የይስማዕከ ቁልቁለት በአራተኛ ‘ዴርቶጋዳ’ው
Wednesday, 03 September 2014 15:02
ርዕስ ዮራቶራድ
ደራሲ የሰማዕከ ወርቁ
የመፅሀፉ ዓይነት ረጅም ልብ ወለድ
ገፅ 208
ዋጋ 48.50
የመጽሃፉ ለንባብ የበቃበት ጊዜ ነሃሴ 2006
አስተያየት በመላዕክነሽ ማሞ
በአማርኛ ስነጽሁፍ አብይ የገጸባህሪያቱን ስረ መሰረት ሳይለቅ፣ የታሪኩን መነሻ ሳይስት በተከታታይ ቅጾች አንድ ልብ ወለድ መነበብ የጀመረው በ ብርሃኑ ዘርይሁን ይመስለኛል። ብርሃኑ ከ1972 እስከ 1975 [ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ፣ ማዕበል የአብዮት ፍጻሜ እያለ] ለንባብ ባበቃቸው ታሪክ ቀመስ ረጃጅም ልብ ወለዶች ለአንባብያን ያስተዋወቀው ይህ አይነት አጻጻፍ በ1987ዓ.ም ዋና መቼቱንና ማዕከላዊ ትኩረቱን የሃመር ማህበረሰብን በማድረግ ‘ከቡስካ በስተጀርባ‘ ሲል የመጣው ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ቀጣይ መጻህፍቱን ‘ኢቫንጋዲ’ና የ’ዘርሴዎች ፍቅር’ን በማድረግ ከብርሃኑ ቀጥሎ የአንድን ጉዳይ ተከታታይ ክፍሎች በሶስት መጻህፍት በማሳተም ሁለተኛ ሆኗል። ይህ ዓይነት አጻጻፍ በአማርኛ ልብ ወለድ ውስጥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲቀጥል ያደረገው በ 2001ዓ.ም ‘ዴርቶጋዳ’ በሚል ርዕስ አዲስ ቅርጽና ይዘት ያለው ድርሰት ያስነበበን ይስማዕከ ወርቁ ነው።
ይስማዕከ የዴርቶጋዳን ተከታይ ቅፆች ራማቶሃራ፣ ዣንቶዣራ፣ እያለ አሁን ዮራቶራድ ላይ ደርሷል።
በ2001 ዓ.ም የታተመው የይስማዕከ ዴርቶጋዳ የቋንቋውን የልብ ወለድ አንባብያን ማነሳሳቱ እሙን ነው። በስንት ሺህ ቅጂ እንደታተመ ባላውቅም [እራሱ ይስማዕከም ቁጥሩን በትክክል እንደማያውቀው ለብራና ሬዲዮ ተናግሯል] ተደጋግሞ ማተሚያ ቤት የገባ ልብወለድ ስለመሆኑ ለማወቅ ‘ይህን ያህልኛ እትም’ እየተባለ ወደ ገበያው የገባዉን ዴርቶጋዳ መቁጠር ይበቃል።
ምንም ይሁን ምንም ዴርቶጋዳን ይዞ መታየት የአንድ ሰሞን ፋሽን ሆኖ የነበረበትንና ዴርቶጋዳን አለማንበብም እንዳላዋቂነት የተቆጠረበትን ጊዜ ሁላችንም ታዝበንው ያለፍንው ጉዳይ ነው።
አንድ ደፋር አስተያየት ስጥ ብባል የምናገረው ነገር ይህ ነው።’በኢትዮጵያ ብዙ ሰው የሰማው የልብወለድ መጽሃፍ ፍቅር እስከ መቃብር’ [በሬድዮ ስለተተረከ] ሲሆን ብዙ ሰው ያነበበው ልብወልድ ደግሞ ዴርቶጋዳ ነው [ምን ያህሉ ገብቶት አንብቦታል ሌላ ጥያቄ ነው] መጽሃፉ ከመወደዱ የተነሳም ከይዘቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ጉዳዮች [እንደ ልብስ መሸጫ ቡቲክ ያሉ] በዴርቶጋዳ ሲሰየሙ አይተናል።
