December 26, 2022 – BBC Amharic 

ዶላር እና ብር

ከ 6 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷ የሳሳ ነው።

የዓለም ባንክ ዶላር እና ወርቅን ጨምሮ የኢትዮጵያ ክምችት በ2020 ሦስት ቢሊየን ገደማ ነበር ይላል።

ለንጽጽር እንዲመች ጎረቤት አገር ኬንያን እንመልከት። በመተሳሳይ ዓመት የኬንያ ክምችት 8.3 ቢሊየን ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ ወደ 9.4 ተመንድጓል።

ኬንያ በተለምደ ጥቁር ገበያ ብለን የምንጠራው የዶላር መገበያያ ሱቅ የላትም።

በአንፃሩ መንግሥት እና ሕዝብ አውቋቸው ማስታወቂያ እና የዋጋ ዝርዝር ሰቅለው በይፋ ዶላር የሚሸጡ እና የሚገዙ ሱቆች በየሰፈሩ ተሰድረዋል።

ባንኮችም ተመሳሳዩን አገልግሎት ለውጭ ምንዛሪ ሻጭና ገዢ በገበያ ዋጋ ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ተቋም የባንኮችን ደጅ ይጠናሉ። በተለይ አስመጪዎች የሚሹትን ያህል ዶላር ከባንክ ማግኘት ሲያቅታቸው ፊታቸውን ወደ ትይዩ ገበያ (ብላክ ማርኬት) ያዞራሉ።

ዶላር ባንክ ውስጥ ያለው ዋጋ እና በትይዩ ገበያ የሚሸጥበት ዋጋ ልዩነት እየሰፋ፤ እየተለጠጠ መጥቷል።

ለምሳሌ ከሰሞኑ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያው ከ90 ብር በላይ እየተሸጠ እንዳለ ቢቢሲ ሰምቷል፤ በባንክ ደግሞ ወደ 53 ብር ገደማ ይመነዘራል።

ይህን የዶላር እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ከአንድም ሁለት ጊዜ በላይ የብር ዋጋን ዝቅ አድርጋለች።

ነገር ግን ይህ የመፍትሔ እርምጃ ዓላማውን ያሳካ አይመስልም። ቢሆንም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አሁንም የብር ዋጋ እንዲወርድ ይሻሉ። ለምን?

ኢትዮጵያ እና ዶላር

ቴድሮስ መኮንን የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ናቸው። በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር የተሰኘው ተቋም የምጣኔ ሃብት ተወካይ ሆነው ያገልግላሉ።

ቴድሮስ ኢትዮጵያ እና ዶላር ያላቸውን ግንኙነት ፈታትተው ይተነትናሉ።

“በቀደመው ጊዜ. . .” ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤ በቀደመው ጊዜ (በፈረንጆቹ 2005/06) ኢትዮጵያ ትጠቀም የነበረው መንገድ ‘ኢንተርባንክ ፎሬይን ኤክስቼንጅ’ የተሰኘ ነበር።

ይህ ማለት ዶላር ሞልቶ የተረፋቸው ባንኮች ዶላር ላጠራቸው ባንኮች የሚሸጡበት ሥርዓት ነው። ይህን የሚቆጣጠረው ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ነው።

በዚህ ወቅት ገበያው ላይ ያለው የዶላር ዋጋ የሚተመነው በባንኮች መካከል በሚደረገው ግብይት እና በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር መሠረት ነበር።

“ሕጉ፤ የዶላር ዋጋ የሚወሰነው በዚህ ግብይት ነው ይላል። ነገር ግን ከተፈለገው በታች እንዳይወርድም ሆነ ወደላይ እንዳይወጣ ብሔራዊ ባንክ ይቆጣጠረዋል። ይህ ማኔጅድ ፍሎቲንግ ይባላል።”

ነገር ግን ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ዶላር እያጠራት መጣ። በፈረንጆቹ 2010/11 ባንኮች እንኳን የሚተርፋቸው ዶላር ሊኖር ይቅርና ካዝናቸው አልሞላ አለ።

ዘንድሮ ብር ከዶላር ጋር ሲነጻጸር ያለውን ዋጋ የሚተምነው ብሔራዊ ባንክ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየቀኑ ዶላር በብር ሲመነዘር ምን ያህል ሊሆን እንደሚገባ ተምኖ ለባንኮች ይፋ ያደርጋል።

ነገር ግን ይህ ዶላር በባንኮች የሚሸጥበት ዋጋ ትክክለኛውን የዶላር ዋጋ አይወክልም፤ ባይሆን በትይዩ ገበያ (ብላክ ማርኬት) ያለው የዶላር ገበያ ዋጋ እውነታውን ያሳያል የሚሉ ተንታኞች አሉ።

እኒህ ተንታኞች የብር ዋጋ አሁንም ካለበት ዝቅ ሊል ይገባል ባይ ናቸው። ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም የዶላር ዋጋ ከፍ ብሎ የብር ዋጋ ዝቅ ቢል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

“ዲቫሉዌት ማድረግ ማለት የአንድን አገር ገንዘብ ከሌሎች አገራት ገንዘብ አንጻር አቅሙን ማዳከም ማለት ነው” የሚሉት የሒሳብ አዋቂው ጥላሁን ግርማ ናቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር አባል የሆኑት ጥላሁን ይህን በምሳሌ ሲያስረዱ “ለምሳሌ ብር ወደ ዶላር ሲመነዘር ምን ያክል ሊሆን ይገባል የሚለውን ተመዝኖ ዝቅ ይደረጋል” ይላሉ።

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ሁለት ጊዜ ብር ከዶላር ጋር ያለውን ዋጋ ተመን ማሳነሷ የሚዘነጋ አይደለም። የመጀመሪያው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ 2017 ላይ የተደረገ ለውጥ ነው።

ነገር ግን ይህ ‘ዲቫሉዌሽን’ ምን ያህል ለውጥ አመጣ በሚለው ሐሳብ ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይከራከራሉ።

ዶላር እና ብር

የወጪ እና ገቢ ንግድ

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዶላር ዋጋ መጨመር አንደኛው ምክንያት የወጪ እና ገቢ ንግድ ሚዛናዊ አለመሆን ነው።

በሌላ ቋንቋ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት (ኤክስፖርት) ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባው በጣም ያነሰ ነው።

በፈረንጆቹ 2017 ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው አንድ ዘገባ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ በገፍ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል አንዱ የተጣራ ፔትሮሊየም ነው ይላል።

የዓለም ንግድ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን መድኃኒት፣ የሰውና የጭነት ተሽከርካሪ እንዲሁም ማዳበሪያ በብዛት ታስገባለች ሲል በ2020 ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

ሪፖርቱ አክሎም ሩዝ፣ ስኳር፣ ስንዴ እና ፉርኖ ዱቄት፣ ዘይትን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶ በርከት ብለው እንደሚገቡም ዘርዝሯል።

በተቃራኒው ወደ ውጭ የምትልካቸው ቡና፣ አበባ፣ አልባሳት እና የቆዳ ውጤቶች ናቸው።

ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የምታወጣው ገንዘብ ወደ ውጭ በመላክ ከምታስገባው ገንዘብ እጅግ የላቀ መሆኑ የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲት) ፈጥሯል ይላሉ ጥላሁን።

ስታቲስታ የተሰኘው የአገራትን ምጣኔ ሃብት በአሃዝ የሚተንተን ገፅ በ2022 የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ንግድ ልዩነት 12 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ይላል።

“የገቢ እና የወጪ ንግዱ ሚዛናዊ ካልሆነ የዶላር ፍላጎት ይቀንሳል የሚል እምነት የለኝም” የሚሉት ጥላሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ መገበያያ የሆነው የዶላር ዋጋ ለመጨመሩ ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው ብለው ያስባሉ።

“የዶላር ፍላጎታችን በዋናነት ከፍ ያለው በርካታ ሸቀጦች ከውጭ ስለምናስመጣ ነው። በተቻለ መጠን ክፍተቱን ማጥበብ አለብን።”

ባለሙያው ይህ የወጪ እና የገቢ ንግድን ለማመጣጠን ኢትዮጵያ አሁን ከምትልከው የላቀ ምርት ወደ ውጭ መላክ እንዳለባትና ‘ኢምፖርት’ የሚደረጉ አንዳንድ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት እንደሚገባ ይመክራሉ።

