
ከ 6 ሰአት በፊት
በተለያዩ ለአዋቂዎች በሚሰናዱ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ሕጻናት እንግዳ ሆነው ይቀርባሉ።
ስለዚህ ውጥንቅጥ ስለበዛበት ዓለም፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ሕይወት ምስቅልቅል ይጠየቃሉ።
በሚሰጡት ምላሻም የሞቀ ጭብጨባ ይቀበላቸዋል፤ የማያቋርጥ የሳቅ ምንጭ ይሆናሉ።
ይህንኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሚሊዮኖች እየተቀባበሉ ይመለከቱታል።
ታዳጊ ሕጻናቱ በጨቅላ እድሜያቸው ዝናን ይከናነባሉ።
ፕሮግራሞቹ የተመልካችን ቀልብ እና ልብን መሳብ ዋነኛ ግባቸው ነው።
በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች ማግኘት ይፈልጋሉ።
ከዚያ ደግሞ ዝናና ገንዘብን ማትረፍ የዓላማቸው አንዱ አካል ነው።
እነዚህ አንደበታቸው የሚጣፍጥ፣ ሲያይዋቸው የሚያሳሱ ልጆች የበርካቶችን ቀልብም ልብም የመግዛት አቅማቸው ተፈጥሯዊ ነው።
የመዝናኛ ፕሮግራሙን ከሕጻናት ጋር አስተሳስረው የሚቀርፁ አካላት አብረው ታሳቢ ያደረጉት ይህንን የልጆች ተወዳጅነትን ነው።
እውነትም በርካታ ተመልካች በማግኘት ፍላጎታቸውን ያሳኩ ይመስላል።
የልጆች ዕድገት እና የሕጻናት ሥነ ልቦና ባለሙያዎች ግን የፕሮግራም አዘጋጆቹ እንዲሁም ወላጆች የዘነጉት ነገር መኖሩን ይናገራሉ።
እኛም የተዘነጋው ቁም ነገር ምንድን ነው? ስንል ጠይቀናቸዋል።
- ኢትዮጵያውያን ወላጆች ልጆቻቸውን በለጋ ዕድሜያቸው ለምን ‘ኮዲንግ’ ማስተማር ፈለጉ?5 የካቲት 2022
- ልጆች ሞባይል ሲጠይቁን እንስጣቸው ወይስ እንከልክላቸው?29 መስከረም 2020
- https://www.bbc.com/amharic/news-56339917
ልጆች የማያተርፉባቸው፣ የልጆች ፕሮግራሞች
የመዝናኛ ፕሮግራሞች መብዛታቸው የተለያየ ተመልካች ለማካተት፣ ፈጠራ የታከለበት ሥራ ለመሥራት በሚደረገው ጥረት ልጆችን እንግዳ የሚያደርጉ ፕሮግራሞች በርካታ ተመልካችን መሳብ መቻላቸውን የልጆች ዕድገት ባለሙያዋ ጆርጎ ድሪባ ታዝባለች።
የሥነ ልቦና ባለሙያ እና የሞሽን ማማከር እና ሥልጠና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ራቦም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።
“ሕጻናት በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀርቡ ራሱ የትኩረት ማዕከል ናቸው። ሕጻናትን አለማየት፣ አለማድነቅ፣ አለመሳም የሚችል ሰው ማግኘት ይከብዳል” ይላሉ የሕጻናትን ተወዳጅነት ሲያብራሩ።
አንደበታቸው ይጣፍጣል፣ ያለፍርሃት እና ይሉኝታ የመጣላቸውን ይናገራሉ፣ ሳቃቸው ወደ ተመልካች በቀላሉ ይጋባል ሲሉ ልጆች ለመዝናኛ ፕሮግራሞች እንግዳነት የተመረጡበትን ምክንያት ይጠቅሳሉ።
ጆርጎ በበኩሏ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ሕጻናትን በእንግድነት የሚያቀርቡ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ትኩረታቸውን ያደረጉት እሜያቸው ከአራት እስከ አስር ያሉት ላይ መሆኑን ማስተዋሏን ትጠቅሳለች።
