December 16, 2022
በአማኑኤል ይልቃል
ላለፉት ሁለት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአማካሪነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ነብዩ ባዬ፤ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ ነብዩ የኃላፊነት ቦታውን የተረከቡት፤ ከሶስት ወራት በፊት በድንገት ህይወታቸው ያለፈውን አቶ አብይ ኤፍሬምን በመተካት ነው።
ሹመቱን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ነብዩ፤ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት እንዲመሩ መሾማቸውን አረጋግጠዋል። አዲሱ ኃላፊ ሹመቱን ያገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካኝነት መሆኑንም ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ በኃላፊነት ከተሾሙ ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ነብዩ ባዬ፤ ከሰኔ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በፕሬስ ሴክሬተሪያት አማካሪ ቡድን አባልነት ሲሰሩ ቆይተዋል። በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በአራዳ ምርጫ ክልል የተወዳደሩት አቶ ነብዩ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ናቸው።
አቶ ነብዩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቲያትር ስነ-ጥበባት ትምህርት ክፍል በ1993 ዓ.ም ነበር። በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ምሩቅ መምህር ሆነው መስራት የጀመሩት አቶ ነብዩ፤ በ2001 ዓ.ም በስነ-ጽሁፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከዚያው ዩኒቨርስቲ ይዘዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ያገኙት አቶ ነብዩ፤ ከመምህርነት ባሻገር በአመራርነትም ሰርተዋል። በ2003 ዓ.ም የቲያትር ትምህርት ቤት ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን፤ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ዓመታት የሥነ-ጥበባት ኮሌጅን በዲንነት መርተዋል። ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በዩኒቨርስቲው የአፍሪካ እና ኦሪየንታል ጥናት ማዕከል “በአፍሪካን ስተዲስ ፕሮግራም” የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሰሩ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ከአንድ ወር በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን በዋና ስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ ተመድበው የነበሩት አቶ ነብዩ፤ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት በተለያዩ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ተሾመው አገልግለዋል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ወደ ስልጣን ሲመጡ፤ በካቢኔ አባልነት ከሾሟቸው ግለሰቦች ውስጥ አንዱ አቶ ነብዩ ነበሩ።
ከነሐሴ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮን እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ነብዩ፤ በኃላፊነት ቦታው ለሁለት ዓመት ገደማ አገልግለዋል። በዚህ የኃላፊነት ቆይታቸው ወቅት፤ የሚመሩት ቢሮ ስያሜ ወደ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ተቀይሯል።
አቶ ነብዩ በአዲሱ ሹመታቸው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን አስተዳደራዊ ስራዎች የመምራት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ከአስተዳደራዊ ኃላፊነቶቻቸው መካከል፤ የጽህፈት ቤቱን ሰራተኞች ማስተዳደር፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነቶችን መመስረት፣ አጀንዳ መቅረጽ፣ ባለጉዳዮችን ማስተናገድ እና ከእነርሱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገኙበት አቶ ነብዩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እነዚህን ተግባራት ሲያከናውኑ የቆዩት አቶ አብይ ኤፍሬም “በድንገተኛ ህመም” ህይወታቸው ያለፈው ጳጉሜ 2፤ 2014 ነበር። አቶ አብይ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ልዩ ረዳት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን ስራ የጀመሩት በ2008 ዓ.ም ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)