
ከ 5 ሰአት በፊት
ኳታር ያዘጋጀችው የ2022 የዓለም ዋንጫ በአል-ባይት ስታዲም በድምቀት ተጀምሯል።
አሜሪካዊው ፊልም ተዋናይ ሞርጋን ፍሪማን እና በዩቲዩብ ታዋቂነትን ያተረፈው ኳታራዊው ጋኒም አል-ሙፍታህ የመድረኩ ፈርጦች ነበሩ።
የውድድሩ ዘፈን የሆነውን ድሪመርስ (ህልመኞቹ) የተሰኘውን ሙዚቃ ደቡብ ኮሪያዊው ፖፕ ኮከብ ጆንግ ኩክ እና የኳታሩ ፋሃድ አል ኩባሲ በስታዲየሙ ተገኝተው እየተቀባበሉ አቀንቅነዋል።
ሞርጋን ፍሪማን በመከፍቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እግር ኳስ ሰዎችን ለማቀራረብ ያለውን ኃይል ተርኳል።
የዓለም ዋንጫ በመካከለኛው ምሥራቅ የሙስሊም አገር ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ኳታር የሠራተኞችን መብት ጨምሮ በብዙ ጉዳዮች ስትብጠለጠል ቆይታለች።
በድንኳን ቅርጽ በተሠራው ስታዲየም ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊን ጨምሮ የቱርክ፣ የግብፅ እና የአልጄሪያ መሪዎች ታድመዋል።
ለ30 ደቂቃ የዘለቀው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በርችት ደምቆ በመጠናቀቅ ሜዳውን ለዓለም ዋንጫው መጀመሪያ ጨዋታ ለቋል።
ኳታር የደቡብ አሜሪካዋን ኢኳዶርን አስተናገደች።
የዳኛው ፊሽካ ከተሰማበት ቅጽበት ጀምሮ የኳታር ብሔራዊ ቡድን ተበልጦ አምሽቷል።
- ኢትዮጵያ እና ዘረ መላቸው የተለወጡ ምርቶችን የመጠቀም ጉዳይከ 6 ሰአት በፊት
- በፔሩ ከአውሮፕላን ጋር የተጋጨው የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና በልምምድ ላይ ነበር ተባለከ 6 ሰአት በፊት
- ቱርክ የኩርድ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶችን ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ ፈጸመችከ 6 ሰአት በፊት
በደቂቃዎች ውስጥ የኢኳዶሩ ኤነር ቫሌንሽያ ኳስን እና መረብን ማገናኘት ቻለ።
በቪዲዮ ምስሎች ድጋፍ ረዳት ዳኞች ኳሱ ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ሽረውታል። እፎይታ ለኳታር።
ይህ ጎል የተሻረበት መንገድ ትክክል ነው አይደለም በሚል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋጋሪያ ሆኗል።
ነገሮች ግን አልተሻሻሉም። ቫሌንሽያ ከፍጹም ቅጣት ምት እና በጭንቅላት ባስቆጠራቸው ጎሎች ኢኳዶር ጨዋታውን 2 ለ 0 በመምራት ወደ መልበሻ ክፍል አመሩ።
ከእረፍት መልስ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቀቀ።
አሰልጣኝወ ሳንቼዝ ከጨዋታው በኋላ “ይህ የጠበቅነው ነገር አይደለም” ሲሉ ለስድስት ወር ካምፕ ገብተው ያደረጉትን ዝግጅት ውሃ እንደበላው ገለጹ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ደጋፊዎች ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል።

ሳንቼዝ ተከፍቶ ከሜዳ ለወጣው የአገሬው ሰው በሚቀጥለው ጨዋታ “እንክሳችኋለን” ቢሉም ቀላል አይመስልም።
በመጪው አርብ የአፍሪካ ሻምፒዮናዋ ሴኔጋልን ነው የሚገጥሙት።
የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ከብርቱካናማዎቹ ኔዘርላንድሶች ጋር።
ኳታር በውዝግብ የጀመረችው የዓለም ዋንጫ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ድምቀት የተሸፈነ ቢመስልም፣ ደጋፊዎች ሜዳ ውስጥ ባዩት ነገር አንገታቸውን ደፍተው ተመልሰዋል።
የዓለም ዋንጫው ዛሬ በሚከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ይቀጥላል።
በምድብ ለ ጨዋታዎች ውድድሩ ሲቀጥል አስር ሰዓት ላይ እንግሊዝ እና ኢራን ይጫወታሉ።
በፖለቲካ ጉዳይ የሚቆራቆዙት ሁለቱ አገራት የሚያደርጉት ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ባለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል።
አህጉረ አፍሪካ ተወካይ ሴኔጋል በምድብ ሀ ከኔዘርላንድስ ጋር አንድ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በምድብ ለ ሁለተኛ ጨዋታ አሜሪካ እና ዌልስ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።