March 4, 2023 – BBC Amharic 

ዶክተር ማርያም ማህሙድ

ከ 9 ሰአት በፊት

“በርካታ ባሎች ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡት የወንድነት መገለጫ ስለሚመስላቸው ነው እንጂ መጥፎ ሰዎች ስለሆኑ አይደለም” ትላለች ዶክተር ማርያም ማህሙድ።

ማርያም በዮርዳኖስ የሥነ አዕምሮ ሐኪም ስትሆን፤ በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ወንዶችን በማወያየት፣ በማስተማርም ትታወቃለች።

የዮርዳኖስ ዜጎችን ስለቤት ውስጥ ጥቃት በሚያስተምረው ኤስኦኤስ የህጻናት መንደር ለተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥም ተቀጥራ ትሰራለች።

ባለሙያዋ የተወሰኑ ወንዶችን ትሰብስብና ሻይ እየጠጡም በእርጋታ ትጠይቃቸዋለች።

“ባለቤትህ እንድትመታህ ትፈልጋለህ?” ቀለል አድርጋ ዶክተር ማርያም ትጠይቃለች፤ ከዚያም ባለቤታቸውን መደብደብ ከሸሪዓ ወይም ከእስልምና ሃይማኖት ሕግጋት ጋር የሚጋጭ መሆኑንም በሚገባቸው መልኩም ታሳስባለች።

ወንዶች በባለቤቶቻቸው ላይ ምን ዓይነት ‘ቁጥጥር’ ማድረግ እንዳለባቸውም በግልጽ ውይይት ይደረጋል።

“ካልተናደድክ እና ገደብ ካላበጀህላቸው ሴቶች መረን ይለቃሉ” ይላል አንድ ባል።

“ስለዚህ የምትደበድባት እንዲህ እንዳትሆን ነው?” ዶክተር ማርያም በፍጥነት ትጠይቃለች።

“በከፋ መልኩ አይደለም የምደበድባት” ይመልሳል።

“በድብደባ እና በከፋ ድብደባ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?” በማለት ባለሙያዋ ድምጿ ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይኖር ትጠይቃለች።

እሱም ይመልሳል “የከፋ ድብደባ ማለት በዓይን የሚታዩ ጉዳቶች፣ ቁስለቶች፣ እብጠቶች ወይም መድማት ሲታይ ነው” ይላል።

“ታዲያ ጭንቅላቷ ለሁለት ካልተከፈለ የከፋ አይደለም ማለት ነው?” ዶክተር ማርያም እንደገና ትጠይቃለች።

“አንድ ወይም ሁለት ጥፊ” ይላል በምላሹ ባል።

“አንድ ወይም ሁለት ጥፊ የተለመደ ነው አይደል?” ጥያቄን በማጫር ዶክተር ማርያም መድረኩን ለሌሎች ባሎች ትከፍታለች።

“ተቃዋሚህ አይደለንም፣ አቡ ሰኢድ አናስርህም” በማለትም ዶክተር ማርያ በቀልድ መልኩ እየተናገረች ይህ መድረክ ለውይይት መሆኑንም ታስረዳለች።

ነገር ግን በዚህ ውይይት ላይ ዋነኛው ነገር ወንዶች በባለቤቶቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ድብደባ ጥቃት መሆኑን ማመናቸው አንድ እርምጃ ነው።

ዮርዳኖስ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት ውስጥ ሴቶችን ከቤት ውስጥ ጥቃት ለመከላከል ሕግ በማውጣት ፈር ቀዳጅ ናት፤ ነገር ግን በአሁኑም ወቅት ከአራት ሞቶች ውስጥ አንዱ ወንዶች በቤት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጽም ግድያ ነው።

ዶክተር ማርያም ወንዶቹን ስታወያይ

“አምላክን አይፈራም”

ዶክተር ማርያም ከምታክማቸው ህሙማን መካከል አንዷ ሳራ ናት። ትክክለኛ ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችውና ሳራ ብለን የምንጠራት ይህች ሴት ለአምስት ዓመታት ያህል በየቀኑ ይደበድባት የነበረው ባሏን መጨረሻ ላይ ጥላ እንድትሄድ ያደረጋትን ምክንያት ትናገራለች።

“ነፍሰ ጡር ሆኜ ደበደበኝ፣ ከወለድኩ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደገና መታኝ። ይሄ ሁሉ አንድ ኩባያ ሻይ ባለማፍላቴ፣ በመርሳቴ ነበር። እስክሞት ድረስ ነበር የደበደበኝ” ብላለች።

