March 5, 2023 – BBC Amharic 

አክሊሉ ሃብተሚካኤል ስልጠና እየሰጠ

5 መጋቢት 2023, 08:03 EAT

ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ በተለያየ ምክንያት የተሰደዱ ወጣቶች ለመኖሪያነት ከሚመርጧቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኡጋንዳ ነች።

እነዚህ ወጣቶች ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር የመሄድ ዕል እስኪያገኙ ድረስ ከዘመድ ወዳጆቻቸው የሚላክላቸውን ገንዘብ እየጠበቁ ያለሥራ ይኖራሉ።

ከመጡበት አገር በሰለጠኑበት ሙያ ሥራ የማግኘት ዕድል እምብዛም ነው።

በሌላ ሙያ ላይ ለመሰማራት ደግሞ የክህሎት እና የቋንቋ ክፍተት እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

ይህንን የተመለከተው ኤርትራዊው አክሊሉ ሃብተሚካኤል በኡጋንዳ ካምፓላ ‘ትሬን አፕ ኢንስቲትዩት’ የተሰኘ ተቋም መሥርቷል።

በ1982 ኤርትራ ተወልዶ ያደገው አክሊሉ፣ በአሥመራ የሥነ-ህንፃ ትምህርት ቤት ቅየሳ ተምሯል።

ከኡጋንዳ በፊት ደቡብ ሱዳን በስደት የኖረው አክሊሉ፣ በስደት የሚኖሩ ወጣቶችን ችግር ከተመለከተ በኋላ ድርጅቱን ለመመስረት መብቃቱን ይናገራል።

እ.ኤ.አ. በ2011 መጨረሻ ኤርትራን ለቆ በኡጋንዳ በስደት መኖር የጀመረው አክሊሉ፣ በኤርትራ የምህንድስና ክፍል ውስጥ ለሰባት ዓመት፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ውስጥ በአንድ የግንባታ ኩባንያ ውስጥ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሲሰራ ያገኘውን ልምድ በመሰረተው የሥልጠና ተቋም ውስጥ እየተጠቀመበት ነው።

አክሊሉ በስደት እየኖረ ከየናይትድ ኪንግደም ሳልፎርድ ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል።

በኡጋንዳ ኔክሰስ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የንግድ ባለቤቶችን እና አስተዳዳሪዎችን በማስተማር እውቀቱን እና ልምዱን ማስፋት ችሏል።

በስልጠና ተቋም ውስጥ ትምህርቷን የምትከታተል ወጣት

ስደተኞችን ለማሠልጠን ምክንያቱ?

አክሊሉ እንደሚለው በደቡብ ሱዳን ዳጎስ ያለ ክፍያ የሚያገኝበትን ሥራውን “ለሌሎች የሚጠቅም እና ሕይወታቸውን የሚለውጥ ተግባር ማከናወን አለብኝ” በሚል ነበር የለቀቀው።

ስለዚህም በየጊዜው ያካበተውን ተግባራዊ እውቀት በተለይም ሌሎችን ለማሠልጠን እና ወጣት ስደተኞችን ለሚጠቅም ዓላማ ሊያውለው ተነሳ። መጀመሪያም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተወሰኑ ሰዎችን ማሠልጠን እንደ ጀመረ ይናገራል።

ከእሱ መማር የሚፈልጉ ሰዎች እየተበራከቱ ሲሄዱ ‘ትሬይን አፕ ኮንሰልትስ’ የተሰኘ የተወሰኑ ሰዎችን የሚያስተምር ማሠልጠኛ ማዕከል ከፈተ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ሳይዘልቅ ቀረ።

በኋላ ላይ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ተቋሙ ‘ትሬይን አፕ ኢንስቲትዩት’ በሚል ስም በኡጋንዳዋ ዋና ከተማ ካምፓላ፣ ካባላጋላ በሚባለው አካባቢ እንደ አዲስ መንቀሳቀስ ጀመረ።

