
ከ 6 ሰአት በፊት
አንዳንድ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ እና የኬንያ አካባቢዎች ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ አላገኙም። በዚህም ሳቢያ ሚሊዮኖችን ለምግብ እጥረት እንደሚያጋልጥ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ሲገልጽ፣ የዓለም ጤና ድርጅት አሃዙን 24 ሚሊዮን ያደርሰዋል።
በዚህም ሳቢያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭት ምክንያት እርዳታ ጠባቂ ለሆኑ ኢትዮጵያውን ድጋፍ ለማድረግ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አሳውቋል።
ከዚህ አንጻር ለተከታታይ ወቅቶች የተከሰተው የዝናብ መታጣት ሊያስከትል የሚችለው ውጤት እየታወቀ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ምን ሲሠሩ ቆዩ? አሁንስ ምን እያደረጉ ነው የሚል ጥያቄን ጭሯል።
በተጨማሪም በተለይ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑት አካባቢዎች ለረዥም ዓመታት ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የቆዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚናንም ጥያቄ ውስጥ ከቷል።
በአገሪቱ ውስጥ በፌደራል ደረጃ የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች [የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ወይም በተለምዶ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች] ከ4400 በላይ እንደሆኑ የመዝጋቢው አካል መረጃ ያመለክታል።
ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት “ባለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል በዘርፉ መሥራት እንፈልጋለን ብለው የተመዘገቡ” ናቸው።
ላለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ በተከሰተው ድርቅ እና የምግብ እጥረት ሳቢያ ክፉኛ ከተጎዱት አካባቢዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ውስጥ ብቻ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
- ተመድ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገለጸ1 መጋቢት 2023
- “ቦረና ውስጥ ያለው ሁኔታ ለማየት እንኳን የሚከብድ ነው” አብነት ከበደ28 የካቲት 2023
- “የ16 ዓመት ልጄ በረሃብ ምክንያት ሞተ” በቦረና የሚኖሩ አባት24 የካቲት 2023
በረጂ ፍላጎት ላይ መመስረት
አቶ ገልገሎ ኦኩቱ በመንግሥታዊው የአደጋ መከላከል ውስጥ ሠርተዋል። አሁን አልቺሶ ፓስቾራሊስት አፕ የሚባለው አገር በቀል ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው።
በቦረና ዞን ብቻ ከ40 በላይ የሚሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቢኖሩም “ለዓመታት የተንከባለለውን የአካባቢውን ችግር መቅረፍ አልቻሉም” ሲሉ ይገልጻሉ።
ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በለጋሾች ፍላጎት መመራታቸው [ዶነር ድሪቭን መሆናቸው] እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
“ይህም ማለት እንደ ለጋሾቹ ፍላጎት ብቻ ነው የምትሄደው። ወይም የሚገኘውን ገንዘቡ ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተዛመደ አስፈላጊ በሆነ ተግባር ላይ ማዋል አይቻልም” ይላሉ።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላም “በለጋሾች ፍላጎት የመመራት ሁኔታን እናያለን። አንድ ድርጅት ድጋፍ ካገኘ ጤና ላይ ሊሠራ ይችላል። [ያው ድርጅት] ድጋፍ ካገኘ በትምህርት፣ በሥነ ጾታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሠላም. . . ላይ ሊሠራም ይችላል” ብለዋል።
አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰቦች ሕግ ደግሞ ድርጅቶቹን በዚህ ዓላማ ዙሪያ አትሠሩም ባይልም ባለሥልጣኑ “በተወሰነ ነገር ላይ ብታተኩሩ” የሚል ሃሳብ ይሰጣል። ብዙዎች ግን አሁንም በበርካታ ዘርፎች ላይ መሠማራትን ይመርጣሉ።
