March 6, 2023 – ምንሊክ ሳልሳዊ 

ለመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ከአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ከፍተኛ ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው።

በኮሜዲያን እሸቱ መለስ መሪነት የሚደረገው የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረት ማዕከሉ ላስገነባው ሕንጻ ማጠናቀቂያ በር እና መስኮት ለመግጠም ያለመ ነው።

የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራው በአገር ውስጥ ባንኮች በኩል፣ በጎ ፈንድ ሚ፣ በካሽ አፕ እና ዜሌ በኩል እየተከናወነ ሲሆን፣ እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ገንዘብ አሰባሳቢዎቹ ከ54 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ በሰዓታት ውስጥ መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል።

እስከ ሰኞ የካቲት 27/2015 ዓ.ም. ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ በጎ ፈንድ ሚ በኩል ብቻ የተሰበሰበው ገንዘብ ከ700ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ሆኗል።

ለሜቅዶንያ ለሚሰራዉ አዲሱን ህንፃ በር እና መስኮት ካልገጠምን ከ ላይቭ አንወጣም 

https://gofund.me/216b39ce

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እያስገነባው ለሚገኘው ሕንጻ ከ1ሺህ 600 በላይ በር እና መስኮቶች ለመግጠም በጎ ፈንድ ሚ አማካይነት እስከ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የለገሱ ሰዎች አሉ።

ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ እየመራ ያለው ኮሜዲያን እሸቱ ለማኅበራዊ ጥሪ ምላሽ ይሆን ዘንድ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ሲሰራ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በቅርብ ጊዜም ለክርስትና እና እስልምና ቤተ እምነት ቦታዎች ግንባታ ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ አሰባስቧል። በቅርቡም በድርቅ ለተጎዳው የቦረና አርብቶ አድር 10 ሚሊዮን ብር እርዳታ ማሰባሰቡ ይታወሳል።

መቄዶኒያ ማን ነው?

መቄዶኒያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያን እና የአእምሮ ሕሙማን መጠለያ፣ ምግብ እና ሕክምና በመስጠት ይታወቃል።

የመቄዶኒያ መሥራች የሆነው ቢኒያም በለጠ ትናንት እሁድ የካቲት 26/2015 ዓ.ም. ማዕከሉ ከተመሠረተ 11 ዓመታት ማስቆጠሩን እና 7500 ሰዎችን ማስጠለሉን ተናግሯል።

በማዕከሉ ተጠልለው ለሚገኙ ሰዎች ምግብ፣ ልብስ እና ሕክምና ለመስጠት የማዕከሉ ዕለታዊ ወጪው 1 ሚሊዮን ብር መሆኑን አመልክቷል።

ቢኒያም፤ “ችግር እየበዛ፤ ተጎጂዎች እየጨመሩ” ሰለሆነ የመቄዶኒያን ተግባር የበለጠ መስፋት ያለበት ጊዜ አሁን ስለሆነ ለማዕከሉ መደረግ ያለበት ድጋፍ እንዲጨምር ለለጋሾች ጥሪ አቅርቧል።

ማዕከሉ አሁን ላይ በ2.45 ቢሊዮን ብር ወጪ እያስገነባ ያለው ሕንጻ ግንባታ 70 በመቶ መጠናቀቁን እና ተገንብቶ ሲጠናቀቅ እስከ 10ሺህ ሰዎች መያዝ እንደሚችል ተናግሯል።

https://youtube.com/watch?v=bQBl1nN6zXk%3Fversion%3D3%26rel%3D1%26fs%3D1%26autohide%3D2%26showsearch%3D0%26showinfo%3D1%26iv_load_policy%3D1%26wmode%3Dtransparent