በጥቂት ተማሪዎች የተጀመረው ሥልጠና አሁን በአንድ ዓመት ውስጥ 180 ተማሪዎችን በተለያዩ ሙያዎች በአካል እና በርቀት ማሠልጠን መጀመሩን አክሊሉ ሃብተሚካኤል ይገልጻል።

በከአራት ባልበለጡ ሠራተኞች የተጀመረው ይህ ድርጅትም ከተለያዩ አገራት 17 ሠራተኞችን ቀጥሮ በስደተኛ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

አክሊሉ መጀመሪያ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ደንበኞች ኤርትራውያን ስደተኞች እንደነበሩ ያስረዳል።

በአሁን ወቅት ግን ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊያውያን፣ ኮንጓውያን፣ ሩዋንዳውያን፣ አንዳንድ ኡጋንዳውያን እና ሕንዶች ጭምር በተቋሙ እየሰለጠኑ ይገኛሉ።

አክሊሉ እውቀትን ለሌሎች የማስተላለፍ ልምድ ከቤተሰቡ መውረሱን እንዲሁም ደግሞ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ እንዳለው በማንሳት ሲያስረዳ “አባቴ ቄስም መምህርም ነው፤ እና እያየሁ ያደግኩት ሙያ አስተማሪነት ነው” ይላል።

አክሎም “በደቡብ ሱዳን የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ስሰራ ያየሁት ነገር ያሳስበኝ ነበር” በማለት ወደዚህ ሥልጠና እንዲገባ የበለጠ ገፊ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል።

በደቡብ ሱዳን ምን ገጠመው?

በኢንጂነሪንግ፣ በአካውንቲንግ እና በሌሎችም ዘርፎች የተመርቁ ሰዎች ለሥራ ቅጥር ሲፈተኑ ብዙዎቹ “…የምስክር ወረቀት አላቸው፤ ነገር ግን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲቸገሩ አስተውያለሁ” ይላል።

ከተቀጠሩ በኋላ ቢሆን እውቀታቸውን ተግባር ላይ ለማዋል እስኪችሉ ድረስ ዓመታት እንደሚወስድባቸው ከተመለከተ በኋላ “በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያገኙ ሰዎች ሥራ ላይ ለምን የሚጠበቅባቸውን ያህል አያበረክቱም?” የሚል ጥያቄ ተፈጠረበት።

ችግሩ ትምህርቱ ከተግባር ጋር አለመገናኘቱ ነው ይላል።

በመሆኑም እነዚህን በትምህርት ጎበዝ የሆኑ ወጣቶችን በማሠልጠን በሥራ ላይ ውጤት እንዲያመጡ፣ ለራሳቸውም ሆነ ለሚሰሩበት ድርጅት – ባለቤትም ይሁኑ ተቀጣሪ – ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ አስቦ ነው የተነሳው።

አክሊሉ “ስለዚህ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያለው ሥልጠና በመስጠት ሰዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው” በማለት የድርጅቱን አላማ ያስረዳል።

አክሊሉ ይህንኑ ለማሳካት ሥራውን ሲጀምር በጥቂት ሠልጣኞች እና አሠልጣኞች መሆኑን ያስታውሳል።

ይህም ለሠልጣኞች መምህሩ በቀላሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እና አስፈላጊውን እውቀት እንዲያስተላልፍ በማሰብ ነበር።

አስተማሪዎቹም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመጡ እና በጽንሰ ሃሳብ የመጠቁ ብቻ ከሚሆኑ ከኢንዱስትሪዎች ጥልቅ የተግባር ልምድ ይዘው የሚመጡ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉንም አስረድቷል።

አክሎም በትሬይን አፕ ውስጥ የሚመለመሉት አሠልጣኝ መምህራን በሙያቸው የሰሩ ወይም የራሳቸው ንግድ ያላቸው እንደሚመረጡ ይገልጻል።

ተማሪዎቹ የሚወስዱት ሥልጠና በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ በሚል “የማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም ለእያንዳንዱ ትምህርት ዓይነት በትግርኛ የተዘጋጁ መማርያ ቪዲዮዎች እንዲቀርብላቸው ይደረጋል” በማለት በሌሎች ቋንቋዎችም ተመሳሳይ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ይናገራል።

በተቋሙ ውስጥ ትምህርት ሲሰጥ

ፈታኝ ሁኔታዎች ምን ነበሩ?