ይሁን እንጂ ሕጻናትን እንግዳ የሚያደርጉ ፕሮግራሞች በዋናነት የዘለሉት ጉዳይ እንግዳ ያደረጓቸው ሕጻናትን መሆኑን ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
የልጆች ደኅንነት፣ ሥነ ልቡና እንዲሁም ስሜት በቸልታ ታልፎ ተመልካችን፣ ገንዘብን እና ዝናን ግብ ስላደረገ እነዚህ ፕሮግራሞች መስመር ስተዋል ማለት እንደሚቻል ይናገራሉ።
ሕጻናቱን አገልግሎ ገንዘብ፣ ዝናን ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፤ ነገር ግን አዋቂዎችን ማዝናናትን ማዕከል በማድረግ የልጆች መብት መጣሱን ያስረዳሉ።
ለሕጻናት እድገት ባለሙያዋ ጆርጎ ድሪባ፣ የልጆችን ተወዳጅነት ብቻ ታሳቢ አድርጎ የአዋቂዎች መዝናኛ ፕሮግራም ማዘጋጀት “በልጆች መነገድ ነው።”
እንዲህ አይነት ፕሮግራሞች ዓላማ ያደረጉት አዋቂዎችን ነው የምትለው ጆርጎ፣ ፕሮግራሙ ልጅን መንከባከብ፣ መጥቀም ዓላማው ስላላደረገ ልጅ በመካከል ሊጎዳ ይችላል።
“አዘጋጆቹ ከዚህ ውስጥ ልጆች ምን ሊጠቀሙ ይችላሉ፣ ምን ያተርፋሉ የሚለውን ሳያስቀድሙ፤ ተመልካቼ ምን ያተርፋል፣ እኔ ምን አተርፋለሁ ብለው ሲነሱ ልጆች ተጎጂ ይሆናሉ።”
የሚቀርቡ ልጆችን ጥቅም የሚያስቀድሙ ፕሮግራሞች “ልጆቹ ከዚህ ውስጥ ምን ያተርፋል፣ ሌሎች ልጆች ከዚህ ውስጥ ምን ያተርፋሉ፣ . . . መጀመሪያ ልጆችን አገልግሎ እድገታቸውን፣ መዝናናታቸውን፣ መጫወታቸውን፣ መማራቸውን ማስቀደም አለባቸው” ስትልም ታክላለች።
ታዋቂነት፣ አዋቂዎችን ማዝናናት፣ ገንዘብ ማግኘት ከዚህ ቀጥሎ መምጣት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም ታነሳለች።
“ሕጻናት የአእምሮ፣ የአካል፣ የመንፈስ ነጻነት ያስፈልጓቸዋል” የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ብርሃኑ፣ በሚዲያዎች ላይ እንግዳ ሆነው ከቀረቡ በኋላ ግን ይህንን ነጻነታቸውን እንደሚገፈፉ ያነሳሉ።
“ልጆች ከቀረቡ በኋላ ሊደነግጡ ይችላሉ። እንቅልፍ ሊያጡ ይችላሉ። በተለይ ብዙ ተመልካች እና ተከታይ ያላቸው ሚዲያዎች ላይ ከሄዱ በኋላ፣ ታክሲ፣ ባስ፣ መንገድ ላይ ሰዎች ነጻነታቸውን ሊነፍጓቸው ይችላሉ።”
ይህንን ደግሞ ሕጻናቱ መቋቋም አይችሉም። በዚህም የተነሳ ለጭንቀት እና ድብርት ሊጋለጡ ሊጋለጡ ይችላሉ።
የሕጻናት እድገት ባለሙያዋ ጆርጎ በእርግጥ እነዚህ የመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ ልጆች በትምህርት ቤትም ሆነ በቤታቸው ሰው በተሰበሰበበት ንግግር የማድረግ ችሎታን እንዲያዳብሩ፣ እንዲደፍሩ እና እንዲበረታቱ፣ እንደሚያደርጉም ገልጻለች።
አቶ ብርሃኑ ደግሞ የእነዚህ ልጆች የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ላይ ያለጥንቃቄ መገኘት አደጋም ጭምር እንዳለው ያስረዳሉ።
ልጆች በተፈጥሯቸው የትኩረት ማዕከል መሆናቸውን በማንሳት ሚዲያ ሲጨመርበት ደግሞ “ሕጻናቱ ግራ እንዲጋቡ፣ ፍርሃት እንዲያድርባቸው፣ እንዲሸማቀቁ ይሆናሉ።”
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒሽን መምህሩ አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች በተለያየ ምክንያት ተነሳስተው ልጆቻቸው በመገናኛ ብዙኃን ላይ እንዲቀርቡ ሊፈቅዱ ይችላሉ ይላሉ።
