March 6, 2023 

ሕገወጡ ራሱን የኦሮሚያ ሲኖዶስ ያለው ስብስብ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የሚያደርገውን ጥቃት፤ ዘረፋ እና ረብሻ ቀጥሏል፤ በዚህም መሰረት ከታች በዝርዝር ዘገባዎች ተቀምጠዋል

በሻሸመኔ ወጣት ኦርቶዶክሳውያን እየታሠሩ መሆኑ ተገለጸ!

ከሕገ ወጡ ቡድን ጋር እየሠሩ የሚገኙት የደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ተስፋ ጊዮርጊስ የተባሉት ግለሰብ ወጣቶችን እየጠቆሙ እያሳሰሩ መሆኑ ተገለጸ።

ለተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል በደረሰው መረጃ መሠረት የታሠሩት ወጣቶች በትናንትናው ዕለት ሕገ ወጡ ቡድን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በመውረር አገልግሎት አስጀምራለሁ ማለቱን ተከትሎ ይህንን ተቃውመው የተናገሩ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።

ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የታሠሩ ወጣቶች ቁጥር 8 መድረሱ ተጠቁሟል።

በሻሸመኔ ከተማ ከአርባ በላይ ኦርቶዶክሳውያን በጸጥታ አካላት እንዲገደሉ ያደረገው ሕገ ወጡ ቡድን በዚህ ሰዓት የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በመውረር ጸሎተ ምሕላ እያደረሰ ይገኛል።

እንደ መረጃ አድራሾቻችን ገለጻ ይህ ድርጊት በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ተጨማሪ እልቂት መፈጠሩ የማይቀር ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ተመድቤአለሁ የሚል ግለሰብ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና በሆነው ደብረ ስብሃት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ተመድቤአለሁ የሚል ግለሰብ መምጣቱ ተገለጿል፡፡

በሕገ ወጥነት ከተሾሙት “ኤጲስ ቆጶሳት” መካከል አባ ቻፒ ከተባለው ግለሰብ የተመደብኩ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነኝ የሚል ግለሰብ በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ባለስልጣኖችና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቤተ ክርስቲያኑ መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ በደብረ ሰብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ነባር አገልጋዮች አገልግሎት እንዲሰጡ የማይመጡ ከሆነ እኛ እንመድባለን ማለታቸውንና የደብሩ አለቃ አባ ተስፋ ጊዮርጊስም ተቀብለው መመሪያውን እያስፈጸሙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ነገር ግን ብፁዓን አባቶች የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋር በተወያዩት መሠረት ቀጣይ ሳምንት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በአበው ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት ታቅዶ እንደነበረ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በምእራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ስም ሹመትና ዝውውር እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በመንግሥት ድጋፍ በምእራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በአሉ አብያተ ክርስቲያናት ዝርፊያ መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል ለዚህም ምንም አይነት እርምጃ በአለመወሰዱ ምክንያት አሁን ላይ ካህናትን በማፈናቀል እና የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ መደቦቸን የሀገር ስብከቱን ማሕተም በመጠቀም ሹመትና ዝውውር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም የተነሳ የምእራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በማለት በሚጠራው የሕገ ወጡ ቡድን አባል በሆነ ቄስ ታዳሳ ደሪቤ በተጻፈ ደብዳቤ የደብረ ንጉሥ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊና ሒሳብ ሹም የነበሩትን ቄስ ሀሰቤ ታዳሳ በጡሎ እና ዶባ ቤተ ክህነት ወረዳዎች ተዛውረው በሥራ አስኪያጅነት እንዲሠሩ መሾሙን የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት ዘግቧል።

በምዕራብ ሐረርጌ ጭሮ ከተማ በሚገኘው በደብረ ሲና ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ዝርፊያ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ጭሮ ከተማ በሚገኘው በደብረ ሲና ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ኪዳን እናደርሳለን ባሉ ከሕገ ወጡ ተሿሚ ወገን በሆኑ 4 ግለሰቦች አማካኝነት ከቤተ ክርስቲያኑ ሽቶ፣ ዕጣንና መብዓ ይዘው ሲወጡ መያዛቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁኔታውን የተመለከተው የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ጥይት በመተኮስ ምእመናን ተሰብስበው ሁለቱ ግለሰቦች ሊያዙ ችለዋል፡፡ ዝርፊያ የፈጸሙት ግለሰቦችን ምእመኑ ለከተማው ፖሊስ ያስረከበ ቢሆንም የከተማው ፖሊስ ግን ግለሰቦቹ ይህንን አያደርጉም አውቃችሁ ነው በሚል ያለምንም ማጣራት ግለሰቦቹን መልቀቁ ተገልጿል፡፡

በአንጻሩ የቤተ ክርስቲያኑን ጠባቂ ለምን ወደ ሰማይ ተኮስክ በሚል ማሰራቸውን ለመረዳት ችለናል ሲል የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት ዘግቧል።

Source – ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል