January 10, 2023 – BBC Amharic

አዲስ አበባ፡ በነዳጅ ማደያ አካባቢ የሚታዩ መኪኖች

9 ጥር 2023

የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ ምርቶች ላይ ለረጅም ጊዜ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ካነሳ በኋላ ባለፉት ስድስት 6 ወራት አንድ ሊትር ቤንዚን የ13 ብር ጭማሪ አሳየ።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ ባለፉት 6 ወራት በቤንዚን ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በመቶኛ ሲሰላ 28.14 ደርሷል።

ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ላይ አንድ ሊትር ነዳጅ 47 ብር ከ83 ሳንቲም ይሸጥ የነበረ ሲሆን፤ ከጥር 01/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ በሆነው የዋጋ ማሻሻያ መሠረት አንድ ሊትር ቤንዚን 61 ብር ከ29 ሳንቲም ይሸጣል።

መንግሥት በነዳጅ ምርቶች ላይ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ቀስ በቀስ ማንሳት መጀመሩን ተከትሎ ባለፉት ወራት ከፍተኛ ሊባል የሚችል ጭማሪ በነዳጅ ምርቶች ላይ እየታየ ይገኛል።

መንግሥት እንደሚለው የነዳጅ ምርቶችን ለመደጎም በወር በአማካይ 10 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ይገልጻል።

መንግሥት እንደሚለው በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ዋጋ ቢሰላ የ1 ሊትር ናፍጣ የመሸጫ ዋጋ ብር 91 ከ23 ሳንቲም እና የቤንዚን ደግሞ በሊትር 82 ብር ከ07 ሳንቲም መሆን ነበረበት። በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ዋጋው ከዚህ ከፍ ይላል።

ነገር ግን መንግሥት አጠቃላዩን የነዳጅ ዋጋን ወደ ተጠቃሚው ከማሸጋገር ይልቅ ከፍተኛ ወጪን በማውጣት ለነዳጅ ምርቶች ጭማሪ ሲያደርግ ቆይቷል።

ይህ ድጎማም በመንግሥት ወጪ ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የወጪ ጫናን በማስከተሉ ቀስ በቀስ ድጎማውን በሂደት ለማንሳት ባወጣው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ይህ ድጎማን የማንሳት ሂደት ግን ሕብረተሰቡ ላይ ጫናን እንዳይፈጥር በሚል በተለየ ሁኔታ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውለውን የነዳጅ አቅርቦት በ”ብሔራዊ የታለመለከት የነዳጅ ድጎማ” አሰራር፣ ድጎማ እየተደረገ መሆኑን መንግሥት ገልጿል።

በነዳጅ ምርቶች ላይ ባለፉት 6 ወራት የታየው የዋጋ ጭማሪ

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከቤንዚን በተጨማሪ በነጭ ናፍጣ፣ በኬሮሲን፣ በቀላል እና ከባድ ጥቁር ናፍጣ እንዲሁም በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ የዋጋ ማሻሻያ አድርጓል።

ሚንስቴሩ፤ ነጭ ናፍጣ 67 ብር ከ 30 ሳንቲም፣ ኬሮሲን 67 ብር ከ30 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 49 ብር ከ67 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 48 ብር ከ70 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 67 ብር ከ91 ሳንቲም እንዲሸጡ ወስኗል፡፡

ሚኒስቴሩከጥር 01/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጸሚ በሆነው የዋጋ ክለሳ ላይ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ሕብረተሰብ የሚሰጠው ድጎማ እንዲጨምር ተደርጓል ብሏል።

በዚህምመሠረት በአንድ ሊትር ቤንዚን ሲሰጥ የነበረው ድጎማ ከብር 15 ከ 76 ሳንቲም ወደ ብር 17 ከ33 ሳንቲም፣ እንዲሁም የአንድ ሊትር ናፍጣ ድጎማ ከብር 19 ከ02 ሳንቲም ወደ ብር 22 ከ 68 ከፍ እንዲል መደረጉ ተገልጿል።