November 27, 2022 – Konjit Sitotaw 

የክልሉ አመራሮች የአርበኛ ዘመነ ካሴን ጉዳይ በሽምግልና የመፍታትን ሂደት በበጎ ባለመቀበላቸው የሽምግልናው ሂደት መቋረጡን በሽምግልናው የተወከሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለፁ!

በአርበኛ ዘመነ ካሴ ጉዳይ የሐገሩን ወግና ባሕል በጠበቀ መልኩ ተጀምሮ በነበረው የሽምግልና ሒደት ላይ የገጠማቸውን ችግር እና ሽምግልናውን ማቋረጣቸውን ለጉዳዩ የተመረጡ ሽማግሌዎች ለህዝባቸው ይፋ አድርገዋል።

Image

በዚህም በመጀመሪያ መንግስት በማንኛውም ግዜ ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት ፍላጎት በኖረው ግዜ ሁሉ የሽምግልና ቡድኑ ሽምግልናውን ለመቀጠል ተባባሪ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ በመቀጠል የክልሉ መንግስት አመራሮች ውጤት ሊያስገኝ የሚያስችል ትብብር ለሰላማዊ ሽምግልና ባህላችን ባለማሳየታቸው እና ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከተደጋጋሚ ፍሬ አልባ ሙከራዎች በኋላ የጀመርነውን የሽምግልና እንቅስቃሴ ያቆምን መሆኑን እንገልፃለን ሲል የሽምግልና ቡድኑ አስታውቋል።

በመጨረሻም ጉዳዩን በተመለከተ የጠየቅናቸው አንድ ግለሰብ የሐገር ሽማግሌዎችን ጥረትና ድካም አመስግነው የሽምግልና ቡድኑ በቀጣይ ባሕልና ወጉን ያረከሱ እብሪተኛ የሆኑ አመራሮችን በስምና በምግባራቸው ለሕዝብ እንዲያሳቅ ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሽምግልናውን አንቀበልም ያሉ አመራሮች የግላቸውን ፍላጎት ወደ ጎን በማለት እንመራዋለን የሚሉትን ህዝባቸውን ደግሞ በማክበር ሽምግልናውን በበጎ በመቀበል የህዝብ ልጅ የሆነውን አርበኛ መፍታት እንደሚገባ ገልፀዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ህዝብ በአመራሩ ላይ ያለውን አመኔታ ከማጣቱም በላይ መዘዙም የከፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ “ግፉበት” የሚል አበረታች ይሁንታ ሰጥተው ነበር።

በእነ አርበኛ ዘመነ ካሴ ጉዳይ የተጀመረውን ሽምግልና በአማራ ክልል አመራሮች እምቢተኝነት ሳይሳካ መቅረቱን እና የሽምግልና ሂደቱን ማቋረጣቸዉን ሽማግሌወች አሳውቀዋል ።