
ዶ/ር መሠረት ዘላለም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ሕጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናት፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በሕጻናት ትምሕርት እና ሕክምና ክፍል ባለሙያ ሆና አገልግላለች፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ የቀድሞ የብአዴን አመራርና የገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡ በህወሃቶች ለረጅም ጊዜ ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የአማራ ባንክን በማቋቋም ትልቅ አስተዋጾ ያደረገ፣ አሁንም የቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ እየሰራ ያለ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡
ዶር መሰረት ዘላለም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ በአማራ ባንክ ውስጥ እያደረጉት ስላለው ነገር አይደለም አሁን ለማንሳት የምፈልገው፡፡ ዶር መሰረት፣ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴሯ ዶር ሊያ ታደሰ፣ አልፎም ለጠቅላይ ሚኒስተሩ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞለአማራ ባንክ ባለ አክሲዮኖች ነው ተጠሪነታቸው፡፡ ስለዚህ ስራቸውን ስላልገመገምኩ የመገምገምም መብት ስለሌለኝ፣ በዚህ ረገድ የምለው ነገር አይኖረኝም፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁለት ወገኖች በሌላ በጣም ትልቅና አንገብጋቢ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ግን ልሞግታቸው እፈልጋለሁ፡፡
ከሁለት አመት ተኩል በፊት የጎንደር ከተማን ህዝብ ፣ “እናገለግልሃለን፣ ያነተ ድምጽ እንሆናለን” ብለው ለምርጫ ቀርበው፣ ህዝቡም ድምጽ ሰጧቸው ነበር፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ 24035 ድምጽ በማግኘት የጎንደር ምርጫ ወረዳ አንድን፣ ዶር መሰረት ዘላለም 19228 ድምጽ በማግኘት የጎንደር ከተማ ምርጫ ወረዳ ሁለትን አሸንፈው፣ ጎንደር ከተማን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል፡፡
ለውጥ ተብሎ የነበረው እንዲመጣ ጎንደር ቁልፍ ሚና የተጫወተች ከተማ ናት፡፡ ከወልቃይት ጥያቄ ጋር በተገናኘ፣ በጎንደር ተጀምሮ ድፍን አማራ ክልል ያጥለቀለቀው ተቃውሞ፣ ህወሃትን ወደ ጎን ለመግፋት የአንበሳውን ድርሻ ነው የሚይዘው፡፡ ያለ ጎንደር፣ ያለ ወልቃይት ጥያቄ፣ ዶር አብይ አህመድ አራት ኪሎ አይርሳትም ነበር፡፡ አቶ መላኩ ፈንታም ከእስር ቤት አይወጣም ነበር፡፡
ሆኖም በወልቃይት ሕዝብ፣ በጎንደርን ህዝብ፣ በአማራ ክልል ህዝብ፣ በአዲስ አበባ ህዝብ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፣ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው የኦህዴድ/ኦነግ ብልጽግና አገዛዝ እጅግ በጣም ትልቅ ክህደት ነው የፈጸመው፡፡
ለጊዜው ጎንደር ላይ ስናተኩር፣ የጎንደር ህዝብ በተለያየ ጊዜ ድምጹን ፣ ቅሬታውን፣ ተቃውሞዉን፣ ጥያቄዎቹን እያሰማ መሆኑን መግለጹ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ጥያቄዎቹ በነአብይ አህመድ እንኳን ሊሰሙ፣ “ህዝቡ ምን ያመጣል ?” በሚል በትልቅ ንቀት ከህዝቡ ፍላጎት በተቃራኒው እየሆነ ነው ያለው፡፡ የጎንደርን ህዝብ ትእግስትና ሰላም ወዳድነትን፣ እንደ ፍርሃትና ሞኝነት ነው በኦሮሞ ብልጽግናዎች እየተቆጠረበት ያለው፡፡ ሕጻን ልጅ ፣ “አያ ጅቦ” ሲባል እንደሚፈራው፣ የጎንደር ህዝብን ህወሃት እያልን፣ በህወሃት እያስፈራራነው ዝም እናሰኘዋለን የሚል እሳቤ ነው ያላቸው፡፡
እንግዲህ አንዱን ትልቁ ጥያቄ፣ “ላንተ እንቆምልሃለን፤ ድምጽ እንሆንልሃለን፣ ምረጠን” ያሉት ተወካዮች የት ነው ያሉት ??? የሚለው ነው፡፡ እነ ዶር ደሳለኝ ጫኔ፣ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የብልጽግና የአዲስ አበባ ተወካይ እነ ዶር መሰረት ዉሂብ የመሳሰሉትን ፣ ለወከላቸው ህዝብ የሚሟገቱትን እየሰማን ነው፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ የት ነው ያለው ? ዶር መሰረት ዘላለም የት ነው ያለችው ???? በነርሱ ዝምታስ እንዴት የጎንደር ህዝብ ድምጽ የሚሆንለት፣ የሚሟገትለት ያጣል ? ይሄስ በጎንደር ህዝብ ላይ የተፈጸም እጅግ በጣም ትልቅ ክህደት አይደለም ወይ ? ለምንስ የገቡትንስ ቃል አይጠብቁም?
