March 4, 2023 – BBC Amharic 

ተቃቅፈው የሚሳሳሙ ቤተሰቦች

ከ 6 ሰአት በፊት

ዩክሬን፣ ሩሲያ ዳግም ልትቆጣጠራት ከምትፈልገው ኩፒያንስክ ከተማ ነዋሪዎች በከፊል ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።

የካርኪቭ ግዛት ባለሥልጣናት፣ በሩሲያ ኃይሎች “የማያባራ” ጥቃት ሳቢያ ሕጻናት ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች እና ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩ ሰዎች ከተማዋን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሩሲያ የሰሜን ምሥራቅ ከተማዋን ቀደም ብሎ ተቆጣጥራት የነበረ ሲሆን ባለፈው መስከረም ዩክሬን መልሳ በቁጥጥሯ ሥር አድርጋታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በምሥራቅ ዩክሬን የምትገኘውን የባህሙት ከተማ መክበባቸውን አስታውቀዋል።

ይህን ያስታወቁት ለሩሲያ ጦር ድጋፍ የሚሰጠው ዋግነር ግሩፕ ኃላፊ ይቪኒ ፕሪጎዚን ናቸው።

የዩክሬን ጦር በበኩሉ የሩሲያ ወታደሮች በባህሙት ላይ የሚወስዱትን ጥቃት መቀጠላቸውን፣ ነገር ግን ጥቃቱን መመከት እንደቻለ ገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከደቡብ ምሥራቅ ከተማዋ ኩፒያንስክ በ130 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባህሙት ከተማ ያለው ሁኔታ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው ነበር።

በኩፒያንስክ የሚገኘው የካርኪቭ ክልል የጦር አስተዳዳር ሐሙስ ዕለት እንደገለጸው፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በከፊል እንዲወጡ የታዘዙት በሩሲያ ጥቃት ምክንያት በአካባቢው ያልተረጋጋ የጸጥታ ሁኔታ በመኖሩ ነው።

የጦር አስተዳደሩ ከተማዋን ለቀው ለሚወጡት ነዋሪዎች የመኝታ፣ የምግብ፣ የሕክምና እና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች ይደረግላቸዋል ብሏል።

ሌሎች ነዋሪዎችም አካባቢውን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ የጦር አስተዳደሩ ጨምሮ ገልጿል።

እስካሁን 812 ሕጻናት እንዲሁም 724 አካል ጉዳተኛ ሰዎች ለቀው ለመውጣት በኩፒያንስክ እና በአካባቢዋ መመዝገባቸውን ጦሩ ገልጿል።

ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በከተማዋ ውስጥ ወደ 25 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ይኖር እንደነበር ይገመታል።

በዚህ ሳምንት ጦርነት ላይ ጥናት የሚካሂደው ተቋም እንዳለው የሩሲያ ኃይሎች በሰሜን ምሥራቅ ኩፒንያስክ “ውስን የሆነ የምድር ጥቃት” እንዲሁም ከደቡብ ምሥራቅ በ80 ኪሎሜትር በምትርቀው ክሬሚና አካባቢ የአጸፋ ጥቃት መፈፀማቸውን ቀጥለዋል።

ኩፒያንስክ ወሳኝ የሆነ የባቡር መስቀለኛ መንገድ መገኛ ስትሆን ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ ከባድ ውጊያ ተካሂዶባታል።

የሩሲያ ኃይሎች ከቀናት ውጊያ በኋላም በቁጥጥራቸው ሥራ አውለዋት ለበርካታ ወራት ይዘዋት ቆይተዋል።

ሆኖም መስከረም ላይ የዩክሬን ኃይሎች መላ የካርኪቭ ግዛትን በእጃቸው ባስገቡበትና በአገሪቷ ሰሜን ምሥራቅ በኩል በፈፀሙት የአጸፋ ጥቃት ከተማዋን በራሳቸው ኃይል ቁጥጥር ሥር አውለዋታል።

ባለፈው ሚያዝያ ላይ ሩሲያ ጦሯን ከኪዬቭ አካባቢ ካስወጣች በኋላ የሚደረጉ ግስጋሴዎች እና የደቡባዊ ከተማ ኼርሶን ከተማ ነጻ መውጣት ወሳኝ የሚባሉ ለውጦች ነበሩ።

ባለፈው ወር ዩክሬን ሩሲያ ወሳኝ የሆነ አዲስ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀች መሆኑን ያስጠነቀቀች ሲሆን ባለሥልጣናትም ሞስኮ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በዩክሬን ምሥራቃዊ ግንባር አሰማርታለች ብለው ነበር።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭም፣ ሩሲያ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የጀመረችው ወረራ አንደኛ ዓመት ለማክበር “የሆነ ነገር ልትሞክር” ትችላለች ሲሉ ከአንድ ወር በፊት አስጠንቅቀው ነበር።

ይሁን እንጂ ሩሲያ በኩፒያንስክ እና ባህሙት ከምታደርገው ግስጋሴ ውጭ በጦር ግንባሩ ይህ ነው የሚባል ስኬት አልታየም።

በቴሌግራም በተጋራ ቪዲዮ ላይ የዋግነር ቡድን ኃላፊ ፕሪጎዚን፣ “ የባህሙት ዙሪያ ተከቧል” ብለዋል።

ኃላፊው ለፕሬዚደንት ዜሌንስኪ በላኩት የቀጥታ መልዕክትም “ የዋግነር ቡድን ከተማዋን እንደከበቡና አንድ መንገድ ብቻ እንደቀራቸው” በመግለጽ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ከተማዋን ጥለው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አርብ ዕለት የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ከአገሪቷ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባን እየመሩ ነው።

ስብሰባው የተካሄደው ፕሬዚደንት ፑቲን የዩክሬን ቡድን ወደ ሩሲያ ድንበር ክልል በመግባት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል ሲሉ ክስ ካሰሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

በሩሲያ የብርያንስክ ግዛት አስተዳዳሪ “ የዩክሬን የጥፋት ቡድኖች በሊዩቤቻን የድንበር መንደር ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች መኪና ላይ ተኩስ ከፍተው ሁለት ሰዎችን ገድለዋል። የአስር ዓመት ታዳጊንም አቁስለዋል” ብለዋል።

ኪዬቭ ግን ሩሲያ “ ቅስቀሳ ለማድረግ የተጠቀመችው ነው” ስትል ክሱን ውድቅ አድርገዋለች።