March 3, 2023 – BBC Amharic 

ብሊንከን (ቀኝ) እና ላቭሮቭ (ግራ)

ከ 5 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን “ዩክሬን ላይ የተከፈተው ወረራ ይቁም” ሲሉ ለሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ።

ብሊንከን ይህን ያሉት ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ፊት ለፊት ከተገናኙ በኋላ ነው።

ሁለቱ ሚንስትሮች በሕንድ ዋና ከተማ ደልሒ እየተካሄደ ባለው የቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ላይ ነው የተገናኙት።

ብሊንከን ከጦርነቱ ባለፈ ፖል ዌላን ስተለባለ ሩሲያ ውስጥ እሥር ላይ ስለሚገኝ አሜሪካዊም ተናግረዋል።

አንድ ነባር የአሜሪካ ባለሥልጣን እንዳሉት ሁለቱ ግለሰቦች ደልሒ ላይ ያደረጉት ውይይት ከአስር ደቂቃ በታች የወሰደ ነው።

ባለሥልጣኑ እንደሚሉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካው አቻቸው የቀረባበቸውን ወቀሳ ሲያጣጥሉ ነበር።

“ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ የነገርኳቸው ከዚህ ቀድም ለተባበሩት መንግሥታት ያልኩትንና የቡድን 20 ሃገራትም የሚጋሩት ነገር ነው። ወረራው ይቁም። ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እንፍታው። ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ይስፈን” ሲሉ ብሊንከን ከውይይታቸው በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አልፎም ሩሲያ ‘ስታርት’ የተሰኘው የኒውክሌር መሣሪያ ስምምነት መልሳ እንድትፈርም ለሰርጌ እንደነገራቸው ገልጠዋል።

ሩሲያው ከዚህ ስምምነት ራሷን ማግለሏ “ኃላፊነት የጎደለው” ነው ብለዋል ብሊንከን።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርያ ዛካሮቫ ሁለቱ ባለሥልጣናት እንደተገናኙ ቢያረጋግጡም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ሚኒስትር ብሊንከንና የሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት ጥር 2022 ጀኔቫ ውስጥ ነበር።

ሐሙስ ዕለት የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ምዕራባዊያን በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ከየትኛውም ወገን ያልሆኑ ሃገራት ሩሲያን እንዲቃወሙ ያስገድዳሉ ሲሉ ወቅሰዋል።

“የምዕራቡ ዓለም ሁሉንም ነገር መግፋት ይወዳል፤ እየገፋም ይገኛል” ብለዋል።

ሚኒስትር ላቭሮቭ ከአሜሪካው አቻቸው ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ምንም ሹክ ባይሉም ውይይታቸው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እንዳልነበር መናገር ይቻላል።

ሚኒስትሩ፤ በቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ወቅት ምዕራባዊያን፤ ዩክሬን በጦርነቱ እንድትገፋ እያስገደዱ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ብሊንከን፤ ከስብሰባው ጎንዮሽ ከተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች ጋር ለዩክሬን ድጋፍ ስለማሰባሰብ ውይይት አድርገዋል።

የዓለማችን 19 ሃብታም ሃገራትና የአውሮፓ ሕብረት የተካተቱበት የቡድን 20 ጥምረት 85 በመቶ የዓለም ምጣኔ ሃብትን ማንቀሳቀስ የሚችሉ ሃገራት ጥምረት ነው።