ይህ እንግዲህ መጽሃፉ በየደረጃው ባለው የህብረተሰብ ክፍል የነበረውን እውቅና ከሚያሳዩ ተራ [silly] ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ ነው።አሁን ጥያቄው ‘ይስማዕከ ከዚህ በሁዋላ የጻፋቸው ዴርቶጋዳዎች በመጀመሪያው ልክ የተቃኙ ናቸው ወይ?’ ከሚለው ላይ ነው።በዚህ ጽሁፍ የኔ ትኩረት አራተኛው ዴርቶጋዳ ዮራቶራድ ይሆናል። ልብ ወልዱን ከልብወለድ አላባውያን አንጻር እንየው።
1.ገጽባህሪ፡- ይስማዕከ በዚህኛው ልብ ወለዱ አዳዲስ ገጸባህሪያትን አካቷል [እንደ ዶን ቦናኖ ያሉ]። እነዚህ አዳዲስ አምሳለ ሰብዓት ለአዲስ አንባቢዎችም ሆነ ከዚህ በፊት የነበሩትን ቅፆች ላላነበቡ ለነባር አንባቢዎቹ ለውጥ የላቸው። ነባሮቹ የዴርቶጋዳ ባልደረቦች ግን ለአዳዲስ አንባብያን ይጎረብጣሉ። ደራሲው እነዚህ ሰዎቹን አያስተዋውቃቸውም።
ይስማዕከን ከዮራቶራድ ጀምሮ ማንበብ የጀመረ ተደራሲ ስለቀድሞ ገጸባህሪያት ትንሽ ገለጻ ካልተደረገለት በቀር ልቦለዱን ለመረዳት ይቸግረዋል። ባጭሩ ደራሲው ገጸባህሪያቱን በማስተዋወቅ በኩል ችግር አለበት።
ሌላው የይስማዕከ ገጸባህሪያትን የተለየ የሚያደርጋቸው የዋሻ ውስጥ ሰው መሆናቸው ነው። በብራዚል የአማዞን ጫካ ውስጥ የሚኖሩ 400 ያህል ጎሳዎች አሉ። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ሰዎች ላለፉት አምስት መቶ አመታት ከቀሪው ዓለም ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። ይህ ህዝብ ከቀሪው ዓለም ጋር ገበያም ሆነ ጋብቻ፣ ሃዘንም ሆነ ደስታ ባጠቃላይ በምንም ዓይነት ማህበራዊ ጋርዮሽ አይገናኝም።
እነዚህ ጎሳዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ርስበርስም ሆነ ከጫካው ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ እየተነገረ ባለበት በዚህ ዘመን የይስማዕከ ገጸባህሪያት ግን ዛሬም በዚያው በዳጋ ዋሻ ውስጥ ናቸው። ምግብና ልብስ አይሸምቱም፣ አይዝናኑም፣ እቁብ፣ እድር፣ ሃዘን፣ ደስታ፣ለነ ሜሮዳ፣ ሲጳራ፣ ወዘተ የማይታሰብ ነው።
2 መቼት፡- ሌላኛው የዚህ ልብወለድ [የዴርቶጋዳ ተከታታይ ቅጾችን በሙሉ ይመለከታል]። ትልቅ ድክመት ጊዜና ቦታን ያላገናዘበ መሆኑ ነው። የልብ ወለዶቹ ገጸባህሪያት የሚተዉኑት ታሪክ የዚህ ዘመን ሆነና፣ ገጸባህሪያቱ በአለም ላይ ያልተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ ሳይንሳዊና የወደፊት ፍጡራን ሆኑ።
ይህ ዓለም ሕገወጦችን የሚዳኝ ሕግና ሕግ አስከባሪ አለው፡፡ የትኛውም ወንጀለኛ ከሲአይ ኤ አምልጦ ስንት ውቅያኖስና ባህር አቋርጦ ዳጋ እሰጢፋኖስ ዋሻ ውስጥ መጥቶ የሚኖርበት መንገድ ቀላል አይሆንም፡፡ እንደ ዴር 33 ያሉ ፈጠራዎች ከራዳር እይታ ውጭ ሆነው የኢትዮጵያንም የሱዳንንም ሆነ የግብፅን የአየር ክልል በቀላሉ አልፈው አስቄጥስ በረሀ አይገቡም፡፡ እንደሚራዥ ያሉ በመንግሥት በጥብቅ የሚፈለጉ ወንጀለኞች ሁሌም አሸናፊ ሆነው እዛው ባህርዳር አፍንጫ ዋሻ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉበት ዘመን አይደለም -ይህ ዘመን፡፡
በአጠቃላይ ገፀባሕርያቱም ሆኑ ሥራቸውና የታጠቁት ቴክኖሎጂ ከዚህ ዘመን ጋር የማይሄድ ነው፡፡
በአጭሩ ገፀባሕርያቱ የአሁን፣ ሥራቸው የወደፊት ሆኖ መቅረቡ የልብወለዱን ተአማኒነት ያሳጣል፡፡
3/ ታሪክ፡- ታሪክ የልብወለድ መሠረታዊና ቀዳሚ ገፅታ እንደሆነ የዘርፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ አንድን ልብወለድ ያነበበ ሰው ምን አነበብክ ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ነው ታሪክ፡፡ ይህ ጥያቄ በይስማዕከ መፅሐፍ ላይ መልስ የለውም፡፡ እመኑኝ ዮራቶራድ ምንም ታሪክ አልያዘም፡፡ በአሰልቺና በተደጋጋሚ ገለፃዎች ግልብ ትንታኔዎችን በመስጠት የቆዩ የታሪክ ድርሳናትን በማተት ሁለት መቶ ስምንት ገፅ የሚሞላ ልብ ወለድ ነው፡፡ ደራሲው በሌሎች ‘ዴርቶጋዳ’ዎቹ ደጋግሞ የገለፀውን ሀሳብ ዮራቶራድ ገፅ 84 ላይ እንዲህ ሲል ደግሞታል፡፡
“ኢትዮጵያ የሰዎቿ ፊት ጠቁሯል፣ አንበሶቿ የሚበቃቸውን ነጥቀው አላበቁም ብሯንም፣ ወርቋንም ነጥቀው አላበቁም፡፡ እረኞቿ ለአረብ ግመል ጥበቃ ልጃገረዶቿ ለባዕዳን የጭን እቃ ሸጣለች፡፡”
ይህንን ሀሳብ ከገፅ 85 እስከ 86 እንዲህ ተደግሞ እናገኘዋለን፡፡
“የኛም አገር የሚታይ ቅጥሯ ፈራርሶ ታላላቆቿ ተሰደው ባዶዋን ቀርታለች፡፡”
ከገፅ 99 እስከ 1ዐዐ ከአሁን በፊት በነበሩት መፃሕፍቱ ደጋግሞ ያስነበበንን በዮራቶራድ እንዲህ ሲል ደግሞታል፡፡
“ቶሎ ቶሎ የያዛችሁትን ይዛችሁ ከኢትዮጵያ ብትወጡ ነው የሚሻላችሁ፡፡ ሕዝቡ እንደሆነ አንቅሮ ተፍቷችኋል፡፡ የሰራችሁትን ስህተት መቼም ቢሆን ይዘነጋዋል ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ በዘር ከፋፍላችሁታል፡፡ ሀገሩን ገንጥላችሁበታል፣ መደብ አሳጥታችሁታል፣ ዘሪያውን በጠላት አስከብባችሁታል፡፡”
ይህንን ሙሉ ሀሳብ በሌላ አገላለፅ ገፅ 134 እንዲህ ሲል ያስነብበናል፡፡