“የልጆቻቸው ተሰጥኦ ለሌሎች እንዲታይ፣ ከዚያም ባሻገር የገንዘብ እና የትምህርት ድጋፍ በመፈለግ፣ ለሌሎች ሕጻናት አዎንታዊ መልዕክት ለማስተላለፍ በመሻት፣ እንዲሁም ሰዎችን ለማዝናናት በመፈለግ ልጆቻቸውን ወደ ሚዲያ ይዘው ሊያቀርቡ ይችላሉ።”
ነገር ግን ይላሉ አብዱላዚዝ (ዶ/ር) ልጆቹ በመገናኛ ብዙኃን ላይ መቅረባቸው አዎንታዊ ጎን እንዳለው ሁሉ የሚኖረው አሉታዊ ውጤትም በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል ይላሉ።
የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ብርሃኑ ወደ ሚዲያ የሚመጡ ሕጻናት “በትክክል የልጅነት ጊዜያቸውን ልጅ ሆነው እንዳያሳልፉ፣ ትክክለኛ እድሜያቸውን እንደ ልጅ ተጫውተው፣ እንደ ልጅ ቦርቀው እንዳያድጉ. . .” እያደረጓቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አካታች ያልሆኑት ፕሮግራሞች
እነዚህ ፕሮግራሞች በእንግዳ አመራረጣቸው እጅግ በጣም ውስን መሆናቸውን የሕጻናት እድገት ባለሙያዋ ታስረዳለች።
በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ የሚቀርቡ ሕጻናት የተለያየ ስጦታዎች ያሏቸው ቢሆንም “በተለይ ግን የመናገር፣ ሳቅ የመፍጠር፣ የማጫወት፣ የማዝናናት ችሎታ” ዋነኛ ተተኳሪ ጉዳዮች መሆናቸውን ታዝባለች።
ጆርጎ እነዚህ ዝግጅቶች “በመልክ የሚያምሩ፣ ቀላ ያሉ፣ በከተማ የሚኖሩ ድንቡሽቡሽ ያሉ ልጆችን እንግዳ የሚያደርጉ” መሆናቸውንም በምልከታዋ ወቅት ታዝባለች።
አክላም “የኢትዮጵያ ልጆች በከተማ ያሉ ብቻ ወይንም መልካቸው፣ የኑሮ ደረጃቸው፣ ደጋግመን የምናያቸው ዓይነት ብቻ አይደሉም” ትላለች።
ጆርጋ እያንዳንዱ ልጅ በፕሮግራሙ ውስጥ ራሱን አለማየቱ የመገለል ስሜት ይፈጥርበታል ስትል ያለውን ተጽዕኖም ትናገራለች።
በፕሮግራሞቹ ላይ የሚቀርቡት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልጆች ከሆኑ “ከሁሉም የሚወክሉ ቢሆኑ ለልጆች ተመራጭ ይሆናል” ስትልም ሙያዊ አስተያየቷን ትሰነዝራለች።
አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃኑም ሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያው ሙሉ በሙሉ ልጆችን ወደ መድረክ በማምጣት፣ በማወዳደር፣ “ልጆችን መጠቀሚያ የማድረግ ነገር” ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
ልጆች በአመክንዮ ስለማያስቡ፣ ስሜታዊ የአእምሯቸው ክፍል ብቻ ያደገ በመሆኑ ያለ አንዳች ፍርሃት አእምሯቸው ላይ የመጣውን በሙሉ የሚናገሩ ግልጾች መሆናቸውን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ጥያቄው መሆን ያለበት ግን ይላሉ አቶ ብርሃኑ እነዚህ ልጆች በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው የተሰማቸውን ሁሉ ያለምንም መሳቀቅ ሲናገሩ “ነገ ምን ይሆናል?” የሚለው ያሳስባቸዋል።
