
ከ 8 ሰአት በፊት
የቤላሩስ ፍርድ ቤት በኖቤል ሽልማት አሸናፊው አሌስ ቢያሊያስኪን ላይ የአስር ዓመት እስር ፈረደበት።
የሕዝብን ጸጥታ በሚጥሱ ድርጊቶች ላይ ገንዘብ በማዘዋወርና ድጋፍ በማድረግም ጥፋተኛ እንደተባለ የቪያስና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል።
የኖቤል አሸናፊው ደጋፊዎች በበኩላቸው ጨቋኝ የሆነው የቤላሩስ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አገዛዝ ዝም ሊያሰኘው እየሞከረ ነው በማለት ተችተዋል።
አሌስ ቢያሊያስኪ በአውሮፓውያኑ 2022 የኖቤል የሰላም ሽልማት ካገኙ ሦስት አሸናፊዎች አንዱ ነው።
በቤላሩስ በነበረው አወዛጋቢ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል በርካቶች በአደባባይ ተቃውሞ ማድረጋቸውን ተከትሎም ነው አሌስ ከሁለት ዓመት በፊት ለእስር የተዳረገው።
የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ ገንዘብ ወደ ቤላሩስ እያሻገረ ነው በሚልም ነበር የተከሰሰው።
የአውሮፓውያኑ 2020 የምርጫ ውጤት ለተቃወሙ ሰላማዊ ሰልፈኞች ፖሊስ የጭካኔ ምላሽ መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን በርካታ የፕሬዚዳንቱ ተቺዎችም ታስረዋል።
አሌስ ከሁለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቫለንቲን ስቴፋኖቪች እና ቭላድሚር ላብኮቪች ጋር ነበር በፍርድ ቤት የቀረበው።
ስቴፋኖቪች የዘጠኝ ዓመት እስር ሲፈረድበት፣ ላብኮቪች ደግሞ ሰባት ዓመት እንደተፈረደበት በአውሮፓውያኑ 1996 በአሌስ የተቋቋመው ቪያስና የሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታውቋል።
- ከአሜሪካው ኤምአይቲ ዩኒቨርሲቲ መጥተው ለኢትዮጵያውያን ‘አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ’ ያስተማሩት ወጣቶችከ 9 ሰአት በፊት
- በዓድዋ ድል በዓል አከበባር ላይ ‘የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወስደዋል’ – ኢሰመኮ3 መጋቢት 2023
- ድርቅ እና ረሃብ፡ በኢትዮጵያ ያሉ የረድኤት ድርጅቶች ለምን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም?3 መጋቢት 2023
ሦስቱም ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉም ለፍርድ ቤቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
የአሌስ ባለቤት ችሎቱ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ሥራቸውን የተቃረነ ነው” እንዲሁም ብያኔው “ጭካኔ የተሞላበት” ስትል ገልጻዋለች።
ለእስር ከተዳረገበት ጊዜ ጀምሮ ባለቤቷ ከእስር ቤት የጻፋቸውን ደብዳቤዎች በመጥቀስ “ሁልጊዜም ደህና እንደሆነ፣ ሁሉ ነገር ጥሩ ነው ይላል። ስለ ጤንነቱ ምንም አያማርርም። እኔን ላለማበሳጨት ይሞክራል” ብላለች።
የቪያስና ቃለ አቀባይ ኮስትያ ስታርዱቤትስ በበኩላቸው በሦስቱ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተላለፈው የፍርድ ውሳኔ “ ልብ የሚሰብር ነው” ብለዋል ።
የኖቤል የሰላም ሽልማትን ሰጪው ተቋም የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሰብሳቢ ቤሪት ሪስ-አንደርሰን በበኩላቸው በአሌስ ላይ የተወሰነው ፍርድ አሳዛኝ ነው ፤እንዲሁም ክሱም ፖለቲካዊ ነው ሲሉም ተችተዋል።
አሌስ በቤላሩስ ውስጥ አንጋፋ የሚባል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነው።
በአውሮፓውያኑ 1996 እስካሁን ቤላሩስን የሚመሯት ፕሬዚዳንት ሉካሼንኮን የተቃወሙ ሰዎች ላይ በደረሰው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃም ነበር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱን ያቋቋመው።
በአውሮፓውያኑ 2011 በግብር ማጭበርበር ክስ ለሦስት ዓመታት ታስሯል።