· ያልተዘመረለቱ ጸረ ፋሽስት ኢትዮጵያዊ አርበኛ:– ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ!
#Achamyeleh tamiru
በሰው ልጅ ሕይዎት ውስጥ ትልቁ ጥያቄ ስንት ዘመን ኖርን የሚለው ሳይሆን ረጅሙንም ሆነ አጭሩን ዕድሜ እንዴት ኖርነው የሚለው እንደሆነ አብዛኛዎቹ አሳቢዎች ይስማማሉ። የምንኖርባት ፕላኔት ለቁጥር የሚበዙ በርካታ ወጣት ጀግኖች ያፈራች፤ በደማቸው አዲስ ታሪክ የጻፉና የነጻነት ፋኖ የለኮሱ የአንድነት ቀንዲል ሆነው በታሪክ ቅብብሎሽ ሂደት በብዙዎቻች ልብ ውስጥ ታትመው የሚኖሩ ሰዎች ያለፉባት ምድር ናት።
አገራችን ኢትዮጵያ ለእናት አገራቸው ቀድመው የደረሱ፣ አንተ በመባያ የልጅ እድሜያቸው አንቱ የሚያሰኝ ድንቅ ስራ የሰሩ፤ ላገራቸው ሩቅ አሳቢ ሆነው የወጣትነት ትኩረታቸው ብዙ ዘመን እንደተጠራቀመ የሽምግልና ምክር ለዘመናት የሚያስተጋባ ተግባር የነበራቸው ጀግኖች ነበሯት። በዛሬው ጽሑፋችን አገራችን ኢትዮጵያ ከነበሯት ከራሳቸው በላይ ላገራቸው የሚያስቡ፤ ምክራቸው አገር የሚያውል ትላልቆች መካከል ቀዳሚው የሆኑትን የወጣቱን የጸረ ፋሽስት ጥሊያን አርበኛ የሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብን ታሪክ እናወሳለን።
በዚህ የሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብን ታሪክ በዳሰስንበት ጽሁፍ የተጠቀምናቸው የታሪክ ምንጮቻችን ታደሰ ሜጫ በ1942 ዓ.ም. «ጥቁር አንበሳ፣በምዕራብ ፣ኢትዮጵያ» በሚል ያሳተሙት መጽሐፍ፤ ሐዲስ ዓለማየሁ በ1985 ዓ.ም. «ትዝታ» በሚል ያሰናዱት ግለ ታሪክ፣ አቶ ተፈራ ይኼይስ በ1952 ዓ.ም. «የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር ትምህርት ቤት ብሩራዊ ኢዮቤልዩ» በሚል ያዘጋጁት መጽሐፍና ጀኔራል ነጋ ተገኝ በ1985 ዓ.ም. «የኢትዮጵያውያን የረዥም ዘመናት ትግልና የዘመናዊ ሰራዊት አመሠራረት 1855-1974» በሚል የጻፉት መጽሐፍቶች ናቸው።
በላይ ኃይለ አብ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የፈረንሳይኛ ትምህርት ተምሮ በእውቀት ከጎለመሰ በኋላ ፍላጎቱ በወታደርነት ግልጋሎት ለውድ አገሩና ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ክብር የሚገባውን መስራት በመሆኑ ወደ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በመግባት የጦር ትምህርት ተምሯል።
በላይ ኃይለ አብ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር ትምህርት ቤት ገብቶ ከተማረና አስፈላጊውን የመኮነንትን ውድድር ከጨረስ በኋላ በመልካም ጠባይና ችሎታው እንዲሁም በጦር ትምህርት ቤት ባሳየው መልካም አርአያ ተግባሩ የተዋጣለበት መኮንን በመሆኑ በሌተናት ኮሎኔልነት ማዕረግ በቅቶ ተመርቋል። በ1928 ዓ.ም. ጠላት ሀገራችንን ለመውረር በመጣ ጊዜ ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ አገሩን ለማገልገል ለገባበት ቆራጥ መንፈስ ታጥቆ በመነሳት የጠላት ጦር ድል እያደረገ ወደ አዲስ አበባ በመቃረቡ አንድ ሻለቃ ጦር እየመራ ወደ ጣርማ በር አዝምቶ ለሚቀጥለው ሲጠባበቅ ከድል በኋላ ለወደፊት የአርበኝነት ሥራውን ለመቀጠል ሲል በጠቅላይ ሠፈሩ የሚገኘውን ጦር አሳብሮ ጠላት ወደ አልደረሰበት ለቀምት ሄደ። ጦሩም ከገነት ተነስቶ ወደ ምዕራብ በሚጓዝበት ጊዜ ለጠላት ተሰብኮ የነበረውና አላዋቂውም ባላገር አላሳልፍም በማለት ከባድ ጦርነት በየመንገዱ ቢያደርግባቸውም እነ ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ግን ከአዲስ አበባ ተነስተው ለቀምት የደረሱት የራቀውን በመምከር፤ የቀረበውን በማስረዳት በኃይልም ለመጣ መልስ በመስጠት ነበር።
ለቀምት እንደገቡ የአውራጃው ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ሀብተማርያም እስከ መጨረሻው በአርበኛነት ለመቆየት እንዲቆርጡና ለመተባበር ያበቋቸው የዚሁ መኮንን ፍጹም አስረጁነት ስለማረካቸው ነበር። ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ በአዛዥነቱ በምስጉንነቱ በቀልጣፋነቱ ወታደሩ የፍቅር ዓይን ጥሎበት ስለነበረ የጥቁር አንበሳ ጦር በምዕራብ ኢትዮጵያ ሲቋቋም በምርጫ ድልድል የጥቁር አንበሳ ጠቅላይ የጦር አዛዥና አሰልጣኝ ሆነ። እንደሚታወቀው የጥቁር አንበሳ ጦር በዳግም ጥሊያን ወረራ ወቅት ሁሉም ሀገሩን ሊታደግ መከራውን ሲያይ በነበረበት ዘመን የሆለታ ገነት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ትምህርት ቤት ምሩቃን የነበሩ የጦር መኮንኖች 400 ያህል ሆነው መቀመጫውን ነቀምት አድርጎ የተመሰረተ ድርጅት ነው።
የጥቁር አንበሳ የጦር ድርጅት ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የእንስሳት ሕክም ባለሞያው ዶክተር አለመ ወርቅ በየነ ሲሆን የጦሩ አዛዥና አሰልጣኝ ደግሞ ባለታሪካችን ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ነበር። ከሁለቱ ታዋቂ አርበኞች በተጨማሪ ድርጅቱ በአርበኛነት የከንቲባ ገብሩ ደስታ መላ ቤተሰብን በሙሉ ያቀፈ ሲሆን በአመራርነት ደግሞ 25 ስመጥር የጦር መኮንኖች እና ታዋቂ ሲቪሎች ነበሩ። የጦር ማህበሩ አላማ ጠላትን መፈናፈኛ በማሳጣት ለእናት አገር መሞት ብሎም ወጣቶችን ለሀገራቸው ዘብ እንዲቆሙ መቀስቀስ ነበር። ለዚህም አለማ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን ቀስቃሽ የድርጅቱን መዝሙር በየቦታው ይበትኑ ነበር፤
በለው፤ በለው!
አትለውም ወይ አትለውም ወይ?
ጥቁር አንበሳ አይደለህም ወይ?
ኸረ በለው፤ ኸረ በለው! በለው! በለው!
ኸረ በለው፤ ኸረ በለው!
አትለውም ወይ አትለውም ወይ!
የጠቅል ሎሌ አይደለህም ወይ?
ያድዋ ጀግኖች ቅርስ አይደለህም ወይ?
ለዙህ ላታላይ ትሠጋለህ ወይ?
ጥንታዊ ጀግና አይደለህም ወይ?