ሕጻናቱ ከሚያውቁት እና በዙሪያቸው ካሉ ጉዳዮች ባሻገር በጥልቀት ስለማያውቋቸው ነገሮች ይጠየቃሉ፣ ምን ሊያስከትል ስለማይረዱም ስለቤተሰባቸው እና ስለሌሎች ሰዎች የሚናገሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ የሆኑት አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) ደግሞ ሕጻናቶችን የግለሰቦችን ስም ያለፈቃዳቸው እያነሱ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ማድረግም ተገቢ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ሕጻናት በምላሻቸው ወቅት የግለሰቦችን የፋይናንስ መረጃ፣ የጤና መረጃዎች እንዲሁም የግል ምስጢር እያነሱ ሊናገሩ ስለሚችሉ መጠንቀቅ እንደሚገባ ያሰምሩበታል።
የሥነ ልቦና ባለሙያው “ይህ የነገ ማንነታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ካሉ በኋላ “ነገ ሳይመጣም የልጆቹን ዛሬ ብንመለከት እንኳ ማኅበረሰቡ ልጆቹን በቴሌቪዥን መስኮት እና በማኅበራዊ ገጾች ላይ በማወቁ ብቻ የሚያደርስባቸውን ጫና መቋቋም ያቅታቸዋል።”
ይህም “የራሳቸውን መንገድ እንዳይከተሉ፣ በአግባቡ በትክክለኛው ጊዜ አድገው ትክክለኛውን ነገር እንዳያደርጉ፣ የሌሎች መጠቀሚያ እንዲሆኑ ሊያደርጋcው ይችላል” በማለት ያሳስባሉ።
ዶ/ር አብዱላዚዝ በዚህ ላይ ሲያክሉ ጋዜጠኞቹ እና ሚዲያዎቹ ፕሮግራማቸውን በሚያቅዱበት፣ በሚቀርፁበት እና አርትኦት በሚሰሩበት ወቅት ሕጻናቱ ስለአካባቢያቸው፣ ስለ ራሳቸው እና ስለቤተሰቦቻቸው ያሏቸው ነገሮችን በሚገባ መመልከት አለባቸው ይላሉ።
በዚህም ፕሮግራማቸው “ወደፊት ልጆቹ ላይ ሊመጡ የሚችሉ የደኅንነት ስጋቶችን” ከመቀነስ እና ልጆቹን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ ካለመክተት አንጻር በኃላፊነት የሚሰራ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።
ለልጆች የሚቀርቡ የአዋቂ ጥያቄዎች
በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ለልጅ የማይነሳ ጥያቄ ሲነሳ፣ ሲያፋጥጧቸው፣ ሲያስደነግጧቸው መመልከታቸውን የሚናገሩት የሥነ ልቦና ባለሙያው፣ ይህ የሆነው ፕሮግራሙን የሚያዘጋጁ አካላት “የሕጻናትን ሥነ ልቦና የተረዱ ወይንም ያነበቡ ባለመሆናቸው” ነው ይላሉ።
“እንደ ባለሙያ ቤት ተቀምጠን ስንመለከት ለልጆቹ በሚቀርበው ጥያቄ እንሸማቀቃለን” የሚሉት አቶ ብርሃኑ ለልጅ መቅረብ ያለበት የልጅ ጥያቄ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ ሃይማኖታዊ ጉዳይ ለልጆቹ ማንሳት “ልጆቹን መጉዳት ነው” ሲሉም ያክላሉ።
በተጨማሪም ዓለምን የሚያስጨንቁ ጉዳዮችን ለልጆች አንስቶ ማዋከብ፣ “ልጆቹ ተስፋ እንዲቆርጡ እና… ወደፊት እንዳይራመዱ ወይንም ደግሞ በአሁኑ ማንነታቸው የበቃቸው እንዲመስላቸው እና የአሁኑ ማንነታቸው ያለቀ እንዲመስላቸው ትልቅን እንደ ትልቅ እንዳያዩ ያደርጋል።”
“በእርግጥ ከጥያቄያችን መካከል ትንሽ የሚያመራምራቸው ነገሮች ልናደርግ ይገባል” የምተለው ጆርጎ ደግሞ ለልጆች የምንሰጠው ሁሉ እድሜያቸውን፣ እድገታቸውን፣ የማሰብ፣ የማገናዘብ አቅማቸውን የማከለ መሆን እንዳለበት ታነሳለች።
