March 4, 2023

(አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ 127ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ለማክበር በተለያየ ቦታ የተሰባሰቡ ብዛት ያላቸው ሰዎች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ምንጮች ሰምታለች፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን የታተሙባቸው እንዲሁም የአጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱን ምስል የያዙ ቲሸርቶችን በመልበሳቸው ብቻ ቤተሰቦቻችን ታስረውብናል የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎችን አዲስ ማለዳ አነጋግራለች፡፡

ዓድዋ በዓልን ለማክበር ፒያሳ የነበሩና ወደ ፒያሳ ሲሄዱ ተይዘው በተለምዶ ማዕከላዊ በሚባለው እስር ቤት የታሰሩ ወጣቶች፣ ትናንት ጠዋት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ በጸጥታ ኃይሎች ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸው የታሰሩባቸው በርካታ ሰዎች ትናንት አርብ የካቲት 25/2015 በምድብ ችሎቱ ተገኝተው ሲጠባበቁ የነበረ ቢሆንም፣ ታሳሪዎች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ የተነገረው እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ይህን ምክንያት በማድረግ ወደ እስር ቤቱ የሄዱ የታሳሪ ቤተሰቦች የታሰሩ ሰዎች ፍርድ ቤት አይቀርቡም እንደተባሉ ተናግረዋል፡፡ “ታሳሪዎች የታሰሩበት ጉዳይ ቀላል ስለሆነ ፍርድ ቤት ቀርበው ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ ይፈታሉ ተብለናል” ያሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለን ነበር፣ ትላንት ጠዋትም እስከ 4 ሰዓት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ጠብቁ ስንባል ነበር፣ አሁን ደግሞ ጉዳያቸው በፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚታየው ተብለናል እርግጠኛ የሆነውን ነገር ማወቅ አልቻልንም ብለዋል፡፡

የታሰሩት ሰዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ዛሬም ፍርድ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ ተረጋግጧል፡፡

“በፌደራል ወይስ በከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ውሳኔው እንደሚወሰን አላወቅንም” ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ውሳኔው ከምን አንጻር ተመዝኖ እንደሚወሰንም ማወቅ አልቻልንም ብለዋል፡፡ የፖሊስ አመራሮችን አግኝተን ማነጋገር አልቻልንም ያሉት ምንጮቹ የሚደርሱን መረጃዎች ተቀያያሪ መሆናቸው የተባለውንም እንዳናምን አድርጎናል ብለዋል፡፡

እስከ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 25/2015 ድረስ ውሳኔው ይታወቃል እንደተባሉ አክለው የተናገሩት ምንጮች፣ ታሳሪ ቤተሰቦቻቸው ለእስር የሚዳርግ የሕግ ጥሰት አልፈጸሙም ብለዋል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ይወሰናል የተባለው ወሳኔ መወሰኑ ያልተነገረ ሲሆን፣ ታሳሪዎቸ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በተያያዘ ዜና፤ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉበት ቲሸርት በመልበሴ ምክንያት ሐሙስ ጠዋት ቤይለር አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች እንደተያዘ የተናገረ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ባልደራስ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ በእስር ከቆየ በኋላ መለቀቁን ተናግሯል፡፡ በፖሊስ ጣቢያ ቆይታው ሌሎች በርካታ ወጣቶች በለበሱት ልብስ ምክንያት ለእስር እንደተዳረጉ ማየቱን ተናግሯል፡፡

ቀኑን ሙሉ ምንም አይነት ምርመራ ባይካሄድባቸውም ምሽት 12 ሰዓት ላይ የተወሰኑት ወጣቶች እንደተለቀቁ የተናገረው የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ይሁን እንጂ ከፒያሳ አካባቢ ተይዘው ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ፖሊስ ጣቢያው የደረሱ በርካታ ወጣቶችና ከተለያዩ አካባቢዎች ተይዘው በጠዋት የታሰሩ የተወሰኑ ወጣቶች አሁንም በእስር ላይ እንዳሉ ተናግሯል፡፡

የአዲስ ማለዳ ሪፖርተሮች ሐሙስ ዕለት ቅኝት ባደረጉባቸው አካባቢዎች በርካታ ወጣቶች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ላይ ሲውሉ የተመለከቱ ሲሆን፣ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ተወስደዋል፡፡

የታሰሩባቸው ቤተሰቦችን አድራሻ ማወቅ ያልቻሉ የታሳሪ ቤተሰቦችም በየፖሊስ ጣቢያው ሲጠይቁ የአዲስ ማለዳ ሪፖርተሮች የተመለከቱ ሲሆን፣ በጸጥታ ኃይሎች ድብደባ ያጋጠማቸው ወጣቶችን ተመልክተዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሎች በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመበተን በወሰዱት እርምጃዎችና በነበሩት መገፋፋቶች በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውም ተነግሯል፡፡