“ሠራተኛው ተስፋቢስና አብሮ መሥራት የማይችልና የዘር አንዘርዝር አናቱ ላይ ወጥቶበት አጥንት ቆጠራ ገብቷል፡፡”
ዮራቶራድ ገፅ 189 ላይ ይህ አረፍተ ነገር እንዲህ ተደግሟል፡፡
“በአሁኑ ጊዜ ግን በማይረባ ስብከት በጎሳና በጎጥ የተለያየውን ኢትዮጵያዊ በአንድነት ከወደቀችበት ለማንሳት ካለን ሕልም በመነሳት ነው፡፡”
ይህ ነው እንግዲህ የ ይስማዕከ ዮራቶራድ ታሪክ። በገሃዱ ዓለም የሰለቸንን ተደጋጋሚ ሃሳብ በልብ ወለድ መደጋገም። ባጠቃላይ አንድ ሰው ይህንን መጽሃፍ አንብቦ ቅደም ተከተሉን ባልሳተ ሁኔታ ይህንን አነበብኩ ብሎ የሚያወራው ታሪክ የለውም ባይ ነኝ።
4 ጭብጥ፡- የልብወለድ ጭብጥ ከታሪኩ ይመነጫል። ልብ ወለዱ ታሪክ ከሌለው የሚተላለፍ መልዕክት የለውም ማለት ነው። ዮራቶራድ እንደረጅም ልብወለድ ከአብይ ጭብጡ ጋር የሚሰናሰሉ ንዑስ ጭብጦች ሊኖሩት ይገባ ነበር። በዚህ መፅሃፍ ሊተላለፍ የተፈለገው ማዕከላዊ መልዕክት ምን እንደሆነ እንኳን አንባቢው እራሱ ደራሲውም የሚያውቀው አይመስለኝም። በቃ ከላይ በተራ ቁጥር3 ስር የገለጽኳቸውን ሃሳቦች ደጋግሞ ከማስተጋባት በዘለለ ምንም መልዕክት ያለው መስሎ አልታየኝም። ከላይ የተገለጹት ተደጋጋሚ ሃሳቦች ዋናውን ጭብጥ ለመደገፍ የገቡ ናቸው ቢባል እንኳ የነዚህን ንዑሳን ጭብጦች የሚመራ አውራ ጭብጥ አይገኝበትም-ልብወለዱ። የፖለቲካ ስርዓቱን፣ የማህበረሰቡን እሴትና መሰል የዘመኑን ሁኔታዎች የሚተች ልብ ወለድ ነው እንዳይባልም ጉዳዩ በተገቢው ሽፋን ተሰጥቶት አልተተረከም።
የቋንቋ አጠቃቀም ስህተት
ሌላኛው የዮራቶራድ ድክመት ነው። ይስማዕከ ከዚህ በፊት በጻፋቸው ልብ ወለዶቹ [በተለይ በዴርቶጋዳ] ከተመሰገነባቸው ነጥቦች አንዱ የማይጎረብጥ ቋንቋ መጠቀሙ ነው። በዮራቶራድ ግን ግዴለሽ ሆኖ [አንባቢን ንቆ] መጥቷል።
ለምሳሌ በግዕዝና በአማርኛ እየደራረብ የሚያበዛቸው ቃላት ብዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ነገስታቶች፣ ቃላቶች፣ አባላቶች፣ መጽሃፍቶች፣ ቅርጻቅርጾች፣ ወዘተ [ከገጽ60-153] ይጠቀሳሉ።
እነዚህን ቃላት በአማርኛ ድርሰት ውስጥ በሁለቱም ቋንቋ እያበዙ መጠቀም ህገወጥ መሆኑን የማያውቁ ሰዎች ቢያደርጉት ላይገርም ይችላል። ይስማዕከ ግን ስህተት እንደሆነ በደንብ ያውቃል [ምናልባት እኛን አንባቢዎቹን ካልናቀና አለያም ግዴለሽ ሆኖ የይድረስ ይድረስ ጽፎ ካላሳተመው በቀር]። ነገስታት፣ ቃላት፣ አባላት፣….. የመሳሰሉት ቀድመው በግዕዝ በዝተዋል። ነገስታቶች፣ ቃላቶች፣ መጽሃፍቶች፣……. የሚባሉ ቃላት በአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ የሉም። እርግጠኛ ነኝ የግዕዝ መዝገበ ቃላትም አያውቃቸውም። “ቅርጻቅርጾች” የሚለውም በግዕዝና በአማርኛ ተደጋግሞ በዝቷል፤ቅርጽ በአማርኛ ሲበዛ ቅርጻቅርጽ ተብሎ ነው፤ ቅርጻቅርጾች በቋንቋው ገበታ ላይ የለም። ይስማዕክ ግን ይህን ሁሉ ከነስህተቱ ጽፎታል።
በአጠቃላይ ይስማዕከ በዚህ መጽሃፉ ከቁልቁለት ጫፍ ላይ ደርሷል። ለወትሮው ይስማዕከን በተመለከት አንድ የምከራከርበት አቋም ነበረኝ። ’ከዴርቶጋዳ በሁዋላ ወርዷል’ የሚሉ ሰዎችን ለምን በሱ ዘመን ካሉ ደራሲዎች አንጻር አናየውም፤ ለምን ከራሱ ስራዎች ጋር እናነጻጽረዋለን በማለት እሞግታቸው ነበር። ይህንን የማደርገው አንድም በእርሱ ዘመን የእሱን ስራዎች የሚፎካከር ድርሰት አለ ብዬ ስለማላምን [ስህተት ሊሆን ይችላል] ሁለትም ማንኛውም ሰው ሁሌም ተመሳሳይ ስራዎችን ይሰራል ብዬ ስለማላምን ነው።
አሁን ግን የዚህ ወጣት ደራሲ አቅም የተሟጠጠ ይመስለኛል። ወይም ለአንባብያን ክብር ነፍጓል። በዚህ የተነሳም የቁልቁለት ጫፍ ላይ ተቀምጧል። ምክንያቱም ጭብጥ የሌለው መጽሃፍ ማሳተም ጀምሯልና!
የይስማዕከ የቁልቁለት ሩጫ ለምን ፈጠነ?
በኔ እምነት የይስማዕከ የመፍጠር አቅሙ ለማሽቆልቆሉ ዋነኛ ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤
1. ተደጋግሞ እንደተባለው ይህ ወጣት ደራሲ ባለሙያዎችን ንቋል። በመጀመሪያ ግጥሙ [የወንድ ምጥ] በአማርኛ ሥነጽሁፍ ውስጥ ሚና ያላቸውን [እንደ የሻው ተሰማ፣ ፍቅረማርቆስ ደስታ፣ የመሳሰሉ ሰዎችን] አሳትፏል። በስራው ላይ ድርሻ ባይኖራቸው ኖሮ ቢያንስ ምስጋና ላይ አያካትታቸውም ነበር።
ዴርቶጋዳ የተባለ ረጅም ልብወለድም ተደራሲያዊ ቅቡልነት እንዲኖረው ከስብሃት ገብረእግዚአብሔር እስከዮፍታሄ ሥዩም [ዶ/ር] ከየሻው ተሰማ እስከ በዕዉቀቱ ሥዩም፣ ከእንዳለጌታ ከበደ እስከ ሌሎች ትላልቅ ሰዎች ድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው ለማወቅ እሱ በምስጋና ገጹ ላይ ያሰፈረዉን ማየት፣ የሰዎቹንም አስተያየት ማንበብ ይበቃል።
ይህ ደራሲ ከዚህ በሁዋላ ጽሁፎቹን ለባለሙያ ለማሳየት ውርደት የሆነበት ያህል ተወው። ይባስ ብሎ በአንድ መጽሃፉ መግለቢያ ላይ [ተልሚድ] ‘ያገኘኝ ሁሉ እንደ እርጥብ ጭቃ ጠፍጥፎ እንዲሰራኝ የምፈቅድ አይደለሁም’ ብሎ ከመዳፈሩም ሌላ ምንም ላልተጻፈባቸው ገጾች ምስጋና ማቅረብ ጀመረ።
ይስማዕከ ከላይ የጠቀስኳቸው የመጀመሪያ መጻህፍቱን ለታላላቅ ሰዎች ያሳየው በአንባብያን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ለማሻሻጫነት ነው የሚል ድፍረት እኔም ለማስፈር እገደዳለሁ። ምክንያቱም ይህ መልካም ነገር ለሥራ ጥራት የታሰበ ቢሆን ኖሮ ይቀጥል ነበር ብዬ ስለማምን ነው።ግን ደራሲው ባለሙያ ንቋል።
