የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ እስከ 200 ፐርሰንት ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ አደረገ

Wednesday, 03 September 2014 12:59

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ድርጅት የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሥሩ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ተሰማ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሬድዋን ሁሴን በየሦስት ወሩ በሚደረገው የቦርዱና የኮርፖሬሽኑ ስብሰባ ላይ ለድርጅቱ ሠራተኞች ከ87 እስከ 200 ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን ሰሞኑን በዋቢሸበሌ ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሠራተኛው በይፋ መግለፃቸውን ምንጮች ጠቅሰዋል። በድርጅት እስከ 200 ፐርሰንት ጭማሪ ያገኙት አነስተኛ ደመወዝ ባላቸው የሥራ መደቦች ላይ የሚገኙ ሠራተኞች መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በሰኔ ወር አጋማሽ ስያሜውን ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የተቀየረ ሲሆን ከደመወዝና ከጥቅማጥቅም ማነስ እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ በነበረው ሁለት ዓይነት የሠራተኞች አስተዳደር ምክንያት ከፍተኛ የባለሙያ ፍልሰት ይታይበት የነበረ ተቋም ነው።

በአሁኑ ወቅት በተቋሙ ጀማሪ ሪፖርተር የሥራ መደብ ብር 2ሺ 98 ደመወዝ የሚከፈል ሲሆን፤ ለአዘጋጅ ብር 3ሺ 950 እንደሚከፈል ምንጮቹ አስታውሰው፤ ይህ የአሁኑ ጭማሪ ይህንን ክፍያ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽለው ግምታቸውን ተናግረዋል።

አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ ማን ምን ያህል ፐርሰንት ይደርሰዋል እንዲሁም ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው እስካሁን ድረስ ይፋ አለመደረጉን ምንጫችን የጠቀሰ ሲሆን፤ የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ለማጣራት የኢብኮ የሥራ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የኢብኮ ሠራተኞች በተለይም ጋዜጠኞች ለመስክ ሥራ ወደ ክልሎች በሚወጡት ጊዜ በመንግሥት የአበል አከፋፈል መሠረት የሚሰጣቸው አበል በቂ ባለመሆኑ የሥራ ጊዜያቸውን በከፍተኛ ችግር እንደሚያሳልፉ፣ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጋዜጠኞች የመስክ ሥራን እስከመጥላት ደርሰው እንደነበር ያስታወሱት ምንጮቻችን አዲሱ የድርጅቱ ማኔጅመንትና ቦርድ ይህንንም በቅርቡ ያስተካክላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጋዜጠኞች ለብሔራዊ ጣቢያ ከመስራታቸው አንፃር አልባሳትና የመዋቢያ ቁሳቁስ ለመግዛትም ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ይገጥማቸው እንደነበር፣ ይህንንም ፍላጐታቸውን ለማሟላት ጋዜጠኞቹ ለአላስፈላጊ አሰራሮች የተጋለጡበት ሁኔታ መኖሩን ምንጮቻችን አስታውሰዋል።