
6 ህዳር 2022
ለበርካታ አስርት ዓመታት በሙዚቃው ዘርፍ ታዋቂነትንና ተወዳጅነትን ያተረፈው አሊ መሐመድ ቢራ በ75 ዓመቱ ማረፉን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ገለጸ።
በኦሮሞ ሕዝብ የኪነ ጥበብ እድገት ውስጥ ትልቅ አሻራ ማሳረፉ የሚነገርለት ድምጻዊ አሊ ቢራ በርካታ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎችን አበርክቷል።
ግንቦት 1940 ዓ.ም. በድሬ ዳዋ ከተማ የተወለደው አሊ ቢራ፤ ባጋጠመው የጤና ችግር ምክንያት ባለፉት ሳምንታት የሕክምና ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል።
አርቲስት አሊ ቢራ ከዚህ ቀደምም የጤና እክል አጋጥሞት በአዲስ አበባ እና በአዳማ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና ሲከታተል ነበር።
አሊ ቢራ ከዚህ ቀደም የልብ እና የስኳር በሽታዎች ታማሚ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
- “ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው” አሊ ቢራ9 ሀምሌ 2019
- ሆስፒታል ከገባ 10 ቀናት የተቆጠሩት አሊ ቢራ ሕክምና እየተከታተለ መሆኑን ቤተሰቦቹ ገለፁ18 ጥቅምት 2022
- በሆስፒታል የሚገኘው አርቲስት አሊ ቢራ “እየተሻለኝ ነው” አለ23 መስከረም 2020
አሊ ቢራ ባለፉት 60 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ሥራዎች ውስጥ ከፍተኛ ስም እና ዝና አግኝቶ ቆይቷል። አሊ ለኦሮምኛ ቋንቋ የሙዚቃ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይነገራል።
አሊ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በተሻገረው የሙዚቃ ሕይወቱ ከ260 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወት ሲሆን፤ ለጥበብ አበርክቶውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።
አሊ ቢራ ከኦሮምኛ በተጨማሪ በአማርኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ተወዳጅነትን ያተረፉ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። የሙዚቃ ሥራዎቹ ቋንቋውን ከሚናገረው ሕብረተሰብ ባሻገርም እጅግ ተወዳጅነትን አግኝተዋል።
ሁለገቡ የሙዚቃ ሰው አሊ ቢራ ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ከመዝፈን በተጨማሪ ግጥምና ዜማዎችን በመፍጠር የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት የእራሱንና ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን አዳዲስ ሥራዎችን ማቅረቡ ይታወቃል።
የአሊ ቢራ ሙዚቃዎች ከእራሱ በተጨማሪ በርካታ ወጣትና አዳዲስ ዘፋኞች ተጫውተዋቸው ዝናን አግኝተውባቸዋል።
የአሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን እንዳለው የአሊ ቢራ ህልፈት በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ ደግሞ ለኦሮሞ ሕዝብ ከባድ ሐዘን ነው ብሏል።
ክልሉ እንዳለው ለአሊ ቢራ የሚመጥን “ለአንድ ጀግና መደረግ ያለበትን ሽኝት ለማድረግ” የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኮሚቴ አቋቁሞ አስፈላጊውን ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።