በአሁኑ ጊዜ ከሁለት ትንንሽ ልጆቿ ጋር በአንድ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የምትኖር ሲሆን፣ የደረሰባት መከራና ስቃይ አሁንም በውስጧ አለ።

“አምላክን አይፈራም፤ እዚህ ያለሁበት መጠለያም ውስጥ ሰብሮም ሊገባ ይችላል” ትላለች።

ዮርዳኖስ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመከላከል ልዩ የፖሊስ ኃይል በማቋቋም በመካከለኛው ምሥራቅ የመጀመሪያዋ አገር ብትሆንም ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ሥልጣን መቀነስ አልተቻለም። ጥቃት ሪፖርት የሚያደርጉ ሴቶች በቤተሰባቸው መገለል አልፎ ተርፎም ወደ እስር ቤት መወርወር ያጋጥማቸዋል።

ሜይሱን (ትክክለኛ ስሟ አይደለም) የሚደበድባት አባቷን በተመለከተ ለዮርዳኖስ ቤተሰብ እና ታዳጊዎች ጥበቃ ፖሊስ መምሪያ በርካታ ጊዜ ሪፖርት አድርጋዋለች።

“ባለሥልጣናቱ ሁልጊዜም አባትሽ፣ ቤተሰብሽ ነው። እስር ቤት ልታሰስገቢው ትፈልጊያለሽ?” በማለት የፀፀት ስሜት እንዲሰማት ያደርጉ እንደነበር ትናገራለች ሜይሱን።

“ባህልሽን እና ወግሸን አስቢ፤ ይህ ኒውዮርክ አይደለም ይሉኛል” ብላለች።

በተደጋጋሚ ሪፖርት ብታደርግም አባቷ ተከሶ አያውቅም። የቤተሰብ ጥበቃ ቡድኑ ሜይሱንን መታረቅ አለብሽ አሏት።

“ወደ ቤትሽ ተመለሽ ያለበለዚያ እስር ቤት ትገቢያለሽ ብለው አስፈራሩኝ።”

“መጀመሪያ ቀልድ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን እሰሩኝ ስላቸው በእርግጥም እስር ቤት አስገቡኝ” በማለት የምትናገረው ሜይሱን፣ ባለሥልጣናቱ የታሰረችው ለራሷ ደኅንነት እንደሆነ እንደነገሯት ታስረዳለች።

የቤተሰብ ጥበቃ መምሪያ ለቢቢሲ እንደገለጸው ዋነኛ ዓላማቸው ሁልጊዜም “ቤተሰቡን ሳይከፋፈል መጠበቅ” ነው።

“አንዲት ሴት ተደብድቤያለሁ ብላ ሪፖርት ብታደርግ ሰውዬውን እናስረዋለን ማለት አይደለም። የእኛ ተግባር በሕጉ መሠረት ቅሬታ አቅራቢዋን መርዳት እና አማራጮችን መስጠት ነው” ስትል አንዲት ሴት ፖሊስ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሜይሱን ለአራት ዓመታት ያህል እስር ቤት የቆየች ሲሆን፣ የዮርዳኖስ የሴቶች ማኅበር፣ ማኅበራዊ ሠራተኛ ለነጻነቷም ተደራድራ ነው ከእስር የወጣችው።

በመጨረሻም ከእስር ቤት ወጥታ በዮርዳኖስ ከሚገኙ ስድስት መጠለያዎች ውስጥ ወደ አንዱ ገባች።

እጇን ያጣመረች ሴት

በሕጉ ላይ የሚታየው ክፍተት

የሜይሱን አባት በሕይወቷ ላይ ማዘዝ ይችላል። ሜይሱን ዕድሜዋ በ30ዎቹ ላይ ሲሆን፣ ያላገባች በመሆኗ አባቷ ሥራ ከመስራት ሊያስቆማት ይችላል።

ዮርዳኖስ በአውሮፓውያኑ 2008 ባወጣችው የቤት ውስጥ ጥቃትን የተመለከተ ሕግ ለፖሊስ ተጨማሪ ሥልጣንን ሰጥታለች። ነገር ግን በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የወጣው ሕግ የቤተሰብን እርቅ አስፈላጊነት አፅንኦት መስጠቱን ቀጥሏል።