ይህን መዝሙር በድምጽና በሙዚቃ የሚያሰሙት ይልማ መንገሻ የሚባሉ አርበኛ ነበሩ። ኋላም ይህ መዝሙር ወደ ካርቱም ተሰዶ ቆይቶ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ወደ መናገሻቸው ሲገቡ ለጉዞው ፊታውራሪ ሆኖ አብሮ እየገሰገሰ አርበኞች በሰልፍ እየዘመሩት ቤተ መንግሥት ድረስ ደርሷል።
ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ በለቀምት የወታደር አሰልጣኝነቱንና የአዛዥነቱን ኃላፊነት ከተሰጠው በኋላ በኅብረት የታጠቀው ጦር መልካም አደፋፋሪና መሪ በማግኘቱ፤ በሥልጣኔም በጦር ታክቲክም ይበልጥ እየሰፋ በመሄዱ በደረሰበት ሥፍራ ሁሉ ጦሩ ጥሩ የጀግና ስም ማትረፍ ችሏል። ከድርጅቱ ቀስቃሽ መዝሙር በተጨማሪ ጥቁር አንበሳ የጀግና ስም ማትረፍ የቻለው ድርጅቱ ጠንካራ የመተዳደሪያ ደንብና ሕግ ስለነበረው ነበር።
ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ውስጡን ያቃጥለው ነበርና በየጊዜው ጦሩን የጀግኖችን አባቶቻችንን ክብር ሳናበላሽ ለጠላት ተዋርደን ሳንገዛ የንጉሠ ነገሥቱን አደራ ሳናጠፋ እስከ መጨረሻው ተጋፍጠን መዋጋት አለብን እያለ የጀግኖችን ወኔ የሚቀሰቅስ ድምፅ እያሰማ ይሰብክ ነበር። በ1928 ዓመት ምሕረት ጦሩ ለቀምት ላይ እንዳለ ሦስት የጠላት አውሮፕላኖች አንዣበው በቦንያ ባረፉ ጊዜ፤ ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ የጠላትን ጦር ተመልክተን እንዴት ልናልፋቸው እንችላለን በማለት ጉዳዩ በኮሚቴ ተጠንቶ ከተወሰነ በኋላ አውሮፕላኖቹን ለማቃጠል ቁርጥ አሳብ እንዲደረግ በጽኑ የመከረ ቆራጥ መኮንን ነው።
በሌላም በኩል የአውሮፕላኖቹ ጥፋት የበለጠ ጉዳት አስከትሎ እኛንም ሆነ ሕዝቡን ይጎዳን ይሆናል ተብሎ በተገመተ ጊዜ መኮንኑ አስቀድመን ተፈልገን ከምንጠፋ እኛ አጥፍተን መጥፋት አለብን በማለት ለኮምቴው አደፋፍሮ ከገለጸ በኋላ በድፍረቱ ተዋጊውን ጦር አስከትሎ አውሮፕላኖቹ ወደ አረፉበት ሥፍራ ጉዞውን አመራ። ከዚያም ስለአጠቃቁ ዘዴና ፕላን እየሰጡ ከተጠጉ በኋላ በ12 ሰዓት ላይ ሲሆን ለግጥሚያው ትእዛዝ የሰጠ ነው። ጠላት የመትረየስና የጠመንጃ እሮምታ ሲተኮስባቸው ተዋጊው የጥቁር አንበሳም የተኩስ መልስ በመስጠቱ ሦስቱም አውሮፕላኖች ሲቃጠሉ አስር የሚሆኑ ከፍተኛ የፋሽስት ጦር መኮንኖች አብረው ሲቃጠሉ የተሳካውን ድንቅ ኦፕሬዥን የመራው ጀግናው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ነበር።
መኮንኑ የሰጠው ትእዛዝ በመልካም ተከናውኖ በድል አድራጊነት ሲመለስ የጠላት ባንዲራ ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተማርኮ ስለነበረ ከፈረሱ ጭራ ላይ አስሮ መሬት ለመሬት እየጎተተ ወደ ጠቅላይ ጦር ሠፈሩ ተመለሰ። በአዲስ አበባ እስከ ለቀምት በነበረው ዘመቻም ሆነ በዚህ ዕለት ባደረገው ሞያ መላው ጦሩ ስለአቀፈውና ስለወደደው ታዛዥነቱን ከልብ አደረገ።
በዚህ ጊዜ ነበር ታዋቂው አርበኛና ባለ ቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ የጦሩን ሞራል ከፍ ለማድረግ
እናት ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
በሶስቱ ቀለማት የተሸለምሽቱ፣
ላንች የማይረዳ ሳለ በሕይወቱ፣
በረከትሽ ይንሣው እስከ ዕለተ ሞቱ።
ሲሉ የገጠሙና ሕዝቡን ለነለጠ ተጋድሎ ያነሳሱት።
ከተሳካው የቦንያ ኦፕሬሽን በኋላ ሌተናት ኮሎኔል በላይ የጠላት ወደ አውራጃው መምጣትን በመረጃ እየተከታተለ ጦሩ በአደጋ እንዳይጎዳበት ዘዴና ፕላን በማውጣትና ሐሳቡንም ለኮሚቴው በሚያቀርብበት ጊዜ ትክለኛና የማያወላውል መኮንን መሆኑን በበለጠ ማስመስከር ቻለ።
