October 11, 2022

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው ህዳር ወር ለማካሄድ ላቀደው ሀገር አቀፍ ምክክር ተሳታፊዎች የሚለዩበት እና አጀንዳዎች የሚመረጡበትን አካሄድ በተመለከተ ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማካሄድ ጀመረ። በትላንትናው ዕለት በተጀመረው እና ዛሬ በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ዙር የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት የታደሙት ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች እና የመንግስት ኃላፊዎች ናቸው።

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ካሉት 11 ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት ማህሙድ ድሪር፤ የውይይቱ ዓላማ በሀገር አቀፍ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች “ልየታ” “አካታች እና አሳታፊ” እንዲሆን፤ እንደዚሁም ሂደቱ “ሁሉም የተስማማበት እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአሁኑ ውይይቱ የምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች ተከታይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአዋጅ ከተቋቋመ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን ሀገራዊ ምክክር ለመጀመር ያቀረደው በመጪው ህዳር ወር አጋማሽ ነው። በኮሚሽኑ የ2015 ዕቅድ መሰረት፤ ከምክክሩ ተሳታፊዎች እና ከአጀንዳ ልየታ ጋር የተያያዙ አብዛኛዎቹ ስራዎች መጠናቀቅ የነበረባቸው እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ነበር።

በኮሚሽኑ ዕቅድ መሰረት፤ መግባባት በሚደረስበት የተሳታፊዎች መለያ መስፈርትና በሚዘረጋው የአሰራር ስርዓት መሰረት የሚመረጡት የማህብረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ብዛት 20 ሺህ ነው። እነዚህ የማህብረሰብ ክፍሎች ተወካዮች በሁለት ዙሮች እንዲለዩ ታቅዶ የነበረው ባለፉት ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ነበር። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ባለፈው ነሐሴ ወር ባካሄደው ውይይት ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ “የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምክክሩ የሚሳተፉት እንዴት ነው?” የሚል እንደነበር ኮሚሽነር ማህሙድ ድሪር አስታውሰዋል። የምክክር ኮሚሽኑ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በቀረበበት በዚሁ ውይይት፤ “የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች በምን መልኩ ነው የሚሳተፉት? አካታችነቱ ምን ያህል ነው?” የሚሉ ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተው እንደነበር ጠቅሰዋል።  

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎን በተመለከተ ኮሚሽነር ማህሙድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሲያብራሩ “ህዝብ የራሱን ተወካዮች መርጦ ነው ለምክክሩ እንዲሳተፉ የሚያደርገው። በህብረተሰባችን ደግሞ የሚገፉ የማህብረሰብ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ ፋቂ፣ ቀጥቃጭ እያልን ሙያዎችን እያናናቅን እንገፋቸዋለን። እነዚህ ሁሉ መሳተፍ ይኖርባቸዋል። የእኛም ትኩረት ይኸው ነው” ብለዋል። 

ትላንት እና ዛሬ በአዲስ አበባው ኃይሌ ግራንድ ሆቴል በተካሄደው ውይይት ላይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበትን አካሄድ በተመለከተ የግብዓት ማሰባሰብ ተካሄዷል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተመለከተቻቸው የውይይት ነጥቦች መካከል አንዱ ተሳታፊዎቹ በመጡባቸው አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አደረጃጀቶች እንዲያብራሩ ይጠይቃል። 

በሌላኛው የመወያያ ነጥብ ደግሞ፤ የውይይቱ ተሳታፊዎች “ከአቀማመጥ፣ አሰፋፈር እና አሰራር አንጻር በአንድ ላይ ሊሰባሰቡ የሚችሉ ወረዳዎች” ካሉ እንዲለዩ ጥያቄ ያቀርባል። ይህ ጥያቄ የቀረበው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ ወጪ ውይይቶችን ለማካሄድ እንዲያስችለው” በሚል መሆኑን በውይይቱ ከተሳተፉ የክልል ተወካዮች አንዱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ከመንግስት መዋቅር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማህብረሰብ የተውጣጡ ተወካዮች ጭምር በተሳተፉበት በሁለቱ ቀን ስብሰባ፤ ተሳታፊዎቹ በመጡባቸው አካባቢዎች መረጃዎችን ለማድረስ ተመራጭ ስለሆኑ መንገዶች ውይይት መደረጉ ተገልጿል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስብሰባዎችን ለመጥራት “ምን አይነት ምን መንገዶችን ቢጠቀም አዋጭ ነው?” ለሚለው ጥያቄም በተሳታፊዎች ግብረ መልስ ቀርቧል። 

ይህን መሰል ውይይት ከቀሪዎቹ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ጋር በቀጣይ ጊዜ እንደሚካሄድ ኮሚሽነር ማህሙድ ተናግረዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንደ ተሳታፊዎች ልየታ ሁሉ የአጀንዳ መረጣ ስለሚደረግበት ስርዓት ውይይቶች እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የአጀንዳ መረጣን በተመለከተ ስለሚከተለው አካሄድ ኮሚሽነር    ሲያብራሩ “እኛ አጀንዳ ይዘን ወደ ህዝቡ የምንቀርበብት አይደለም። ልሂቃን የሚያመጡት አጀንዳም አይደለም ህዝብ ራሱ በራሱ ‘እነዚህ ናቸው የእኔ አጀንዳዎች’ ብሎ ለይቶ ይሰጣል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው የምንመካከረው። በጣም ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች፤ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ አጀንዳዎች ይለያሉ። ይህንን ስልጣን አዋጁ የሰጠው ለኮሚሽኑ ነው” ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ያቋቋመው አዋጅ፤ ኮሚሽኑ “ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በህዝባዊ ውይይቶች ወይም በሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም ይለያል” ሲል ደንግጓል። ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን የመቅረጽ፣ አጀንዳዎቹ ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት እና ምክክሮችን እና ውይይቶችን የማሳለጥ ኃላፊነት እንዳለውም በአዋጁ ተቀምጧል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ ለአጀንዳ መረጣ እና ለተሳታፊዎች ልየታ ይረዳው ዘንድ በክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን እንደሚከፍት ኮሚሽነር ማህሙድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የምክክር ኮሚሽኑ በ2015 በጀት ዓመት 96 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የማቋቋም እቅድ እንዳለው በዓመታዊ እቅዱ ላይ ሰፍሯል። እነዚህ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ ይቋቋማሉ ቢባልም፤ እስካሁን ድረስ አንድም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አለመቋቋሙን የኮሚሽኑ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)