March 6, 2023 

” ሌላ አዲስ ማሽን ካልመጣ በስተቀር አንድም ተጠግኖ ስራ ላይ የሚውል አንድ ብሎን እንኳን የለም ” – አቶ ካሳሁን ፎሎ

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አመራሮችን ያቀፈ የልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል፣ በጦርነት ምክንያት የወደሙ የኢንቨስትመንት ተቋማትን በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል።

ልዑኩ ከጎበኛቸው የወደሙ ተቋማት መካከል የ ” ሸባ ሌዘር ኢንዱስትሪ ” እና ” ሰማያታ እምነበረድ ፋብሪካ ” ይገኙበታል።

ከጉብኝቱ በኃላ በመቐለ ውድመት ከደረሰባቸው የኢንቨስትመንት እና ኢንድስትሪ ተቋማት ሰራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል።

በዚህ መድረክም በጦርነቱ የደረሰው ውድመት፣ በሰራተኞች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጓል።

የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በጉብኝታቸው የተመለከቱን እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል ፥

” ሙሉ በሙሉ 100% የወደሙ ሌላ አዲስ ማሽን ካልመጣ በስተቀር አንድም ተጠግኖ ስራ ላይ የሚውል አንድ ብሎን የለም ”

አቶ ካሳሁን ይህንን በመቐለ አካባቢ ባደረጉን ጉብኝት መመልከታቸውን አስረድተዋል።

” ሌሎቹ ስለራቁብን ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ ቦታዎች ላይ የማንደርስባቸው አሁንም ጥሩ ያልሆኑ አካባቢዎች አሉ በደንብ ያልተፈቱ ጉዳዮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ያላለቀለት እዛም ችግሮች አሉ ። ” ያሉት አቶ ካሳሁን ” ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው ከወልቃይት ስኳር ፋብሪካ፣ ህይወት እርሻ ሜካናይዜሽን ተፈናቅለው ያሉትን ዞረን ያሉበትን ቦታ አይተናል በምን ደረጃ ላይ እንዳሉም ተመልክተናል ፤ ይሄ የጦርነት ውጤት ነው ፤ በቃላት ከምንገልፀው በላይ በአይናችን አይተናል ” ሲሉ አስረድተዋል።

” ችግሩ በሰላም በውይይት እንዲፈታ ፣ ወንድም ወንድሙን አይግደል ፣ ኢትዮጵያውያን ነን እየተገዳደልን ያለነው ፣ ከጦርነት ማንም የሚያተርፍ የለም እያልን መግለጫ ስናወጣ ነው የቆየነው ” ሲሉም ፕሬዜዳንቱ አስታውሰዋል።

በትግራይ ክልል በተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እንዲሁም ሰራተኞች ያሉበት ሁኔታ የከፋ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ኢሰመኮ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ያሉትን ችግሮች መፍታት እንዲቻል ከመንግስት እና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ጥረት እንዲያደርግ ለሰራተኞችም ትኩረት እንዲሰጥ ከትግራይ ሰራተኞች ተጠይቋል።

አቶ ካሳሁን ፎሎ በትግራይ ያለው ችግር ከባድ መሆኑን አንስተው ችግሮችን መፍታት ለአንድ ወገን ብቻ የሚሰጥ ስራ ባለመሆኑ ከክልል ፣ ከፌዴራል ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ኢሰማኮ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርግ ማሳወቃቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

NB. ሼባ ሌዘር ፦ 100% ውድመት ደርሶበታል። ተጠግኖ እንኳን ስራ ላይ የሚውል ንብረት እንዳይቀር ተደርጎ ነው የወደመው። ሼባ ሌዘር 1200 ሰራተኞች ነበሩት ውድመት ከደረሰበት በኃላ ሰራተኛው ደመወዝ አጥቶ ፣ ተቸግሮ ተፈናቅሏል።