አቶ ብርሃኑ ታዳጊዎቹ እና ሕጻናቱ ‘የአዋቂ ጥያቄዎች’ መጠየቃቸው እና በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸው፣ ከአደጉ በኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱት “ወላጅ አልነበረኝም ወይ? እንዴት ለእንደዚህ ዓይነት ነገር አጋልጠው ሰጡኝ?” ብለውና “ነገ በራሳቸው እንዲያፍሩ” ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሕጻናቱ እድሜ እና የእድገት ደረጃ ተገቢው ምላሽ የማይሰጥባቸውን ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ሥርዓተ ጾታ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመሳሰሉትን መጠየቅ እና እንዲመልሱ ጫና በማድረግ አላስፈላጊ ለሆነ የተደራሲ ትዝብት ልጆቹን ማጋለጥ ነው።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ልጆች ላይ በአጭር እና በረዥም ጊዜ ጉዳቶችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
የሕጻናት እድገት ባለሙያዋም ሆነች አቶ ብርሃኑ እንደሚስማሙት በአጭር ጊዜ “ልጆች ግራ በመጋባት፣ በጭንቀት፣ በፍርሃት፣ በእፍረት እና በሌሎች ባልተገቡ ጫናዎች ውስጥ እንዲያልፉ” ይሆናሉ።
ለሌላው መዝናናት ሲባል በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ መደረጉ “ሰብአዊነት አይደለም” የምትለው ጆርጎ፣ “በእነዚህ ጫናዎች ውስጥ ልጆችን እንዲያልፉ ማድረግ መጉዳት ነው. . . ትክክል አይደለም ሊባልም የሚገባው ጉዳይ ነው።”
በረጅም ጊዜ ደግሞ ልጆቹ ካደጉ በኋላ ሚዲያ ላይ መቅረብ የማይፈልጉ፣ የግላቸውን ሕይወት በፀጥታ መኖር የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉት አቶ ብርሃኑ “ያንን ዕድላቸውን ጭምር ነው የተቀሙት” ይላሉ።

ሌሎች ሕጻናት ‘የማይወዷቸው’ ልጆች
እነዚህን ልጆች “እኩዮቻቸውም አይወዷቸውም” የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ሕጻናት ዝናቸው በፍጥነት እንደሚናኝ በማንሳት ነው።
“በየሄዱበት ቦታ ሰው ሆይ ሆይ ይላቸዋል። በእያንዳንዱ ሰው ቤት ስማቸው ይጠራል። ይህ ሲሆን የእነርሱ አቻ የሆኑ እና ቤት ውስጥ ያሉ ልጆች ምን ይባላሉ? ‘የእከሌን ልጅ አላየህም? አላየሽም? እርሱ በዚህ እድሜው ሚዲያ ላይ እንዲህ ሲናገር እናንተ ገና እዚህ ናችሁ’ ተብለው ስለሚወቀሱ ልጆቹን ይጠሏቸዋል።”
በዚህ የተነሳም በሚዲያ ላይ የሚቀርቡት ብቻ ሳይሆኑ ቤት ተቀምጠው የሚያዩ ሕጻናትም ላይ ድብርት እና ጭንቀት ይፈጥራል።
ጆርጎ ልጅ ሁሉ ሲያወራ ፈጣን አለመሆኑን፣ ያ ደግሞ የልጅ ክህሎት ብቸኛ መለኪያው አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥታ ታስረዳለች።
ቶሎ ቶሎ መናገርን ለልጆች ልናበረታታ አይገባም የምትለው የሕጻናት እድገት ባለሙያዋ “ልጆች አስበው፣ ተረጋግተው ነው እንዲናገሩ የሚመከረው” ትላለች።
ሁሉም ልጆች ራሳቸውን ከንግግር በተጨማሪ በጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል ጭምር እንደሚገልጹም ታስረዳለች።