ከቆይታ በኋላ የጦሩ ለቀምት በመቆየት በአገረ ገዢው በተጠላ ጊዜና እንዲለቁላቸውም ተጠይቀው ስለነበረ በእምቢታ ቢቆዩ ጦሩ አደጋ ላይ ሳይወድቅ አይቀርም በማለት ወደ ጎሬ ሄዶ በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም ሲታሰብ መኮንኑ ትክክለኛ ሐሳብ መሆኑን ያስረዳ ነበር። ከልዑም ራስ እምሩ ጋር በመገናኘት ሐሳብ ለሐሳብ ሲለዋወጡ ልዑልነታቸው የጎሬውን ጦር መፈታት አይነት ለጥሊያን እጅ ለመስጠትና ወደ ስደት ለመሄድ ሲያስቡ መኮንኑ ግን ወደ ወለጋ ተመልሶ ጠላትን ተከትሎ መውጋት የተሻለ ነው ሲል ክርክር አቅርቦ የሌሎቹን ልብ ለመማረክ በመቻሉ ወደ ወለጋ ያለውን ጉዞ በማደፋፈር ጉይ ላይ የሚደረገውን ከባድ ጦርነት ድል ለመንሳት የሚረዳውን የውጊያ ስልት መስጠት ጀመረ።
ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ የአዛዥነቱን ሥልጣን በማጠንከር በየቦታው አዋግቶና ተዋግቶ ለገጠመው ችግር መካች ሆኖ የጦሩን መንፈስ ከማበረታታት ያልተመለሰ ጀግና ነበር።
እንዲሁም የጦር መስመሩ ወደ ጂማ እንዲዛወር ተቆርጦ በሚጓዝበት ጊዜ የሀገሬውን ንብረትና ሀብት እንዳይዘረፍ ወይንም እንዳይበላሽ ከፍ ያለ መቆጣጠርና ሥነ ሥርዓትም እንዲከበር ጥብቅ ትእዛዝ በመስጠት በትክክል የመራ ነው። ጦሩም ጉማ በደረሰ ጊዜ ጅማ ድረስ ሄዶ ጠላትን ለመውጋት ለቀረበው ሐሳብ አንደኛው ዘዴ ሰጭ ነበረ። በየመንገዱ በደረሰበት አደጋ ተስፋ እንዳይቆርጥ የጦርነቱም መከራ እያንዳያንደገግፈው ሲያበረታታ የቆየ ነው። ለቀምት እንደገቡ የነበራቸው ብዛት 400 መሆኑን እንዳስረዳነው በየጊዜው በደረሰው አደጋ በጠቅላላው 250 ሰዎች ያህል ሲሞቱ ምንም ቅር ሳይላቸው እነርሱም ተራቸውን ለመቀበል የሚሽቀዳደሙት የዚህ መኮንን ቆራጥ አዛዥነት በሚሰጠው ጽኑ እምነት ነበር።
ልበ ሙሉ የሆነው መኮንን ጦሩን እያደፋፈረና እያጽናና ጎጀብ ሲደርስ ከወዳጅ ጠላት ወጥመድ ሲገባ ቆራጡ መኮንን ከመማረኩ በፊት ተታኩሶ ከጠላት ክበብ ውስጥ የቻለ እንዲያመልጥ ቆርጦ ነበረ፤ ነገር ግን የመጨረሻው ሐሳብ ተማጽነው የተጠጓቸው ሕጻናትና ሽማግሌዎች አናስፈጅም በማለት መማረክ ስለተመረጠ መኮንኑ በጠላት እጂ ቢወድቅም ልቡን ለጠላት ሳይሰጥ በምርኮ እንደተጉላላ ጂማ ድረስ ሲመጣ ከዚያም በስቃይ አዲስ አበባ ታስሮ ደረሰ።
በዚህ መሠረት አዲስ አበባ እንደገባ በከባድ ተግሣጽ ይቅርታ ተደርጎላቸው ለሞታቸው አጋጣሚ ጊዜ ይጠበቅላቸው ስለ ነበረ፡ ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ለጊዜው ሕይወታቸው ከሞት ቢተርፍም በማናቸውም ጊዜ እንደሚገድሉት ያውቅ ነበረና ከጠላት ከበባ ውስጥ ወጥቶ በአርበኛነት የሚሰራበትን ጊዜ ሲጠባበቅ በግራዚያኒ ላይ የቦንብ አደጋ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በተደረገው ምክንያት ጠላት የፍላጎቱ መፈጸሚያ ስላገኘ ይዘው አስረውት የአደጋው ተባባሪ ነህ በማለት ሲገድሉት ከብዙ መኳንንንቶችና መኮንኖች ጋር በእግር ብረት ታሰረ።
ወንጀል ሰርተሃል በተባለበት ጥፋት ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ብዙዎቹ እየተጠሩ ከባድ ስቃይና የሞት ፍርድም ሲፈጸምባቸው ቆይቶ የሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ተራ ሲደርስ ተጠርቶ በአንድ ሃምሳ አለቃ ተይዞ ወደ ምርመራው ሥፍራ እንዲሄድ ቢጠየቅ፣ መሞቱን ያረጋገጠው ቆራጡ መኮንን «እኔ ሌተናት ኮሎኔሉ በአንድ የበታች ሹም ታጅቤ ለመሄድ ክብሬ አይፈቅድልኝም፤ ይህንን አድርጌ ያስተማረችኝን እናት አገሬን ሊያዋርዷት በመጡ ጠላቶቿ ፊት አላዋርድም፤ ቢፈልግ አዛዡ ይምጣና እሄዳለሁ» ሲል መለሰለት። የሃምሳ አለቃው ወደ ምርመራው ሹም ሄዶ «በአንድ አነስተኛ ሹም ተይዤ አልመጣም» ማለቱን ለበላይ አለቃው አመለከተ።