አቶ መላኩ ፈንታም ሆነ ዶር መሰረት ዘላለም፣ እንኳን በፓርላማ ለጎንደር ህዝብ ሊሞግቱ ፣ ሊከራከሩ ቀርቶ፣ በፓርላውም ተገኝተው ምን እየሆነ እንዳለም የሚያውቁ ስለመሆኑ፣ አንድም ጊዜም እንደ ፓርላማ ተወካይ ህዝቡን ጠርተው ያነጋገሩበት ጊዜ እንዳለ የሚገልጹ ምንም አይነት ማስረጃዎች የሉም፡፡
አዎን ፓርላምው ፓርላማ ነው ማለት አይቻልም፡፡በተለይም የአብይ አህመድን ረጅም ውሸትና እብሪት የታጨቀባቸው፣ አሰለቺ ንግግሮች ቁጭ ብሎ ማዳመጥ እንደ ትልቅ ቅጣት ነው የሚቆጠረው፡፡ በፓርላማ ረጅም ጊዜ መቀመጥ፣ ጊዜ ማጥፋት፣ ደባሪና ደባች ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል በፓርላማ የማይገኙት፡፡ ሌላው ደግሞ ለውጥ ማምጣት አንችልም ብለውም ይሆናል፡፡
እንደዚያ ካሰቡ፣ ማድረግ የነበረባቸው፣ በይፋ፣ ከህዝብ ተወካይነታቸው እንደለቀቁ መናገርና ለጎንደር ህዝብ ሌላ ተወካይ እንዲመረጥ ማሳወቅ ነው፡፡ ያንን ቢያደርጉ፣ ቢያንስ ህዝቡን አክበሩት ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ በፓርላማ ምንም ማድረግ አይቻልም፣ ማለት ከወዲሁ ለነ አብይ አህመድ እጅ መስጠት ነው፡፡ ብዙ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አለ፡፡ በየጊዜው ጥያቄዎች እየጠየቁ፣ ረግጦ እስከመውጣት የሚደርስ እርምጃዎች እየወሰዱ፣ በፓርላማው ለተረኛውና ዘረኛው የኦህዴድ አገዛዝ ትልቅ ራስ ምታት መሆን ይችላሉ፡፡
ሜዳውንም፣ ፈርሱንም ሁሉንም ነገር ለኦሮሞ ብልጽግናዎች አሳልፈን ሰጥተን፣ ከበሻሻና ከአምቦሳ የመጡ፣ በጎንደር፣ በወልቃይት፣ በራያ፣ በአዲስ አበባ ወዘተ ባሉይ ወሳኝ ጉዳዮች እንዲወስኑ እየፈቀድን፣ “እነ አብይ አህመድ ይሄ አደረጉ” ብለን ቀንና ሌሊት በኦህዴድ ብልጽግናዎች ላይ ማማረር ማቆም አለብን፡፡
አሁን ለዶር መሰረት ዘላለምና ለአቶ መላኩ ፈንታ የምለው ይሄን ነው፡፡ እስከአሁን የሆነው ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ቢያንስ ቃል የገባችሁትን አክብሩ፡፡ ህዝቡን ስብሰቡና አነጋገሩ፡፡ ከህዝቡ ስሙ፡፡ የህዝቡን ጥያቄ የፌዴራል መንግስቱ እንዲፈጸም ባገኛችሁት መድረክ ሁሉ አንገት ለአንገት በመያያዝ ተናነቁ፡፡ ለህዝህ ከመቆም፣ ለህዝብ ከመጋፈጥ የበለጠ ክብር የለምና፡፡
ያንን ማድረግ ፍቃደኛ ካልሆናችሁ ደግሞ፣ አቶ መላኩ ምን አልባት ከዚህ በፊት እስርን ስላየ፣ ዳግም መታሰር አልፈለግም ካለ፣ ዶር መሰረት ደግሞ በጤና ጥበቃ ያገኘችውን ስልጣንና ሃላፊነት እንዳታጣ ከፈራች፣ አልቻልንም ብለው ይልቀቁ፡፡ በቃ አቶ መላኩም በአማራ ባንክ፣ ዶር መሰረት በጤና ጥበቃ ስራቸውን ይስሩ፡፡ የጎንደር ህዝብ ደግሞ ድምጹ የሚሆኑለትም ጥቅም ለማስከበር የሚተጉትም መርጦ ተወካዮችን አዲስ አበባ ይላክ፡፡