ስለዚህ ራሳቸውን በተለያዩ ነገር የሚገልጹ ሕጻናት ምርጫቸው መከበር እና መበረታታት እንዳለበት የሚያነሱት ባለሙያዎቹ፤ እነዚህ ፕሮግራሞች የሚያቀርቧቸው ታዳጊዎች ከሚያሳዩት በመነሳት በወላጆች፣ በአሳዳጊዎች እንዲሁም በእኩዮቻቸው ዘንድ ትክክለኛው ልምድ ቶሎ ቶሎ መናገር ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በረዥም ጊዜ ሊያዝ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ጋዜጠኛው አጠገቡ የተቀመጠው ሕጻን አንደኛ እንደሆነ፣ በዓለም ላይ እርሱን የሚመስል ሌላ ልጅ እንደሌለ፣ በጣም ብርቅ እንደሆነ አድርጎ ሲያቀርብ ቤት ተቀምጠው የሚያዩ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ልጆቹም በራሳቸው ሀፍረት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ጆርጎ በዚህም የተነሳ “ልጆች ራሳቸውን መሆን ትተው የሚያይዋቸውን ልጆች መሆን ይጀምራሉ” ትላለች።
አክላም “ልጆች ራሳቸውን ሲያወዳድሩ እኔ እንዲህ ዓይነት ልጅ አይደለሁም በማለት የበታችነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል፤ ወላጆችም ልጅ እንደዚህ መሆን አለበት የሚል ያልተገባ መስፈርት በማውጣት ልጆች ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ” ትላለች።
ከዚህ አንጻር አቶ ብርሃኑ ሕጻናቱን በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች “እኛ በአጋጣሚ እነዚህን ልጆች አቀረብን እንጂ በየቤቱ እንደ እነርሱ ጎበዝ የሆኑ እንደውም የበለጡ ልጆች ይገኛሉ” በማለት ተቀምጦ ለሚመለከተው ሕጻን እውቅና ሲሰጡ አለመመልከታቸውን ይተቻሉ።
ችላ የተባሉት የሕጻናት ጉዳዮች
የኢትዮጵያ ወላጆች ልጆቻቸው በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡላቸው “ምንም የሚሆኑባቸው አይመስላቸውም” ይላሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ራቦ።
ነገር ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ የትኛውም የመገናኛ ብዙኃን ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ከመውሰዳቸው በፊት ልጆቻቸውን በትክክል እና በግልጽ ፈቃዳቸውን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።
ሌሎች ልጆች ስለቀረቡ ብቻ ገፋፍቶ እና አባብሎ መውሰድ ሳይሆን “ልጆቹ እኔም እኮ እችላለሁ. . . ልሂድ” ማለት መቻል አለባቸው ይላሉ።
ያኔ ደግሞ “ሚዲያ ላይ የመቅረብ ጥቅም እና ጉዳቱን” የማስረዳት ኃላፊነታቸውን ቤተሰቦች መወጣት እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ ያሰምሩበታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ የሆኑት አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) ሕጻናትን እንግዳ የሚያደርጉ መገናኛ ብዙኃን የወላጆቻቸውን ወይንም አሳዳጊዎቻቸውን ፈቃድ በጽሑፍ ማግኘት እንዳለባቸው እንደሚመከር ይናገራሉ።
በዚህ ወቅትም የፕሮግራሙ ዓላማ ምንድን ነው? በየትኛው ፕሮግራም፣ ቀን እና ሰዓት ላይ ለምን ያህል ደቂቃ እንደሚተላለፍ በግልጽ ማስረዳትም ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።
ወላጆች ልጆቻቸው ወደ መገናኛ ብዙኃን እንዲቀርቡ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ፣ ጫና ተፈጥሮባቸው መሆን እንደሌለበት በመግለጽ፣ ሚዲያው ለልጆቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ሐዘኔታ ሊኖረው እና ያለውን አደጋ ሁሉ የማስረዳት ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ከዚህ ውጪ የጋዜጠኝነትን ሥነምግባር መከተል ምንጊዜም መዘንጋት እንደሌለበት ባለሙያው ይመክራሉ።
ወላጆች ለልጆቻቸው የዛሬውን እና የነገውን በትክክል ማሳየት አለባቸው የሚሉት የሥነ ልቡና ባለሙያው፣ ካልሆነ ግን የፕሮግራሙ አዘጋጅም ሆነ አቅራቢ ለልጆቹ በሚቀርቡ ጥያቄዎች እና ተከትለው በሚመጡ ጉዳዩች “ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው” ይላሉ።
ወላጆች ልጆቻቸው በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡ “ምን ጥቅም ለማግኘት” የሚለውን መመለስ እንደሚኖርባቸው አስታውሰው “ልጆቹ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም የሥነ ልቦና ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል” ሲሉም ይሞግታሉ።
ሕጻናት እና ታዳጊዎች ወደ መገናኛ ብዙኃን መድረክ መጥተው መቅረብ ካለባቸው፣ አዘጋጆቹ የሕጻናት ሥነ ልቦና ምን አንደሚመስል በመጠኑም ቢሆን እውቀት ቢኖራቸው ሲሉ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
ልጆች በሚያዩት እና በሚሰሙት ተጽዕኖ ውስጥ በእጅጉ አንደሚወድቁ የምትናገረው ጆርጎ፣ እነዚህን ዝግጅቶች የሚያዘጋጁ ባለሙያዎች በጣም በጥንቃቄ እና በታሰበበት መልኩ መልዕክቱ ልጅ ጋር ሲደርስ ምን ዓይነት ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል የሚለው ተመዝኖ መሰራት አለበት።
ፕሮግራሞቹ ሲሰሩ ቅኝታቸውን እና ዓላማቸው መስተካከል እንዳለበት የምታነሳው የሕጻናት እድገት ባለሙያዋ “ልጆችን በመውደድ፣ ለልጆች በመራራት ስሜት” መሰራት እንዳለበት ትናገራለች።
ስለዚህ ፕሮግራሞቹ ዓላማቸው ማዝናናት፣ ትውልድን ማነጽ፣ መልካም ሥነምግባርን ማስረጽ፣ የተለያየ ችሎታን ያላቸውን እንዲያወጡ ማበረታታት፣ ልጆች በመልካም ጎኑ እንዲታወቁ ማድረግ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።
ልጆችን ማዕከላዊ አድርገው ራሳቸው ልጆቹን ለማዝናናት፣ ለማጫወት፣ እድገታቸውን ለማገዝ፣ እድሜያቸውን እና የእድገት ደረጃቸውን የሚመጥን ዝግጅት በፍቅር እና በርህራሄ ማቅረብ እንደሚገባ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች በጋራ የሚስማሙበት ነው።
ከልጆቹ መረጃ ወይንም ዕውቀት ሲጠየቅ ደግሞ የልጆቹን ክብር እና ደኅንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበትም ያነሳሉ።
የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ቢሆኑ የልጆቹን እድሜ እና የእድገት ደረጃቸውን ከግንዛቤ ያስገቡ፣ የፕሮግራሞቹም ይዘቶች አዋቂ እንዴት ይረዳዋል ሳይሆን ልጆች ጋር ሲደርስ የሚሰጠው ትርጉም ምንድን ነው? የሚለው መሆን እንዳለበት አጽንኦት ይሰጣሉ።