January 10, 2023 – Konjit Sitotaw
ከመቐለ ወደ አዲስአበባ ለመጓዝ የአውሮፕላን ትኬት የቆረጡ ወጣቶች በመቐለ አሉላ አባነጋ ኤርፖርት ከጉዞ ተከልክለው እየተመለሱ መሆኑ ገለፁ። የጉዞ ክልከላው በተለይም ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ተመሳሳይ የጉዞ ክልከላ ከሽረ ወደ አዲስአበባ በሚጓዙ ወጣቶች ላይም መደረጉ ተገልጿል።
የበረራ ትኬት ቆርጠው ከመቐለ ወደ አዲስአበባ ለመጓዝ መቐለ ወደሚገኘው አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፍያ ካመሩ መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች የሆኑት ከጉዞ እየተከለከሉ ያሉት ካለፈው ዓርብ ሕዳር 28 ቀን 2015 ጀምሮ መሆኑ ተገልጿል። የጉዞ ክልከላው ከገጠማቸው መካከል የሆኑት ከአዲስአበባ መቐለ በረራ እንደተጀመረ በሁለተኛው ቀን ወደ መቐለ መምጣታቸው የነገሩን ኑሮአቸው አዲስ አበባ ያደረጉ፣ ቤተሰብ ጥየቃ ወደ መቐለ የመጡት አቶ ሀፍታይ ገብረ፥ ዛሬ አዲስአበባ ወዳሉት ልጆቻቸው እና ወደ ቋሚ ስራቸውና ኑሯቸው ለመመለስ የጉዞ ትኬት ቆርጠው በአሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፍያ ቢገኙም በኤርፖርቱ የፀጥታ ሰራተኞች ከጉዞ መከልከላቸው ነግረውናል። 50 ዓመታቸው መሆኑ ያገሩን አቶ ሀፍታይ የኤርፖርቱ ሰራተኞች “ሽማግሌዎች እና ህፃናት ብቻ እየለዩ እያሳለፉ ነው፣ እኛን ግን ከልክለውናል” ብለዋል። ችግሩ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኩል ይሁን ከክልሉ አስተዳደር ግልፅ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።
ሌላው ያነጋገርነው ከጉዞ የተከለከለው ወጣት ገብረሩፋኤል በርሀ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የተነሳው በመዘጋጋቱ ምክንያት አቋርጦት የነበረ የውጭ ሀገር ጉዞ ሂደት ለማስቀጠል መሆኑ ጠቅሶ ይሁንና ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር መከልከሉ እንዳሳዘነው ነግሮናል። “የኤርፖቱ ሰዎች ለምን እያከላከሉ እንዳለ ስንጠይቃቸው እኛ የምናውቀው ነገር የለም፣ ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው እየፈፀምን ያለነው ነው የሚሉት” ብሏል ገብረሩፋኤል።
ለረዥም ጊዜ ወደ ትግራይ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም የተጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት ባለፈው ሕዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር።
ዛሬ ረፋድ በአሉላ አባነጋ ዓለምአቀፍ ኤርፖርት በነበረን ቆይታ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ” የሚል ፅሁፍ ያለበት ልብስ የለበሱ እንዲሁም “ብሔራዊ መረጃና ድህንነት አገልገሎት” የሚል ዩኒፎርም ያደረጉ፣ የፍተሻ እና ሰነዶች ማረጋገጥ ሰራተኞች፥ መታወቅያ እና የጉዞ ትኬት እየተመለከቱ ገሚሶቹን ሲያሳልፉ ሌሎችን ደግሞ ሲመልሱ ተመልክተናል። በአብዛኛው እንዲመለሱ የሚደረጉት ወጣቶች ሲሆኑ፤ ህፃናት የያዙ እናቶች፣ አረጋውያን፣ በሽተኞች በቀጥታ እንደሚያልፉ ተረድተናል። ኤርፖርቱ በቅርቡ ተቋሙ በተረከቡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጥበቃ ይደረግለታል። በክልከላው ዙርያ የኤርፖቱ የደህነት ሰራተኞች ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም። ተመሳሳይ ክልከላ ከሽረ ወደ አዲስአበባ በሚበሩት ላይም መደረጉ ከቦታው መረጃ ያደረሱን ገልፀውልናል።
በጉዞ ክልከላው ዙርያ ከፌዴራሉ መንግስት እና የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ወደ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ጥሪ ባለመመለሳቸው ማካተት አልቻልንም። መንግስታዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ዛሬ ባሰራጨው ዜና ከመቐለ ወደ አዲስአበባ የሚጓዙ ወጣቶች ለምን ከጉዞ እንደታገዱ የክልሉ መንግስት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር እየተነጋገረበት ስለመሆኑ አስታውቋል። ለረዥም ጊዜ ወደ ትግራይ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም የተጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት ባለፈው ሕዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር።