የያቤሎ ከተማ ነዋሪውና በቦረና ባህል ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጡት አቶ ጃተኒ ዲዳ ደግሞ በበኩላቸው ድርጅቶቹ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ አለመሆናቸውን ያነሳሉ።
“መንግሥት ድርጅቶቹ እንዲሠሩ የማይፈቅድላቸው ዘርፎች አሉ። ለምሳሌ እንደአድቮከሲ ያሉትን እንዲሠሩ አይፈቅዱላቸውም። ከድርቅ ጋር በተገናኘ የአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ላይ ለመሥራትም ካልተፈቀደላቸው በስተቀር መሳተፍ አይችሉም” ይላሉ።
ነገር ግን መንግሥት አንድ ድርጅት ከተመዘገቡበት ዓላማ፤ ከኢትዮጵያ ሕግ እና ከሕዝብ ሞራል ተቃራኒ እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም መስክ መሥራት እንደሚችል ይገልጻል።
የውጭ ድርጅቶች ከፖለቲካ አድቮከሲ እና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ መሥራት ተከልክለዋል። ከዚያ ውጪ “ማንኛውም ድርጅት የገቢ ምንጩ ሕጋዊ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም ሕጋዊ መስክ መሥራት ይችላል” ይላሉ አቶ ፋሲካው።
እንደ አቶ ጃተኒ ድርጅቶቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ ካደረጋቸው ነገሮች መካከል ሌላኛው፣ ሕብረተሰቡ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የማያውቁ ሠራተኞችን እና ኃላፊዎችን መቅጠራቸው እንደሆነ ያምናሉ።
ስማቸው እንዳይተቀስ የፈለጉና ቢቢሲ ያናገራቸው በትግራይ የሚንቀሳቀስ የውጭ የእርዳታ ድርጅትን የሚመሩ አንድ ግለሰብ፤ ላለፉት 30 ዓመታት በእርዳታ ድርጅት መሥራታቸውን ይገልጻሉ።
በድርጅቶቹ ውጤታማነት ላይ “በክልሉ ከነበረው ሁኔታ አኳያ ሕብረተሰቡን ከመለወጥ ብቻም ሳይሆን የአደጋ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድም አጥጋቢ አልነበሩም” ይላሉ።
የፀጥታ ችግር እና ትግራይ ላይ የቆየው ‘ከበባ’ የፈጠረው የግብአቶች እጥረት ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።
“የሠራተኞች እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ቁርጠኝነት ላይ ችግር ነበር የሚል እምነት የለኝም። የደኅንነት እና የከበባው ጉዳይ ነው ውስብስብ የነበረው። እንጂ’ማ ብዙ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ሕይወት እስከ መክፈል ደርሰዋል” ሲሉ አክለዋል።
“ውጤታማነታቸው ሲታይ ግን በጣም አጋዥ ነበሩ” የሚሉት ኃላፊው ይህ ግን ከድርጅት ድርጅት እንደሚለያይ ይገልጻሉ።

“የጠባቂነት መንፈስ”
ከእርዳታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ድርጅቶቹ በሕዝቡ ዘንድ የጠባቂነት መንፈስ እንዲፈጠር አድርገዋል የሚል አስተያየትም ይሰጣል።
“እንደ ግድብ፣ ውሃ የማቆር፣ የከብት ግጦሽ አስተዳደር . . . ያሉ ለረዥም ጊዜ የሚያገለግሉ ፕሮጀክቶችን ሳይሆኑ ትንንሽ ነገሮችን በመስጠት ሕዝቡ ጥገኝነት ተማረ። ሕዝቡ በፊት የነበረው የግጦሽ፣ የመሬት እና የአካባቢ አስተዳደር ባህሉ ጠፍቷል” ሲሉ አቶ ገልገሎ ሃሳቡን ያብራራሉ።
ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎችም በዘላቂነት ለውጥ ከሚያስገኝ ድጋፍ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ከለጋሽ ድርጅቶች ስለሚያገኙት ጥቅም መጠየቅ ጀምረዋልም ይላሉ።
ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ የሚገልጹት በትግራይ የሚሠሩት የእርዳታ ድርጅት ኃላፊው፤ የድርጅቶቹ ድጋፍ ከዕለት ጉርስ አልፎ ሽግግር ወደ ሚፈጥሩ ሥራዎች ማደግ እንዳለበት ያምናሉ።
“ሰው በልቶ የሚያድረው ሲያጣ እርዳታ መጠበቁ ነውር አለው ብዬ አላስብም። ቆይቶ ግን እርዳታዎቹ እንደ ሴፍቲ ኔት ወዳሉ የዘላቂ ልማት ፕሮግራሞች በመቀየራቸው ችግንሩ ማቃለል ይቻላል” ብለዋል።
አንዳንድ ድርጅቶቹም ድጋፈ እና ዘላቂ የኑሮ ለውጥ ከሚያስፈልገው በችግር ውስጥ ካለው ሕዝብ ይልቅ የተቀጣሪዎቻቸውን ሕይወት መቀየሪያ መንገድ ሆነዋልም ይላሉ።
እንደ አቶ ገልገሎ ሌላው ትልቅ እንቅፋት የተለያዩ ድርጅቶች በአንድ አካባቢ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተመሳሳይነት ወይም መደራረብ ነው።
“አንዱ ድርጅት እዚህ ጋር በውሃ ላይ የሚሠራ ከሆነ ሌላውም ይመጣና ተመሳሳዩን ሥራ ይሠራል” በማለት የሕዝቡን ችግር በሚለውጡ የተለያዩ ዘርፎች ላይ አለመሰማራታቸው ሥራቸው በአንድ በተወሰነ መስክ ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆናል።
የሚደረግ ክትትል
ሌላው ደግሞ ለበርካታ ዓመታት በአንድ አካባቢ ላይ ሠርተው ጠብ ያለ ነገር መፍጠር ያልቻሉ ድርጅቶች መኖራቸው ተደጋግሞ ይነሳል።
አንድ ድርጅት ተመሳሳይ ነገር ለ20 እና 30 ዓመታት መሥራቱ የሚያኩራራ አይደለም የሚሉት አቶ ፋሲካው “ይህን ውድቀት ነው ብለን ነው የምንጠቅሰው። አንድ ድርጅት ከነዋሪው ጋር ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ ፈጥሮ ችግር ወዳለበት ሌላ አካባቢ ሄዶ መሥራት ሲችል ነው ውጤታማ የሚባለው” ይላሉ።
መንግሥት ለዚህም ቁጥጥር ሥርዓት ዘርጋቻለሁ ይላል። ሁሉንም ነገር ከመቆጣጠር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ራሳቸውንም መቆጣጠር (ሰልፍ ሬጉሌት) ማድርግ አለባቸው ብሎ ያምናል።
“ተቋማቱ ለሕግ ታምነው የሚሠሩ እንጂ መንግሥት አየኝ አላየኝ ብለው የሚሠሩ መሆን የለባቸው፤ መንግሥትም ይህንን አይፈልግም” ይላሉ አቶ ፋሲካው።
አክለውም ይህ የቁጥጥር ዓላማ ግን ለመቅጣት እና እርምጃ ለመውሰድ አይደለም በማለት “መደገፍ ላይ እናተኩራለን። የህግ ጥሰት ካለም ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣ የማገድ እና ድርጅቱ መሰረዝ ካለበት ለቦርድ አቅርቦ እንዲሰረዝ ይደረጋል” ይላሉ አቶ ፋሲካው።
በዚህ መሠረት ባለፉት ዓመታት ለተለያየ ጊዜ ታግደው ክፍተታቸውን አርመው ሥራ የጀመሩ እንዲሁም ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የፈረሱም አሉ።
“ፋይናንሳቸውን ጨምሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምን እየሰሩ እንደሆነ እናውቃለን። መረጃውም አለን። የተለያዩ ሪፖርቶችም ይደርሱናል” ይላሉ።

በጋራ መሥራት
ቁጥጥሩንም በተመለከተ መንግሥት በወከለው አካል የሚመራ ኢመርጀንሲ ኮኦርዲኔሽን ሴንተር (ኢሲሲ) የሚባል መድረክ መኖሩን በትግራይ ክልል ያለ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ሁሉም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ የመንግሥት እና የተቋማቱ ኃላፊዎች በየሳምንቱ እየተገናኘን የምንነጋገርበትና የምንገመግምበት መድረክ ነው” ይላሉ።
ድርጅቶቹ በየሩብ ዓመቱ ለመንግሥት ሪፖርት አንደሚያቀርቡ እና በየጊዜው ከሚመለከተው ሴክተር መሥሪያ ቤት ጋር እንደሚገናኙም ይገልጻሉ።
በሕጉ መሠረትም ሥራቸውን ብቻ እየሰሩ ስለመሆናቸው፣ በዕቅድ የተያዙ ሥራዎችን ስለመከወናቸው፣ የተፈለገው ማኅበረሰብ ጋር በአግባቡ ተደራሽ መሆናቸው ዝርዝር ቁጥጥር እንሚደረግ ይነገራል።
በግምግማው መሠረትም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ለድርጅቶቹ የሚገለጽ ሲሆን “ነገር ግን መጠናከር አለበት ብዬ አምናለሁ” ይላሉ በትግራይ ክልሉ የሚንሳቀሰው ድርጅት ኃላፊ።
በተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለይ ደግሞ በድርቅ ምክንያት ሰዎች ለችግር እና ለመፈናቀል ሲዳረጉ በየአካባቦወቹ ያሉ የረድኤት ድርጅቶች ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የሚጠበቅባቸውን ስለመወጣታቸው በርካቶች ይጠይቃሉ።
አቶ ፋሲካው እንደሚሉት የእርዳታ ድርጅቶቹ በድርቅ፣ በጎርፍ እና በጦርነት ምክንያት ሕዝቡ ጉዳት ሲደርስበት ከማንም ቀድመው የመደገፍ ኃላፊነት አለባቸው።
ከዚህ አንጻር “በእኛ ግምገማ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል። ካለው ችግር አንጻር በቂ ባይሆንም ቀላል የማይባል ሥራ ግን ሠርተዋል። የሚበረታታ ብዙዎችን የሚደገፍ ሥራም ሠርተዋል” በማለት መመስገን እንሚገባቸው ጠቅሰዋል።
አሁን በስፋት መነጋገሪያ በሆነው የቦረና አካባቢ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ ቀርቦ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰበሰብ እና የሚያቀናጅ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ከዚህ አንጻርም የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ ፋሲካው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ገልገሎ ሕብረተሰቡ በአብዛኛው የመንግሥት ኃላፊዎችን ወይንም ተወካዮችን ይቀበላል ይላሉ።
“ስለዚህም እነዚህ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በቅንጅት በመሥራት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላሉ” ብለው ያምናሉ።