January 22, 2023 – EthiopianReporter.com 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሸገር ከተማ አስተዳደር የሰነድ ርክክብ መፈጸማቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

ወደ አዲስ አበባ የተካለሉ በቀድሞ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የነበሩና በአዲሱ የአስተዳደር ወሰን መሠረት ወደ አ/አ እንዲካለሉ የተደረጉ አካባቢዎችን የተመለከቱ መረጃዎችና ሰነዶችን፣ አጎራባች ለሆኑ የአዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች ማስረከቡን የሸገር ከተማ አስተዳደር አሳውቋል።

በተመሳሳይ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ሥር ሲተዳደሩ የነበሩና በተካለለው የአስተዳደር ወሰን መሠረት በቅርቡ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ወይም ወደ ሸገር ከተማ እንዲካለሉ የተደረጉ አካባቢዎችን የተመለከቱ ሰነዶችንም፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ማስረከቡ ተነግሯል።

“የባለቤትነት መብት የተፈጠረላቸው ላይ የሚቀየር ነገር የለም” ያለው አስተዳደሩ ወደ ኦሮሚያ የመጡት ፋይላቸው ዞሮ ርክክብ መፈጸሙን አሳውቋል።

በዚህ መሠረት ግንባታቸው ተጠናቆ ዕጣ የወጣባቸው የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የተገነቡት በአዲስ አበባ አስተዳደር ሲሆን፣ የቤቶቹ ባለቤቶች የተመዘገቡ ቆጣቢዎች በመሆናቸው ቤቶቹ ለቆጣቢዎች መተላለፋቸውን ገልጿል።

የሸገር ከተማ በቤቶቹ ላይ የሚፈጥረው አዲስ ባለቤትነት አይኖረውም የተባለ ሲሆን ወደ ሸገር አስተዳደር ሲተላለፉ የባለቤትነት መብት ተፈጥሮላቸው መሆኑ ተመላክቷል።

የሸገር ከተማ ኃላፊነት ከዚህ በኋላ ያለውን ሁኔታ ማስተዳደር ብቻ እንደሚሆን ተገልጿል።

” የቤቶቹ ባለቤቶች መብታቸውን ይዘው በሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር ይተዳደራሉ ” ያለው አስተዳደሩ፤ “የመሸጥ፣ የመለወጥና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በሸገር አስተዳደር የሚከናወን ይሆናል” ብሏል።