በዚህ ጊዜ ሌላ ሻምበል ይዞት እንዲመጣ ተደርጎ ሻምበሉም ትእዛዙን ነግሮ እንዲከተለው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብን ቢጠይቀው «ክብሬ አንተን ከመሰለ ጋር ለመሄድ አይፈቅድልኝምና እምቢ» ሲል በድጋሜ ገለጸ። ከዚህ በኋላ ሌላ አንድ ኮሎኔል ቢላክበት «ካንተ ጋር ለመሄድ ቅር አይለኝም» ብሎ በመከተሉ አጃቢውም መኮንን የቆራጡን መኮንን ኩሩ መንፈስ አድንቆ የሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብን አክብሮት በመፈጸም በቀኝ በኩል ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ አጃቢው በግራ በኩል ሆነው ወደ ምርመራው ቦታ ደረሱ።
በዚህ ወቅት ሌተናት ኮሎኔል በላይ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ሲጠየቅ ያለፍርሃትና ያለ ድንጋጤ «አገሬን ልወሩ የመጡ ብዙ ፋሽስት ጥሊያኖችን በማስጣቴ ደስታዬ ወሰን የለውም፤ ለሃገሬ፣ ለባንዲራዬና ለንጉሠ ነገሥቴ ስል የመጣውን አጥቂ ለመመከትም ሆነ ለማጥፋት የገባሁበትን የወታደርነት ቃልጊካድንና የኢትዮጵያዊነቴን ግዴታ ፈጽሜያለሁ» ሲል ተናገረ። ፋሽስቶቹም ይህንን መልስ በሰሙ ጊዜ የሌተናት ኮሎኔል በላይ ቆራጥ ወታደርና ጀግና ኢትዮጵያዊ መሆኑን ስላስገመተ ለወደፊት ለፋስት መንግሥት የማይገዛ አደገኛ እንደሆነ በመረዳት የሞት ቅጣት እንዲቀበል ፈረዱበት። የሞት ቅጣቱንም መጀመሪያ ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ወስደው ቦሩ ሜዳ ላይ አቶ ኃይለ አብ አባቱ ባሉበት ስፍራ ይኸውልህ ዓመጸኛ ልጅህን ተሰናበተው፤ ሊገደል ነው ብለው በአውሮላን ወደ ወለጋ በቦንያ ወስደው ከነሕይወቱ ከአውሮፕላን ውስጥ አውጥተው ወርውረው ገደሉት።
በስሩ ባሉ ወታደሮች ዘንድ በመልኩ የቀይ ዳማ፣ ቁመቱ አጠር ያለ፣ በአለባበሱና በአረማመዱ ቀልጣፋነት ያለው፣ንግግሩ የጣፈጠና ጦሩ በሙሉ የፍቅር አይን የጣለበት በሚል ይገለጽ የነበረው ጀግናው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ለአገሩ የሚገባውን አድርጎ የሞት ጽዋን በፍቃዱ ለአገሩ ሲል ጨለጠ። በለቀምት የወታደር አሠልጣኝነትና የጠቅላይ አዛዥነት ኃለፊነት ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ ጦሩን በሥልጣኔ ከማራመዱ በላይ «ስለ አገራችን ነጻነትና እለንጉሠ ነገሥታችን ፍቅር ብንሞት በክብር እንወዳለን። ይህችን ነጻነት አባቶቻችን በአጥንታቸው መሥርተው በደማቸው ዋጅተው በአደራ ስላስረከቡን አደራችንን ሳናጠፋ እንደጠበቅን እንሞታለን እንጂ እኛ ለጠላት ተዋርደን የጅግናይቱን እናታችንን ክብር አናዋርድም» እንዳለው ሰማዕት ለመሆን በቃ።
ጀግናው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ በጉዞ ጊዜ በፈረስ ሆኖ ዘወትር የሚሄደው ከግንባር ቀመድ ጦር ጋር ነበር። እንዲሁም ጦርነት በተጀመረ ጊዜ ሽጉጡን መዝዞ ከወታደር ፊት ፊት እየሮጠ የውጊያውን ጉዳይ ያከናውን ነበር እንጂ እንደጠቅላይ የጦር አዛዥ ይቅርና መካከለኛ ማዕረግ እንዳለው መኮንን እንኳ ከወታደር ኋላ ወይንም በአማካኝ ሥፍራ መገኘት ሞት ይመስለው ነበር።
ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ በሕይወቱ መስዕዋት ለከፈለላት ልጇ ለታላቁ አርበኛ ለሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ታሪኩ እንዳይጠፋና ተግባሩ በትውልዶች ሁሉ እንዳይረሳ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለባለውለታው መኮንን በ1950 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ትምህርት ቤት ታድሶ ሲመረቅ የመኮንኑ ጀግንነትና ባለ ውለታ ለመሆኑ ተመስክሮ ጥሩ የወታደር አዛዥ ከመሆኑም በላይ በአደረገው አመራር የሚያስደስት ጀብዱ ስለሠራ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የጦር ሜዳይ ከሁለት ዘንባባ ጋር እንዲሁም ያንድ ዓመት ያርበኛነት ሜዳይ ከአንድ ዘንባባ ጋር ተሸልሟል። ከዚህ በተጨማሪ የጦር ትምህርት ቤቱ ውስጥ ሐውልት ቆሞለት በስሙም መጥሪያ የሚሆን የተማሪዎች መኝታ መንደር ተሰይሞለታል።
ይህንን ሁሉ ጀብዱ የፈጸሙት ኢትዮጵያዊ ጀግና በግፍ ሲገደሉ እድሜያቸው ሀያ አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ነበር። ስማቸው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ይባላል። ልብ በሉ! ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ያንን ሁሉ ታሪክ የሰሩት የ21 አመት ልጅ ሆነው ነው። ከወረራው በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በገነት ጦር ትምህርት ቤት ውስጥ መታሰቢያ አቁመውላቸው ነበር። ለእናት አገራቸው መተኪያ የሌለው መስዕዋትነት የከፈሉት የነ በላይ ኃይለ አብ መታሰቢያ የሚገኝበት ታሪካዊው የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ኢትዮጵያን ለማፍረስና የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት በታገለው በወያኔው ሐየሎም አርአያ ስም ይጠራል።
ጀግናው ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ የተወለዱት በ1908 ዓ.ም. ሲሆን ትውልዳቸው ከመረብ ማዶ ከባህረ ነጋሽ ነው። እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዛችን ብለው ሊወጓት ጫካ ቢገቡና ቢያደሟትም እነ ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ግን ለእናት አገራቸው ኢትዮጵያ የሞት ጽዋን ተቀብለዋል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቷንና የጠላቶቿን ሁሉ የጡት አባት ጨካኙን ኢሳያስ አፈወርቂን በየ ሳምንቱ በክብር ስትቀበል ስለ እሷ የወደቀውን ጀግናውን ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብን ግን የምታስታውስበት አፍታ የላትም፤ አትፈልግምም! የሷ ጀግኖችና ክብር የሚገባቸው ሊጥሏት የተነሱት የሻዕብያው አምበል ኢሳያስ አፈወርቂና ደቂቆቹ ናቸው። ለዚህም ነበር ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ፤
ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤
ሲሉ ዘመን የማይሽረው ሀሳብ ቋጥረው ያለፉት!
ክብር ለታላቁ ጀግና ለኢትዮጵያዊው ሰማዕት ለሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ!!