የአገሪቱን ማኅበረሰብ እና ሕጎች መረዳት እና መደበኛ ሕይወት መምራት የመሳሰሉ ከስደት ጋር ተያይዘው የሚመጡት ተግዳሮቶች እና መሰናክሎች የተጠበቁ እንደሆኑ ይናገራል።

ብዙ ሰዎች ትምህርት ላይ አለመሰማራታቸው ወይ ኢንቨስት አለማድረጋቸውም ሥልጠና ተቋም ለመክፈት የሚያበረታታ አይደለም።

“ይሁን እንጂ ህልሜ ሰዎችን በትምህርት ላይ በተግባራዊ ክህሎቶች በማሠልጠን ሕይወታቸውን ሲቀይሩ ማየት ስለነበር አንድ ብዬ መነሳት ነበረብኝ።”

አብዛኞቹ የተቋሙ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰው በተለያየ መንገድ ኡጋንዳ የገቡ ስደተኞች ናቸው። “ስደት ላይ የሁለተኛ ደረጃ እውቀት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ከሕይወት ልምዳቸው የተገነዘቡ ናቸው” ይላል።

በተጨማሪ ሌላ ሰው ላይ ጥገኛ በመሆን ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ብቻ መኖር ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ ስለገባቸው በፍላጎት እንደሚማሩም ያስረዳል።

በኡጋንዳ አንድ እውቀት እና ክህሎት ያለው ሰው በአግባቡ ከተማረ ቢያንስ ራሱን ከዚያም አልፎ ቤተሰቡን ለመደገፍ የሚያስችለውን ሥራ ማግኘት እንደሚችል የትሬይን አፕ ዳይሬክተር አክሊሉ ሃብተሚካኤል በልበ ሙሉነት ይናገራል።

በተለይ በካምፓላ የሚኖሩ አብዛኞቹ ስደተኞች የሚላክላቸወን ገንዘብ እየጠበቁ የመሥሪያ እና የመለወጫ እድሜያቸውን ከሚያባክኑ “…የትምህርት ዕድል ካቀረብንላቸው እና ከትምህርት በኋላ የሥራ ዕድል ካመቻቸንላቸው ሐዋላ ከመጠበቅ ተገላግለው ራሳቸውን ይችላሉ” ብሎ ያምናል።

“እኛጋ የሰለጠኑ አብዛኞቹ ወጣት ስደተኞች ሥራ ጀምረው፣ ራሳቸውን ችለው ኤርትራ ውስጥ ይሁን ሌላ ቦታ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ጀምረዋል” ይላል።

ትሬይን አፕ ኢንስቲትዩት ከአጫጭር ሥልጠናዎች ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት የሚወስዱ ትምህርቶች እና በዲፕሎማ ደረጃ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በተማሩት እና በሥራው ዓለም ባለው እውነታ መካከል ክፍተት መኖሩን የሚናገረው አክሊሉ “ይህን ክፍተት ለማጥበብ የምንችልበት መንገድ ተማሪዎችን ከተመረቁ በኋላ በልምምድ/በኢንዱስትሪ ሥልጠና መልክ ወደ አጋር ተቋማት መላክ ነው” በማለት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተግባራዊ ልምምድ ግንኙነት እንዳለቸው ያብራራል።

ትሬይን አፕ ኢንስቲትዩት በኡጋንዳ ሕግ እና መመሪያ መሠረት ከትምህርት እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከብሪትሽ ካውንስል እውቅና ያገኘ ተቋም ነው።

የኢንስቲትዩቱ መሥራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አክሊሉ ሀብተሚካኤል ተቋሙን ወደፊት በዩኒቨርስቲ ደረጃ ለማሳደግ አላማ አለው።