2. ከማህበረሰቡ የሚሰነዘሩ የሆይሆይታ አድናቆቶችን ካልሆነ በቀር ከባለሙያዎች የሚመጡ አስተያየቶችን በክፉ አይን ማየት ጀምሯል- ይስማዕከ። እዚህ ጋር እሱ እንደሚለው ‘ሥራዎቹን ጭቃ ለመቀባት’ የሚታትሩ የሉም -እያልኩ አይደለም። ዋናው ነገር የሚሰጡ ሙያዊ ትችቶችን በበጎ ዓይን ማየት አለመፈለጉ ለማሽቆልቆሉ ምክንያት ሆኗል የሚለው ይሰመርልኝ።
3 ክረምት በመጣ ቁጥር መጽሃፍ ለማሳተም የሚያደርገው መጣደፍ ስራው ‘ኩሽማንኩሽ’ እየሆነ እንዲመጣ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። በርግጥ በክረምት ወራት በርካቶች ጊዜ ሲለሚያገኙ ለገበያ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይችን አጋጣሚ ለመጠቀም በሚል በሩጫ ረጅም ልብወለድ መጻፍና ማሳተም ዋጋ ያስከፍላል። [ራማቶሃራ ክረምት2002፣ ዣንቶዣራ ክረምት 2004፣ ዮራቶራድ ክረምት 2006፣ ተልሚድ ክረምት2003 ላይ መጻፋቸውን ልብ ይሏል]። ይህ ደግሞ በአንደኛው መጽሃፉ ላይ የተሰጠውን አስተያየት እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ወደ ቀጣዩ ሥራ ለመግባት ጊዜ እንዲያጣ ያደርገዋል። ይህም በዴርቶጋዳ በታዋቂ ሰዎች ተንጠላጥሎ ባገኘው ስምና ዝና እየነገደ ነው ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል።
4. የዘመኑን ማህበረሰብ እሴቶች በማጣጣል፣ የኢትዮጵያን ታሪኮች በማጉላትና ፖለቲካዊ ትኩሳቶችን በመተቸት አንባብያዊ ተቀባይነት አገኛለሁ የሚል ከንቱ እሳቤ ያለው ይመስለኛል-ይስማዕከ። በርግጥ እነዚህ ሁሉ የገሃዱ አለም እውነታዎች በመሆናቸው ደራሲውም ከነዚህ ነጸብራቆች እንዲወጣ አይገደድም። ይሁን እንጂ በአራት መጻሃፍት ላይ አንድን ጉዳይ በተመሳሳይ ገለጻ ሲያመጣው ይሰለቻል።
ባጠቃላይ ይስማዕከ ከስሙ ይልቅ ለሥነጽሁፋዊ ችሎታው ከስሜቱ ይልቅ ለእዉቀቱ መገዛት ሲጀምር፣ ከገንዘብ ይልቅ የድርሰት ፍቅሩን ሲያስቀድም ወደነበረበት ዙፋን ይመለሳል።
ማስታወሻ ይስማዕከ በሥራዎቹ ላይ መረር ያሉ አስተያየቶችን የሚሰጡ አስተያየቶችን ‘ከሌላ ፍላጎት በመነጨ ሥራዎቼን ጭቃ ለመቀባት የሚጥሩ’ ይላቸዋል። ይህ የኔ አስተያየት ግን እሱ እንዳለው ሳይሆን ለደራሲው አቅም ክብርና አድናቆት ያለኝ ስለሆንኩና እሱም ከአቅሙ በታች እየጻፈ እንደሆነ ስለታዘብኩ ነው፤ በተዘዋዋሪ ለሥነጽሁፉ መጎልበትም ይጠቅም ይሆናል