አብዛኛውን ጊዜ የግላዊ ሁኔታን የሚመለከተው የሸሪዓ ሕግ ለወንዶች በሴቶች ላይ ከፍተኛ ማዘዝ መብትን የሚሰጥ ሲሆን፣ አለመግባባቶችም ወደዚህ እንዲያመሩ ይደረጋል። የቤት ውስጥ ጥቃት ሕጉንም የሸሪዓ ሕጉ ይሽረዋል።

በዚህም መሠረት አንድ አሳዳጊ ወንድ ሴት ልጅ እስከ 30 ዓመቷ ድረስ ከቤት እንዳትወጣ በሕጋዊ መንገድ መቆጣጠር ይችላል።

ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች በወንድ ዘመዶቻቸው ቁጥጥር ስር መሆን የተለመደ ነው።

እንደ አስታራቂ በመሆንም ማኅበራዊ ሠራተኛዋ የሜይሱን አባት ከቤተሰቧ ነጻ የሚያደርጋት ስምምነት እንዲፈርም አሳመነችውና ነጻ ወጣች።

በሕይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜም በራሷ ውሳኔ መንቀሳቀስ እና ኑሯዋን መግፋት ስለመቻሏ ስታወራ በእንባ ታጥባ ነው።

“ያ ባይፈረምልኝ ኖሮ ከመጠለያ መውጣት፣ መሥራትም ሆነ ነጻ መሆን በፍጹም አልችልም ነበር” በማለት ታስረዳለች።

“ያ ፊርማ የሕይወቴ ወሳኝ ነገር ነው። ወረቀቱ ሎተሪ እንደማሸነፍ ያህል ነው” ብላለች።

ነገር ግን ለቤት ውስጥ የጥቃት ሰለባዎች የመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሌለበት አገር ውስጥ እንደ ትልቅ እመርታ ነው የታየው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ በዮርዳኖስ ከሚገኙት ሴቶች መካከል ግማሾቹ ከ30 ዓመት እድሜ በኋላ በሕብረተሰቡ ጫና ምክንያት ሥራቸውን ለቀው ወጥተዋል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ የሴቶች ሚና በቤት ውስጥ መቆየት ነው፤ በተጨማሪም በተመጣጣኝ ዋጋ የህጻናት እንክብካቤ ማዕከላት አለመኖራቸው እንዲሁም የሕዝብ ማመላሻዎች ለሴቶች ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጫና እንደሚያሳድሩ አይኤምኤፍ አሳውቋል።

ያለው የምጣኔ ሀብት ጫናም ወንዶች በሴቶች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት ላይ ሚና እንዳለው ዶክተር ማርያም ታምናለች።

“የኢኮኖሚው ቀውስ ፈታኝ እንደሆነ ለወንዶቹ እነግራቸዋለሁ። እንደሚያበሳጫችሁ አውቃለሁ እላቸዋለሁ” ትላለች።

ሆኖም “ይህ ምንም ሰበብ ሊሆን አይገባም። ለጥቃት ምክንያት አይነት ሊሰጠው አይገባም። ድብደባው ምክንያታዊ ነው ብላችሁ ብታስቡም በጭራሽ ተቀባይነት እንደሌለውም እነግራቸዋለሁ” ትላለች።

ዶክተር ማርያም እንደነዚህ አይነት ጥቃቶች ሴቶችን ሊሰብሩ ይችላሉ ይላሉ። ከሳራ ጋር በምታደርገው ቆይታም ሕይወቷን እንዴት መልሳ መገንባት እንደምትችል በመነጋገር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ።

በመጠለያዎቹ ቢበዛ ለስድስት ወራት መቆየት ለሚችሉ ሴቶች ረጅም እና በብቸኝነት የተሞላ መንገድ ነው።

የሳራ ባለቤት በፈጸመባት የከፋ ጥቃት ለሦስት ቀናት በእስር ቤት አሳልፏል፣ ነገር ግን በወሲብ ንግድ ነው የምትተዳደረው ብሎ ከሰሳት። ይህ በዮርዳኖስ ከባድ ክስ ሲሆን ልጆቿን ልታጣ እና ወደ እስር ቤትም ልትገባ ትችል ነበር።

የቤተሰብ ጥበቃ ሁኔታውን መርምሮ በመጨረሻ የባለቤቱን ክስ ውድቅ አደረገ። ሳራ ትንሽ ድል አግኝታ ነጻ ብትሆንም የባለቤቷ ዛቻ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

“ባለቤቴ ንብረቴ ናት ብሎ ያስባል። ሌላ የግድያ ሰለባ እንዳልሆንም ለሕይወቴ እሰጋለሁ” ብላለች።

መንገድ ላይ እየተራመደች ያለች ሴት