You are currently viewing በአምባሰል ወረዳ የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ     የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም…

በአምባሰል ወረዳ የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም…

Post published:March 1, 2023

በአምባሰል ወረዳ የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ ሸዋ

በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ለአድዋ ጦርነት ምክንያት በሆነውና የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የመታሰቢያ ሐውልት የካቲት 22/2015 ተመርቋል።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል በይስማ ንጉስ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል። ይስማ ንጉስ ላይ የተገነባውን የአጼ ምንሊክና የእቴጌ ጣይቱ የማስታወሻ ሐውልት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ህሊና መብራቱና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን/ዶ.ር/ መርቀው ከፍተዋል፡፡

የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት ኮንት አንቶሎኒን “ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ” ብለው መናገራቸውን የሚገልፅ ሲሆን የአጼ ምንሊክ ሐውልት በዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ደግሞ ንግስቲቱን በጥሞና ሲያዳምጡ የሚያሳይ ነው፡፡

ለመታሰቢያ ሐውልቱ ግንባታ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉና ወጭውም በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሸፈኑን ተገልጿል። የአጼ ምንሊክ ሐውልት 2 ሜትር ከ70 ሳንቲሜትር እንዲሁም የእቴጌ ጣይቱ 2 ሜትር ከ 80 ሳንቲሜትር ርዝመት አለው።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ህሊና መብራቱን ጨምሮ የደቡብ ወሎ ዞን እና የአምባሰል ወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የመታሰቢያ ሐውልቱ በይስማ ንጉስ ለመገንባት በእቅድ ከተያዘው ውስጥ በሁለተኛ ምዕራፍ የግንባታ ሂደት ውስጥ የተካተተ ነው። በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ይስማ ንጉስን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከአማራ ክልል መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በተገኘ 25 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጭ የመግቢያ በር፣ሙዚየም እና ካፌ ጥር 2013 ዓ.ም መመረቁ ይታወቃል።

ለታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት መነሻ በመሆን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የውጫሌ ውል ቀዳሚው ነው፡፡ የውጫሌ ውል በንጉሥ ምኒሊክ እና በጣሊያን ንጉሥ ኡምቤርቶ ወኪል ኮንት አንቶሎኒ መካከል ውጫሌ በሚባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡

ውጫሌ ውል ስያሜው የተሰጠው የውጫሌ ውልን 17 ኛ አንቀፅ በጣሊያኖች የተዛባ የጣሊያንኛ ትርጉም አስተርጉመው የአጼ ምንሊክ ባለቤት ጣይቱ ብጡል በማወቃቸው ውሉን ለማፍረስ በጊዜው የተገደዱበትን ታሪካዊ ገፅታ የሚያንፀባርቅ ነው።

የውጫሌ ውል 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን የውሉ 17ኛ አንቀጽ ትርጉም የተዛባ፣የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካና ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር ነው። ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት ከሆነው የውጫሌ ውል በዋናነት አለመግባባቱን የፈጠረው አንቀጽ 17 በአማርኛ:_ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል፡፡

” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደና ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት መመስረት እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡ የአንቀጹ የጣሊያነኛ ትርጉም:_ “የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ አገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል፡፡” በሚል ነበር።

የአምባሰል ወረዳ ኮሙኒኬሽን