አካፋ

6 መጋቢት 2023

የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር በዩክሬን ጦርነት የሚሳተፉ የሩሲያ ተጠባባቂ ወታደሮች በጥይት እጥረት ምክንያት ‘በጨበጣ ውጊያ አካፋ’ እየተጠቀሙ ሳይሆን አይቀርም አለ።

ሚኒስቴር መሥረያ ቤቱ ባወጣው የስለላ ዘገባ ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መገባደጃ የሩሲያ ተጠባባቂዎች “የጦር መሣሪያና አካፋ” ይዘው ነው ወደ ጦር ሜዳ የዘለቁት ብሏል።

ሚኒስቴሩ፤ በጦርነቱ በ1869 የተመረተው ኤምፒኤል-50 የተሰኘው አካፋ ጥቅም ላይ ውሏል ይላል።

“ሩሲያ ውስጥ ኤምፒኤል-50 የተባለው መሣሪያ ምን ያህል ገዳይ እንደሆነ የሚነገርለት አካፋ ነው” ይላል ሪፖርቱ።

ዘገበው አክሎ የዚህ አካፋ በጦርነቱ ጥቅም ላይ መዋል “ጦርነቱ በቴክኖሎጂ የወረደና አሰቃቂ መሆኑን ያሳያል” ሲል አስነብቧል።

ከተጠባባቂ ወታደሮቹ መካከል አንዱ “በአካልም ሆነ በመንፈስ ዝግጁ ሳይሆን” ወደ ጦርነት ሜዳው እንደመጣ ሰምተናል ይላል የሚኒስቴሩ መግለጫ።

መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣው ዘገባ ጨምሮ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩክሬን ውስጥ በቅርብ ርቀት ውስጥ የሚደረጉ የደፈጣ ውጊያ እየተበራከተ እንደመጣ መረጃው አለን” ይላል።

“ይህ የሆነበት ምክንያት ሩሲያ የጦር መሣሪያ እጥረት ስለገጠማት የጦር አዛዦች ከትላልቅ ጦር መሣሪያ ይልቅ ወታደሮች በኋላ ቀር መሣሪያ እንዲዋጉ ስለሚያደርጉ ነው።”

ቢቢሲ የመካለከያ ሚኒስቴር ዘገባን በገለልተኛ ወገን ሊያጣራው አልቻለም።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል ውጊያዎች በየትኞቹ አካባቢዎች እየተካሄዱ እንደሆነ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

በሌላ በኩል የሩሲያ ወታደሮች ከበዋት የነበረችውን ባኽማት የተሰኘችውን ከተማ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥፍራ ላይ መቀመጣቸውን የጦርነት ጥናት ተቋም ገልጧል።

4 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ያሏት የባኽማት ከተማን ለመቆጣጠር የሩሲያ ወታደሮች ለወራት የዘለቀ ውጊያ አድርገዋል።

ምንም እንኳ ከተማዋ ያላት ስትራቴጂክያዊ ጥቅም ጥያቄ ቢነሳትም ከተማዋን በቁጥጥር ሥር ማዋል ለሩሲያ ወታደሮች ትልቅ ድል ሆኖ ሊቀጠር ይችላል።

የጦርነት ጥናት ተቋም እንደሚለው የሩሲያ ወታደሮች ወደከተማዋ እየገፉ መምጣት “ወሳኝ እንቅስቃሴ” ሊሆን ይችላል።

እንደ ተቋሙ ትንታኔ “ወሳኝ እንቅስቃሴ” ወደፊት እየገሰገሰ ያለ ጦር መሰል ከተማዎች ሲያስለቅቅ የጠላትን የተዘጋጀ ምሽግ መስበርና ከከበባ ይልቅ ማጥፋትን የሚያካትት ነው።

“የሩሲያ ወታደሮች ባኽማትን ለመክበብ አልመው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የዩክሬን ጦር እንዳመለከተው ከከበባ ይልቅ ከተማዋን ለቆ መውጣትን ይመርጣል” ሲል ተቋሙ ገልጧል።

ቢሆንም የዩክሬን ሠራዊት እሑድ ዕልት እንደገለጠው ከተማዋን ለቆ የመውጣት ዓላማ የለውም።

የጦር ሠራዊቱ ጄኔራል ቢሮ የሩሲያ ጦር ወደ ከተማዋ እየገሰገሰ መሆኑን አምኖ ነገር ግን በዶንባስ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት ከ100 ጊዜ በላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን መመከቱን አስታውቋል።

ከጦርነቱ በፊት 75 ሺህ ሰዎች ይኖሩባት የነበረችው ባኽማት ከተማን ለመቆጣጠር በተደረገው ውጊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች እንደሞቱ ተገልጧል።