
3 መጋቢት 2023, 13:05 EAT
ሐሙስ የካቲት 23/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተከበረው የዓድዋ በዓል አከባበር ወቅት አንድ መምህር በጥይት ተመትቶ መገደሉን የሟች ዘመድ ለቢቢሲ ተናገረ።
በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባሌ ነው ያለው መምህር ሚሊዮን ወዳጅ የዓድዋ በዓል ለማክበር በወጣበት ከመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ተመቶ መገደሉን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።
የሟች ሚሊዮን ወዳጅ የአክስት ልጅ እና የቅርብ ጓደኛ የሆነው አዲስ ኃይሌም በተመሳሳይ ለሚሊዮን ሕይወት ማለፍ በጥይት መመታቱ ምክንያት እንደሆነ ከጤና ባለሙያዎች መረዳቱን ገልጿል።
በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው የዓድዋ ድል በዓለ በሚከበርበት የምኒልክ አደባባይ ለመታደም የወጡ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች በአስለቃሽ ጭስ እና በቆመጥ መበተናቸውን በስፍራው የነበሩ ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ በአደባባዩ አካባቢ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል በርካቶች በአስለቃሽ ጭስ እና በድብደባ ተጎድተው ወደ ሐኪም ቤት መወሰዳቸው ተሰምቶ ነበር።
ኋላ ላይ ደግሞ በዚህ ግርግር መካከል በጥይት የተመቱ ሰዎች እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፣ አንድ ግለሰብም በጥይት ለሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
የሟች ሚሊዮን ዘመድ የሆነው አዲስ እንደሚለው “የዓድዋ በዓልን ምኒልክ አደባባይ ተገናኝተን ለማክበር ረቡዕ ማታ ተቀጣጥረን ነበር። እርሱ ከጎሮ ተነስቶ ቀድሞ ደረሰ። እኔ በቦታው እንደደረስኩ ደውየለት ወደ እኔ እንዲመጣ ነግሬው በመምጣት ላይ እያለ አስለቃሽ ጭስ ተተኮሰ . . .” ይላል።
ሚሊዮን ከቆይታ በኋላ ለአዲስ ደውሎለት በጭሱ ታፍኖ እንደነበር ነገር ግን ደህና እንደሆነና “ወደ እኔ እንዲመጣ ነግሬው ስልኩን ዘጋን” በማለት ሚሊዮን በጥይት ከመመታቱ በፊት የነበረውን ክስተት ለቢቢሲ ተናግሯል።
- ሊቨርፑል ከዩናይትድ፣ ሲቲ ከኒውካስል፤ የፕሪሚየር ሊግ ግምቶች3 መጋቢት 2023
- በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እና የረድኤት ድርጅቶች ሚና3 መጋቢት 2023
- ከ12 ዓመታት በኋላ ገሚሱ የዓለማችን ሕዝብ ከመጠን ያለፈ ክብደት ይኖረዋል3 መጋቢት 2023
አዲስ እንደሚለው ከጥቂት ቆይታ በኋላ በሚሊዮን ሞባይል ስልክ ይደወልለታል። ስልኩን ሲያነሳ ግን ማንነቱን ያላወቀው ሰው አስደንጋጩን ዜና ይነግረዋል።
“ትንሽ ቆይቶ ሌላ ሰው በሚሊዮን ስልክ ደውሎልኝ በጥይት ተመትቶ ወድቋል ድረስ አለኝ። . . . ከዚያ ወደ ቦታው ስሄድ መሞቱን እና ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተነገረኝ። የተወሰደበትን ሆስፒታል ሳፈላልግ አብነት ሆስፒታል መሆኑን ጠቁመውኝ እዚያው ሂጄ አገኘሁት” በማለት ያስረዳል።
ሚሊዮን ፒያሳ ምኒልክ አደባባይ አካባቢ በጥይት ከተመታ በኋላ ሕይወቱ አልፎ አብነት ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ስለአሟሟቱ ሁኔታ የጤና ባለሙያዎችን መጠየቁን አዲስ ይገልጻል።
“አሟሟቱን ስንጠይቅ በጥይት ተመትቶ በጎኑ የገባው ጥይት በሌላኛው ጎኑ እንደወጣ ነገሩን። ከዚያ ውጪ ዝርዝር መረጃ ለፖሊስ እንጂ ለእናንተ አንሰጥም አሉን” በማለት አዲስ ይናገራል።
ቢቢሲ አዲስን በስልክ ባነጋገረበት ወቅት የሟችን አስክሬን ይዘው ወደ ትውልድ አካባቢው ደቡብ ጎንደር ንፋስ መውጫ እየተጓዙ ነበር።
አዲስ እንዳለው ሟች ሚሊዮን ወዳጅ በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሲቪክስ መምህር እና የአንዲት ሴት ልጅ አባት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ደግሞ ሚሊዮን የፓርቲው አባል እንዲሁም በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህር ቤት የፊዚክስ መምህር ነበር ብሏል።
በዚህ በዓል ላይ ያጋጠመው ክስተት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ አብን የፀጥታ ኃይሎች በበዓሉ አክባሪዎች ላይ ፈጽመውታል ከተባለው ድርጊት ጋር በተያያዘ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሐሙስ አመሻሽ ላይ ሁኔታውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ በዓሉ በታሰበው መሠረት መከበሩን ገልጾ፣ ነገር ግን “በምኒልክ አደባባይ የነበረውን በዓል ለመረበሽ የፈለጉ አካላት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል” ብሏል።
በዚህም “የአደባባዩ በዓል መረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ” እንደሞከሩ እና የፀጥታ ኃይሎች ሁከት ፈጣሪዎችን ለመቆጣጠር ባደረጉት “ጥረት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ሃይማኖታዊ በዓል መስተጓጎሉን እና ምእመናን ላይ መጠነኛ ጉዳት” መድረሱን ገልጿል።
ከዚህ ባሻገር ከፖሊስም ሆነ ከሌላ የመንግሥት አካል በፀጥታ ኃይሎች እርምጃ ሕይወት ስለማለፉም ሆነ ስለደረሰ ጉዳት የተባለ ነገር የለም።