
በፌደራል መንግስትና ሕወሓት መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላም፣ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር የነበሩት የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ኹለት ወረዳዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ያሉት ወረዳዎች ጻግብጂና አበርገሌ ሲሆኑ፣ በአካባቢዎቹ ከ67 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የኹለቱ ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በችግር ላይ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ተፈናቃዮቹ ለከፍተኛ ችግር መዳገራቸውን ተከትሎ ወደ ቀየያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየጣርኩ ነው ያለው የዋግ ሕምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አደጋ መከላልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መከላከያ ሰራዊት በአጭር ቀናት ውስጥ አካባቢዎቹን ነጻ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ምኅረት ታምሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ መከላከያ ሰራዊት ኹለቱን ወረዳዎች በአጭር ቀናት ውስጥ ከሕወሓት ነጻ በማውጣት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሚሰራ ለዞኑ አስታውቋል፡፡
በዚህም መከላከያ ሰራዊት ለዞኑ የጸጥታ ማረጋገጫ እስኪሰጥ ድረስ እየተጠበቀ ነው ያሉት ምኅረት፣ ሰራዊቱ በምን አይነት ሁኔታ ወረዳዎቹን እንደሚቆጣጠር አናውቅም ብለዋል፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግም ጽ/ቤታቸው ከ15 መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር ተፈናቃዮችን ወደየቀያቸው መመለስ ስለሚቻልበትና መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ሀሙስ የካቲት 23 በሰቆጣ እንደተወያዩ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ጽ/ቤቱ መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠውን የጸጥታ ማረጋገጫ ተከትሎ የሚያደርጋቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ለመጀመር ከየካቲት 28 ጀምሮ የሚጠቀምበት የክንውን እቅድ ያወጣ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና ዕለታዊ እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ 250 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡
በዚህም መሰረት መንግሥታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ማበርከት የሚችሉትን ካሳወቁ በኋላ ለአማራ ክልል አደጋ መከላልና የምግብ ዋስትና ቢሮ ሪፖርት ይደረጋል ያሉት ምኅረት፣ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ብለዋል፡፡
የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ከወረዳዎቹ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ የተነገረ ሲሆን፣ ተፈናቃዮች ወደየቀያቸው ከተመለሱ በኋላ የሚኖረውን መልሶ ማቋቋም በተመለከለት የእርዳታ ድርጅቶች እቅዳቸውን እንደሚያቀርቡ ተሰምቷል፡፡
ተፈናቃዮች በአብዛኛው በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ በመሆኑ መጪውን የእርሻ ጊዜ እንዲጠቀሙ ለማድረግ በቅርብ ቀናት ውስጥ መከላከያ ሰራዊት ሕወሓትን ከወረዳዎቹ የማስወጣት ሥራውን እንደሚያጠናቅቅ ያላቸውን ተስፋ የተናገሩት ምኅረት፣ 67 ሺሕ ለሚሆኑት ተፈናቃዮች አሁንም በቂ እርዳታ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ሕወሓት የኹለቱ ወረዳዎች አካል የሆኑ 21 ቀበሌዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ እና ማኅበረሰቡ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዳልነበር ሲገለጽ ነበር፡፡
ምንጭ አዲስ ማለዳ