November 10, 2022 – BBC Amharic 

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ
የምስሉ መግለጫ,ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ (ፎቶ ከፋይል)

ከ 9 ሰአት በፊት

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከአገር እንዳልወጣ ከአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ተከለከልኩ አሉ።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም. ወደ እስራኤል አገር ለሕክምና እና ለጉብኝት ለመጓዝ ከተነሱ በኋላ ጉዞ ተከልክለው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጄኔራሉ የፓስፖርት ቁጥጥር የሚደረግበትን ስፍራ ካለፉ በኋላ ጉዞ ማድረግ እንደማይችሉ ስለተነገራቸው ወደ ቤታቸው ለመመለስ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ለክልከላው የተሰጣቸው ምክንያት “ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው” የሚል መሆኑን የገለጹት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፤ የጉዞ ክልከላው ምክንያት ምን እንደሆነ ለመጠየቅ ወደ ኢሚግሬሽን ከሄዱ በኋላ፤ “የበላይ አመራሮችን ጠይቀን ምላሽ እንሰጣለን” የሚል መልስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ጉዞ እንዳያደርጉ የተከለከሉት ከዚህ ቀደም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጉዳይ ጋር ስለመያያዙ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ግን አሁን ላይ ከአገር እንዳይወጡ የተከለከሉት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጉዳይ ጋር “የተያያዘ አይደለም” ብለዋል።

ከወራት በፊት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከአዲስ አበባ በደኅንነት ኃይሎች ተይዘው በሄሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር ከተማ ከተወሰዱ በኋላ “ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለመናድ መሞከር” በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ፖሊስ አስታውቆ ነበር።

ጉዳያቸው በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲታይ ከቆየ በኋላም በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ተወስኖ፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ መፈታታቸው ይታወሳል።

“በወቅቱ በዋስ ስወጣ በ15 ቀናት ክስ እንመሠርታልን ተብሎ ነበር። ነገር ግን በ15 ቀናት መክሰስ አልቻሉም። የአሁኑ ከአገር እንዳልወጣ የተደረገው ክልከላ ከዚያ ጋር የሚያያዝ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ የወንጀል ሕግ መሠረት በዋስትና መብት ከእስር የወጣ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ነጻ አስካልተባለ ድረስ ዐቃቤ ሕግ ክስ ሳይመሰረት ስለቀረበ ብቻ ነጻ ሊባል እንደማይችል ቢቢሲ ያነገራቸው የሕግ ባለሙያ ገልጸዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በአማራ ክልል ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

ከዚያም በኋላ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ የተከሰተውንና የክልሉ ርዕሰ ከፍተኛ አመራሮች የተገደሉበትን ክስተት ተከትሎ ለእስር ተዳርገው መለቀቃቸው ይታወሳል።

ጄኔራል ተፈራ በትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በተባባሰበት ጊዜ የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ ቆይተው፣ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ከዚሁ ኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በድርድር ለማብቃት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ንግግር ከመጀመሩ በፊት የአማራ ሕዝብ በእራሱ ተወካዮች ሊሳተፉ ይገባል በማለት ጥያቄ ባነሱ ወገኖች ከተጠቆሙት መካከል ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ አንዱ ናቸው።