March 3, 2023 

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አሥረኛ ዓመት በዓለ ሲመት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ተከትሎ ነበር ቅዱስነታቸው 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት።

ከቀረቡ አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች መካከል ለመምረጥ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፤ ከካህናት፤ ከምእመናን፤ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት የተወከሉ ሲሆን ጠቅላላ ቁጥራቸው 806 የሚደርሱ መራጮች ነበሩ።

የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ከአጠቃላይ መራጮች ውስጥ 500 ድምፅ በማግኘት ነበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት።

በዚያው ዓመት የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተፈጸመው በዓለ ሲመት ቅዱስነታቸው “እኔ አባ ማትያስ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆኜ ተሾሜያለሁ::

ስለዚህ የተጣለብኝን ኃላፊነት ያለምንም አድሎና ተጽዕኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ ምእመናንና ምእመናት የሁሉም አባት ሆኜ በቅንነትና በታማኝነት፤ በፍቅርና በትኅትና አገለግላለሁ” በማለት ቃል የገቡ ሲሆን ከዚያን ቀን አንስቶ ቤተ ክርስቲያንን በታላቅ ኃላፊት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በነበረው የበዓለ ሲመት መርሐ ግብር ላይ “ቆዱስ አባት ሆይ እነዚህ እንደኛ በእኛ ዘንድ አንድ እንዲሆኑ ጠብቃቸው።” በሚለው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ቁጥር 11 ላይ በሚገኘው ኃይለ ቃል መነሻነት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው እግዚአብሔር አምላክ ከምንም በላይ መለያየትን ይጠላል ያ ባይሆን ኖሮ ለምእመናን አንድነት ሲል ደሙን ባላፈሰሰ ነበር ያሉ ሲሆን መለያየት አንዱን ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በእኩል ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም በቤተ ክርስቲያን የሚፈጠር መለያየትም ከሌላው ሁሉ በባሰ ሁኔታ የማኅበረሰብን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሕይወት በእጅጉ ይጎዳል በውጤቱም ደካማ ሀገርንና ማኅበረሰብን ይፈጥራል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ስለወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ችግር ያነሱት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን ያጋጠማትን ችግር በቀላሉ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ በንስሐ፣ በሰላምና በውይይት መፍታት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ጥቅም በመረዳት እንጂ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት ቀላል ስለሆነ አይደለም ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ሊቃነ ጳጳሳትም ምእመናን አንድ ለማድረግ እንጂ ለመበታተን ሳይሆን አንድ ለማድረግ የተሾሙ መሆናቸውን ሊዘነጉ እንደማይገባ አሳስበው ሰከን ብለን እናስብና ወደ ልባችን እንመለስ ብለዋል።

በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አፈጻጸም ከአባካኝነት፣ ከአድልዎ፣ ከዘረኝነትና ከፖለቲከኘነት ለማጽዳት በቁርጠት መሥራት አለብን። እስከመቼ በዚህ ስንታማ እንኖራለን፤ ከእንግዲህ ወዲህ በቃ! ማስተካከል አለብን! ማስተካከል አለብን! ማስተካከል አለብን ሲሉ አበክረው አሳስበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።

ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል
እውነተኛ የተዋሕዶ ድምፅ