March 3, 2023 – BBC Amharic 

ወፍራም ሴት

ከ 5 ሰአት በፊት

በአውሮፓውያኑ 2035 ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ‘ወፍራም’ ወይም ‘ከልክ ያለፈ ክብደት’ ያለው ተብሎ ሊመደብ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።

የዓለም ኦቢሲቲ ፌዴሬሽን አፋጣኝ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ከአንድ አስርት ዓመታት በኋላ አራት ቢሊዮን ሕዝብ ለጤና አስጊ የሆነ ክብደት ይኖረዋል ብሏል።

አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ እና ኢሲያ አገራት ደግሞ ከልክ ያለፈ ክብደት ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ጭማሪ የሚታይባቸው አገራት ሊሆኑ እንደሚችሉ ፌዴሬሽኑ ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል።

በብዛት ከመጠን ያለፈ ክብደት የሚኖራቸው ሕጻናት እና አፍላ ወጣቶች እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ከልክ ካለፈ ውፍረት ጋር ተያይዞ የዓለም ዓመታዊ ወጪ 4 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሉዊስ ቦር የሪፖርቱ ግኝቶች አገራት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ ካልሆነ ደግሞ ወደፊት ለሚመጣው አደጋ እንዲዘጋጁ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ከልክ ያለፈ ውፍረት አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ በሪፖርቱ የተመላከተ ሲሆን፤ በመላው ዓለም ከሚገኙ አገራት በዜጎች ውፍረት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ከሚገጥማቸው ቀዳሚ 10 አገራት መካከል 9ኙ በአፍሪካ እና በኢሲያ የሚገኙ አስተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ናቸው።

የሰዎች ክብደት ከልክ እንዲያልፍ ምክንያት ናቸው ከተባሉት መካከል በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መመገብ ማዝወተር፣ የአካል እንቅስቃሴ ያለማድረግ ባህሪ መጨመር፣ የምግብ አቅርቦት እና ገበያ ፖሊስ ቁጥጥር ደካማ መሆን እንዲሁም ክብደትን ስለመቆጣጠር እንዲሁም የጤና ትምህርት ትኩረት አለማግኘት ተጠቃሽ ናቸው።

ሪፖርቱ በመላው ዓለም ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚኖራቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩ በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብሏል።