብ ድረስ መምህር ታረቀኝ ትኩስ ቡና ከመጠጣት በዘለለ፣ ስለቡና ምንም ዓይነት ሥራ ለማዘጋጀት አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ከዚያ በኋላ በጥያቄው መሠረት ግጥምና ዜማውን ሰርተው ማስጠናት ጀመሩ።

በ1971 ዓ.ም. የጅማ ቦሣ 04 ታዳጊ የሕጻናት የኪነት ቡድን ከቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ መዝሙሩ ተዘጋጀ።

ይህ የኪነት ቡድን መዝሙሩን መድረክ ላይ ካቀረበ በኋላ፣ እንደተለመደው አድናቆትን እና ተቀባይነትን አገኘ።

የአሁኑ ግን የተለየ አድናቆት ነበር።

መዝሙሩ በኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀርጾ ለዕለታዊ የቡና ዋጋ መግለጫ ማጀቢያ ሆኖ መቅረብ ጀመረ።

መምህር ታረቀኝ፣ ለ25 ዓመታት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ገበያ መግለጫን አጅቦ የኪነት ቡድኑ መዝሙር ማገልገሉን ይናገራሉ።

ይኹን አንጂ ባለሥልጣኑ ለዚህ መዝሙር ደራሲ ወይንም ለኪነት ቡድኑ አባላት ክፍያ አለመፈፀሙን በቅሬታ መልክ ያነሳሉ።

በእርግጥ በ2004 በአጋሮ ከተማ በተዘጋጀ የቡና ፌስቲቫል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በይፋ ስማቸውን ጠርተው አመስግነዋቸዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,የ“ጅማ ቦሣ አራት” [ቡና ቡና] ኪነት ቡድን

የኪነት ቡድኑ ሌሎች ሥራዎች

መምህር ታረቀኝ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና የሚለው ሥራቸው ይግነን እንጂ፣ ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አበርክተዋል።

ሥራቸው ልማትን፣ ጀግንነትን፣ አንድነትን፣ ንጽህናን፣ ጤናን፣ ትምሀርትን፣ ሰላምን እና የሴቶች መብትን ይሰብኩ እንደነበር ይናገራሉ።

ለአብዮቴ፣ ወደ ፊት እንሂድ፣ ጥቁር ዕንቁ፣ ለዓለም ሰላም፣ ድርብ ጭቆና፣ ጤንነት መብታችን፣ የተሰኙት እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ሥራዎች አሏቸው።

እንደ አቶ ታረቀኝ ገለፃ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መዝሙሮቻቸው በኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥ ተቀርፀዋል።

ወታደራዊው መንግሥት መውደቁን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሬድዮ የሚደመጠው “የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና” ብቻ ሆነ።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ታረቀኝ ሕብረተሰቡን ሊያስተምሩ የሚችሉ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የሌላቸው በርካታ መዝሙሮችን ሠርተዋል።

የጅማ ቦሣ 04 ታዳጊ ቡድን አባላት በብሔራዊ ቤተመንግሥት ኮሎኔል መንግሥቱ በተገኙበት በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተው ሥራቸውን አቅርበዋል።

በወቅቱ በጅማ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ሩሲያውያን እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ታረቀኝ፣ እርሳቸው በአማርኛ ከጻፏቸው አብዮታዊ ግጥሞች መካከል የተወሰኑትን በአገራቸው ቋንቋ ተርጉመው መውሰዳቸውንም ይናገራሉ። 

የኪነት ቡድኑ መፍረስ

መምህር ታረቀኝ ለኪነት ቡድናቸው ግጥምና ዜማ የሚሰሩት እርሳቸው እንደነበሩ ይናገራሉ።

ቡድናቸውም በሚያቀርባቸው ሥራዎች በጅማ ከተማ ከሚገኙ 27 የኪነት ቡድኖች ጋር ተወዳድሮ ያሸንፍ ነበር።

በሕብረ ዝማሬ አቀራረብም ከሌሎቹ ጎልቶ የሚታይ ተመልካችን ሳቢ እንደነበር አባላቱ ያስታውሳሉ።

“የቀበሌው ማኅበረሰብ እንደ ልጁ ነበር የሚያየን” የሚሉት አባላቱ “ጅማ ከተማ ላይ ዕንቁዎች ነበርን” ይላሉ።

የጅማ ቦሣ 04 ታዳጊ ሕጻናት ቡድን እስከ 1974 ዓ.ም. ድረስ ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል።

ከዚያ በኋላ ግን፣ በ1975 አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አኢወማ) ጋር እንዲቀላቀል ተደረገ።

ለምን እንደሆነም መምህር ታረቀኝ ሲያብራሩ፣ በዚያ ዓመት መምህር ታረቀኝ በሥራ ምክንያት ወደ ሶቭየት ኅብረት መጓዛቸው እና የኪነት ቡድኑ አባላት ከሕጻንነት እድሜ ስላለፉ ወደ ወጣቶች ቡድን እንዲቀላቀሉ ስለተወሰነ ነበር።

ይህ ግን ለቡድኑ የፈጠራ ሥራ ምቹ አልሆነም። ስለዚህም እንዲበተን ምክንያት ሆነ።

የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና ግን፣ በዘመኑ የሬዲዮ አድማጭ እና በቡና አፍቃሪያን ዘንድ ልብ ውስጥ ሁሉ አብሮ አለ ማለት ይቻላል።