“እርግጥ ነው ፍላጎትን በአንድ ጊዜ መግታት አይቻልም። ሰዎች ጫማ አትድረጉ፣ አትልበሱ፣ መድኃኒት አታስገቡ ማለት አትችልም። ነገር ግን እዚሁ አገር ቤት ማምረት ከቻልን የዶላር ፍላጎት እየቀነሰ ይመጣል።”

በቅርቡ መንግሥት የአልኮል መጠጥ እና የመዋቢያ ቁሳቁሶችን የመሳሰሉ ምርቶች ወደ አገር ቤት የሚያስገቡ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ ማዘዙ ትዕዛዝ አውጥቶ፣ መልሶ ይህን ውሳኔ በመከለስ አንዳንዶቹ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መፍቀዱ ይታወሳል።

ብር

ዲቫሉዌሽን . . . ?

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ቴድሮስ የኢትዮጵያን ብር ዋጋ ከዶላር አምጻር ማዳከም ተገቢ አይደለም ብለው ከሚከራከሩ ሰዎች ጎራ ናቸው።

“ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሞክረናቸው አልተሳኩልንም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ነገር ግን የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋምን (አይኤምኤፍ) ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ኢትዮጵያ የብርን አቅም ማዳከም (ዲቫሉዌት) ማድረግ አለባት የሚል ምክር ሲሰጡ ይደመጣሉ።

የብር አቅም መደካም አለበት ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አንደኛው አመክንዮ፣ የዶላር ትክክለኛ ዋጋ በትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ) ላይ ያለው ነው የሚል ነው።

ይህ ላናገርናቸው ሁለቱም የምጣኔ ሃብት ሙያተኞች የሚዋጥ ሐሳብ አይደለም።

ለምሳሌ አረብ አገራት የዶላር ፍላጎት ከፍ ሲል ከክምችታቸው (ሪዘርፍ) አውጥተው ወደ ገበያው እንደሚያሰራጩ፣ አሊያም ትክክለኛ ወዳሉት የምንዛሪ ተመን እንደሚቀይሩት የሚያስሩዱት ቴድሮስ ኢትዮጵያ ግን ይህን የማድረግ አቅም አላት ብለው አያስቡም።

“እኛ አገር ዋና ዋና የሚባሉት ምግብ እና ነዳጅ እንዳይወደዱ ስለሚፈለግ መንግሥት ከወጭ ገበያውም ሆነ ከሬሚታንስ (ሃዋላ) ሚመወጣውን ዶላር በርካሽ ይገዛውና ይጠቀምበታል። ነገር ግን ባንክ በተመነው ዋጋ የዶላር እጥረት ስላለ አስመጪዎች ወደ ትይዩ ገበያ (ብላክ ማርኬት) ይሄዳሉ።”

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት “ዋጋው ከትይዩ ገበያው እኩል ይሁን አሊያም ትክክለኛውን ተመን አውጡ” ብለው ቢወተውቱም ከአንድም ሁለት ጊዜ ተሞክሮ ብዙ ውጤታማ እንዳልሆነ ቴድሮስ ያነሳሉ።

ሰዎች ዶላር የሚገዙበት ዋነኛ ምክንያት ሁለት ነው። አንደኛው ዕቃዎችን ለማስመጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሃብት ለማስቀመጥ ነው።

ስለዚህ ይላሉ ቴድሮስ፤ “የብር ዋጋ አዳከምን ማለት አንደኛው ሃብታቸውን በዶላር የሚያስቀምጡ ሰዎች እንዲገዙ፤ ሁለተኛ ከውጪ የሚመጡ ዕቃዎች ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል።”

ጥላሁንም በዚህ ይስማማሉ። “የዶላር ዋጋ ጨመረ ማለት መንግሥት ከውጭ የሚያስገባቸው ነዳጅን የመሳሰሉ ምርቶች ዋጋ ከፍ አለ ማለት ነው” ይላሉ።

“ለምሳሌ ብራችንን ዲቫሉዌት አድርገን አንድ ዶላር 100 ብር ብናደርግ ያለው የዋጋ ንረት እንዴት እንደሚከብድ እናስበው፤ ሰዎች መቋቋም ከሚችሉት በላይ ሊሆንባቸው ማለት ነው።”

ስለዚህም ያለው አማራጭ አገሪቱ አምርታ ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች መጠን ከፍ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን ከፍ ማድረግ እንዲሁም ከውጪ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ አቅርቦት መተካት በባለሙያዎች ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።